myEthiopia.com
  • Home
  • Forum
  • Amharic
  • English
  • Zelalem

በየትኛው ፍቅር እንደመር?

4/15/2019

0 Comments

 
በዋካንዳ ዘኢትዮጵያ 
 
ከዚህ በፊት “እንዴት በይቅርታ እንሻገር?” በሚል ርዕስ በጻፍኩት ጽሁፍ መጨረሻ ላይ “በፍቅር እንደመር” ላይ ለመጻፍ ቃል ገብቼ ስለነበርቃሌን ለማክበርና የፍቅርን ታላቅ ኃይል ለመጻፍ በማሰላሰል ላይ እያለሁ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ የተከሰተ አንድ ገጠመኝ ትዝ አለኝ:: 
 
“ዳይናሚክስ” የሚባል የ”ፊዚክስ” ዘርፍ ትምህርት አስተማሪየነበረ ኢጣሊያዊ፦  ለመፍታት ከባድ የሆነ ጥያቄ እንዴት እንደሚሠራ አሳየንና “ገብቷችኋል?” ብሎ ጠየቀን፤ ሁላችንም ዝም አልን:: “አልገባችሁም?” ብሎ እንደገና ጠየቀን፤ አሁንም ዝም አልን:: ከዚህ በኋላ የሚከተለውን በላቲን ቋንቋ ጥቁር ሰሌዳ ላይ በጠመኔ ጻፈ:: “Vox Clamantis in Deserto” ትርጉሙም “በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ” ነው:: 
 
በአገራችን ኢትዮጵያ ወቅቱን በተመለከተ ብዙ መልካም ሐሳብ ያለባቸው ጽሁፎች፣ አውደ ጥናቶችና ንግግሮች ተደርገዋል፤ እየተደረጉም ነው:: በኢትዮጵያ ውስጥ የመጣውን ለውጥ አራማጆች:- ያለፉትን በደሎችና ስህተቶች ለታሪክ ተመራማሪዎች ትተን “በይቅርታ እንሻገር”፤ የተሰሩት በጎ ሥራዎች ላይ ለመጨመር “በፍቅር እንደመር”  የሚል መርሕ ይዘው ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ወደ የተሻለ አብሮ የመኖር፣ዴሞክራሲና እድገት ለማድረስ የሚያስችልን ጎዳና ለማስተካከልና የለውጡ በጎ አስተሳሰብ ተቋሟዊ እንዲሆን ሌትና ቀን እየሠሩ ይገኛሉ:: የእነዚህ መልካም አሳቢዎችና ለውጥ አራማጆች ድካም እንደ እኔ አስተማሪ ሰሚ ያጣ የምድረ በዳ ጩኸት ሆኖ ይሆን ወይ የሚል ስጋት አለኝ:: ምክንያቱም የብዙዎቻችን ጆሮዎች የሚከፈቱት ህዝብን ለሚያፋቅሩና ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሔ ለሚያመጡ ሐሳቦች ሳይሆን ለተራ አሉባልታ፣ለጥላቻና ግልብ ጀብደኝነት በመሆኑ ነው::
ያለፈውን በጎ ሥራ በማንቋሸሽና አፍርሶ አዲስ በመጀመር፣ እጃችን እስኪዝል ክፉውን በማውገዝ የትም እንደማይደረስ ተሞክሯችን አሳይቶናል:: እኛ ከዜሮ ስንጀምርና እርስ በእርሳችን ስንባላ ሌላው ዓለም ቆሞ አይጠብቀንም:: አሁን ያለንበት ዘመን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ከምንገምተው በላይ ያደገበትና ለሰው ልጆች ችግሮች መፍትሔ ለመሆን ራሱን እንደ ጥሩና ዋና አማራጭ ያቀረበበት ዘመን ነው:: እርጅናን በማዘግየት እድሜን ማራዘም ይቻል እንደሆነ ለመሞከር ከፍተኛ በጀት ተመድቦ እኛው አገር አካባቢ በሚገኝ አይጥ መሳይ ፍልፈል ላይ ምርምር እየተደረገ ነው:: ከተመሠረቱ ሃምሳ ዓመት ያልሞላቸው እንደ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ያሉ አገሮች እንኳ ማርስ ላይ የድርሻቸውን ለማግኘት ዕቅድ ይዘው እየሠሩ ይገኛሉ:: እነዚህን በምሳሌነት ያነሳሁት ቁጭት እንዲይዘንና ለመልካም ሥራ ልባችን እንዲነሳሳ በማሰብ እንጂ ብንጽፍ ልንጨርሳቸው የማንችላቸው ብዙ ሥራዎችና ምርምሮች በዓለማችን ላይ እየተከናወኑ ነው::
 
ኢትዮጵያ ብዙ ደም የፈሰሰባትና ግፍ የተሠራባት አገር ስለሆነች ብዙ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች አሉ::ጉዳት የደረሰባቸው ቂም ቢቋጥሩና በቀልን ቢያስቡ አይገርምም:: ነገር ግን በዚህ መንገድ ብንሄድ ስነልቦናዊ  እርካታ ይገኝ ይሆናል እንጂ አገራችንን ቁሉቁል ከመሄድ አይታደጋትም:: ከዚህ ይልቅ ይቅርታና ፍቅር የተሻሉ አማራጮች ናቸው::
 
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ከመምህራን ጋር በነበራቸው የውይይት ጊዜ እንደተናገሩት ብዙ አማራጮች የሉንም፤  “ወይተያይዘን እንጠፋለን ወይም ተያይዘን እናድጋለን”:: በማንኛውም የእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት የመጀመሪያዎቹ ገፈት ቀማሾች ሕፃናት፣ ሴቶች፣ አቅመ ደካሞችና አዛውንቶች ሲሆኑ የጥፋቱ አድራሽና ተማጋጅ ወጣቱ ነው:: ባለሀብቶች፣ ልሂቃንና ከፍተኛ የፓለቲካ አመራሮች የሚደርስባቸው ጉዳት ምንም ወይም በጣም አነስተኛ ነው:: ከዚህ በተጨማሪ ከገዢው ፓርቲ ጋር ይፋለሙ የነበሩ ጥቂት ፓለቲከኞችና አክቲቪስቶች በአገራችን ውስጥ ከነበረው የዴሞክራሲ እጦት የተነሳ ለረጅም ዓመታት በስደት በውጭ አገራት ስለኖሩ የሌላ አገራት ዜግነት አላቸው ብንል ስህተት አይሆንም:: እነዚህ ሰዎች አገራችን ደም በደም ብትሆንዞረው የሚገቡበት አገር አላቸው:: ዜግነት የሰጧቸው አገሮች አውሮፕላኖቻቸውንና ልዩ ሀይላቸውን በመላክ ከእሳት ውስጥ ያወጧቸዋል::
“አንቺ ምንቸገረሽ ሁለት አባት አለሽ:
አንዱ ቢሞትብሽ በአንዱ ትምያለሽ::”
ተብሎ የለ?! ለብዙዎቻችን ግን ያለችን አገር አንድ ብቻ ነች:: እሷው “ከሞተችብን” ወዴት እንሄዳለን?
እኛ ኢትዮጵያውያን ከጥላቻ ይልቅ በፍቅር ለመያያዝ የሚያስገድዱን ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች አሉን፤ ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው::
  1.  ኢትዮጵያ ጥንታዊና አኩሪ የሆኑ ታሪኮች ያላት አገር ብትሆንም ዛሬ ያለችበት ደረጃ ግን በዓለም ድሃ ከሚባሉት አገራት መደዳ ነው:: ከድህነት ወጥተን ከሰለጠኑትና ሀብታም ከሚባሉት አገራት ተርታ ልንቆም የምንችለው ወገኖቻችንን ለመግደል በከፍተኛ ወጭ ጦር በማደራጀትና በመቶ ሺዎች በሚቆጠር ብር ክላሽንኮቭና ስናይፐር በመግዛት፣ ከአገራዊ ጥቅም ይልቅ በድርጅትና ወገናዊ ፍቅር ሽፋን ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት ሌት ተቀን ከሚሠሩ ሴረኞች ጋር አውቀንም ሆነ በየዋህነት በመደመር አይደለም:: ከድህነት የምንወጣው አውዳሚ መሳሪያዎችንና አስተሳሰቦችን ከመካከላችን በማስወገድ፣ አገራችንን በጋራ ለማሳደግ ያለንን ሀብትና እውቀት በጋራ አዋጥተን፣ ለራሳችንና ለመጪው ትውልድ በማሰብ በቁርጠኝነትና በቅንነት ስንሠራ ብቻ ነው:: ይህንን ማድረግ የምንችለው እርስ በእርሳችን በፍቅር ስንደመር ነው::
  2.  ኢትዮጵያውያን ግፍ ያንገፈገፈን፣ዴሞክራሲ የራበንና እኩልነት የጠማን ነን:: እኛም ወግ ደርሶን እንደ ሌሎች አገራት ሕዝቦች ደስ ብሎን፣ መጪው ዘመን ብሩህ እንደሆነ እያሰብን፣ ገዢዎች እየፈሩን፣ ሳንሸማቀቅ ለመኖር እንፈልጋለን:: ሌሎች እንደዚህ መኖር ከቻሉ እኛም እንደነሱ ሰዎች ስለሆንን መኖር እንችላለን፤ ይገባናልም::  ግፈኞች እጃቸውን የሚሰበስቡትና ገዢዎች የሚፈሩን ሁላችንም ለአገራችን መልካም አስተሳሰብና ተግባቦት ኖሮን፣ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ መሠረት የሚሆኑት ተቋሟት እውን ሆነው፣ የስልጣን መወጣጫው መንገድ የእኛ የምርጫ ካርድ መሆኑን ሲገነዘቡ ነው:: ለዚህ ስኬት የእኛ በፍቅር መደመር ወሳኝ ነው::
  3.  እንኳን ትልቅ አገርን ለመገንባት ትንሽም ፕሮጀክት ቢሆን ሁሉም ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ካልተሳተፉበትና ካልተባበሩ አይሳካም:: ከመቶ ሚልዮን ቁጥር በላይ፣ የተለያየ  ቋንቋና ባህል ያላቸው ዜጎች የሚኖሩባትን አገር ብትንትን ባለ አስተሳሰብና ብጥስጥስ ባለ ሀብት መገንባት አይቻልም:: ትልቅ ነገርን ለመሥራት የግድ መነጋገርና መግባባት ይጠይቃል:: የጥንት ባቢሎናዉያን ሰማይ ጠቀስ ግንብ ለመሥራት ወጥነው ቋንቋቸው ሲደበላለቅ መግባባት ስለተሳናቸው ሳይጨርሱት እንደቀሩ ቅዱሱ መጽሐፍ ይነግረናል:: ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን መላው የአፍሪካ አገራት ብዙ ተስፋ ያላቸው እንደሆኑ በተለያዩ ዘርፎች የተደረጉት ጥናቶች ያመለክታሉ:: ዓለም ከአፍሪካ ጋር አብሮ ለመሥራት የአፍሪካን መመንጠቅ በጉጉት እየጠበቀ ነው:: መጪው ዘመን የእኛ ነው:: ካወቅንበት የዓለም ማዕከል እኛ እንሆናለንና ለአገራችንና ለዓለም በረከት ለመሆን በጥላቻ ከመቀነስ በፍቅር መደመር ይበጀናል::
  4. ይህ ለውጥእንዲመጣብዙ ወገኖቻችንተገርፈዋል፣ተሰቃይተዋል፣ ተዋርደዋል፣ተሰደዋል፣ቤተሰባቸው ተበትኗል፣ አካላታቸውን አጥተዋል፣ ተገድለዋል፤ ይህ ሁሉ መከራ የወረደባቸው እኛ በነጻነትና በእኩልነት እንድንኖር ነው እንጂ እርስ በእርሳችን በጥላቻ ተጠላልፈን በግፈኞች የባርነት ቀንበር ስር እንድንወድቅ አይደለም:: አሁን ያገኘነው መልካም አጋጣሚ ከእጃችን አምልጦ የብልጣ ብልጦች ሰለባ እንዳንሆን ልንፋቀር ይገባናል::እንዲህ ዓይነት ለውጥ የሚገኘው በብዙ መሥዋዕትና በረጅም ዓመታት ውስጥ አንድ ጊዜ ስለሆነ ከእጃችን ካመለጠ ተመልሶ አይመጣም፤ ከመጣም  እኛንም የሚመጣውንም ትውልድ ብዙ ዋጋአስከፍሎ ነው:: “ብልህ ልጅ የሰጡትን እየበላ ያለቅሳል” እንደሚባለው ለውጡ ያመጣልንን ትሩፋቶች በእጃችን ጨብጠን የበለጠ ስኬታማ እንዲሆን መፋቀር ግድ ነው::
  5. በዚህ ዘመን የምንኖር ኢትዮጵያውያን ሁሉ እድለኞች ነን:: ምክንያቱም የአገራችንን የፖለቲካ ልምድ ለመቀየርና የእውነተኛ ዴሞክራሲ መሠረት ለመጣል አመቺ መስመር ላይ ስለምንገኝ ነው:: ይህ እውን ሆኖ ለማየት ብዙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጓጉተው ሳያገኙት አልፈዋል፤ እኛ ግን ታሪክ ሠሪ ልንሆን ነው:: ካሳካነው በመጪው ትውልድ “አባቶቻችን አገራችንን በጽኑ መሠረት ላይ ተክለዋት አስረከቡን” የምንባልበት ጊዜ በቅርብ ርቀት ላይ ነው:: 
  6. ኢትዮጵያውያን ከፈጣሪ ጋር ጥብቅ ግንኙነት አለን:: ከፈጣሪያችን ፍቅርንና ይቅርታን ተምረን ለሰዎች ሁሉ ይህንኑ እንድናደርግ ትእዛዝ ተሰጥቶናል:: ስለዚህ በፍቅር መያያዝና መደመር ሃይማኖታዊ ምግባራችንም ነው::
 
ፍቅር ለሰው ልጆች አዲስ አይደለም፤የማያፈቅር ሰው የለም:: ጨካኞች የሚባሉ ሰዎች እንኳ ያፈቅራሉ:: በአለማችንም ሆነ በአገራችን  በሰዎች ላይ እኩይና አሰቃቂ ድርጊቶችን የፈፀሙ ግፈኞች ልጆቻቸውንና የቅርብ ዘመዶቻቸውን ማንኛችንም እንደምናደርገው በፈገግታ ሲያስተናግዷቸው፣ ሲንከባከቧቸው፣ ሲያቅፏቸው፣ ሲስሟቸውናፍቅራቸውን በተለያየ መንገድ ሲገልፁላቸው እንመለከታለን::ፍቅር በግል ኑሯችን የተለመደ ቢሆንም በአገራችን የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ግን እንግዳ ነው:: እንዲያውም ፍቅርን በፖለቲካ ውስጥ ማስገባት ጅልነት፣ አጉል ሃይማኖተኛነትና የዋህነት  በተቃራኒው ግን ጥላቻ፣ መጠላለፍ፣ ተንኮልና ሸር የመሳሰሉት እኩይ ሐሳቦችና ተግባራት ግን እንደ የፖለቲካ ምህንድስናነት የሚቆጥሩ ፖለቲከኞች አሉ:: በአገራችን ቢያንስ ለአርባ ዓመታት የመንግሥትን ከፍተኛውን ሥልጣን የያዙ ግለሰቦችና ቡድኖች ሕዝብን በመደብ፣ በርዕዮተዓለም፣ በዘርና በቋንቋ አልፎ አልፎም በሃይማኖት በመክፈል አንዱ ለአንዱ ስጋት እንደሆነ እንዲያስብ አድርገዋል:: ይህንን ያደረጉበት ምክንያት በአገራችን ውስጥ የነበሩትንና ያሉትን ችግሮች ይፈቱልናል ብለው አንዳንዶቹ ከቅንነት ሌሎቹ ደግም ከእኩይነት ሊሆን ቢችልም ይህ “ቤተ ሙከራ” ብዙ ሰዎችን ለሞትና የአካል መጉደል፣ ለእስራትና ግርፋት፣ ለስደትና መፈናቀል ዳርጓል፤ በማኅበረሰቡ ዘንድ ደግሞ ጥላቻ፣ መከፋፈል፣ አለመተማመንና ጽንፈኝነትን ሲያገዝፍ መልካም ዕሴቶቹን ደግሞ አኮስሷል::
 
“በፍቅር እንደመር” በሚለው መርሕ ላይ ብዙ አስተያየትና በቂ ውይይት ሲደረግ አይስተዋልም:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድም ብዙ ዓይነት ፍቅር እንዳለ ጠንቅቀው ቢያውቁም በፍቅር እንደመር አሉን እንጂ እንዴትና በየትኛው ፍቅር እንደምንደመር አላብራሩልንም፤ቢያንስ እኔ አልሰማሁም:: ስለዚህ እንደ ህልም ሁላችንም የራሳችንን ፍቺዎች ይዘን በመጓዝ ላይ እንገኛለን:: አንዳንዶች ዶ/ር ዐብይን መውደድ የሚል ፍቺ ይዘው ሲጓዙ ሌሎች ደግሞ እነ አቶ ለማንና አቶ ገዱን ሲጨምሩ ሌሎች ደግሞ የተወሰኑ አክቲቪስቶችንና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሲያካትቱ እኔም ደግሞ የራሴን ፍቺ ለመስጠት እየተንደረደርኩ ነው::
 
በእኔ አስተሳሰብ ፍቅር በሁለት ይከፈላል፤ እነርሱም “ዓይነ ስውር”ና “ዓይናማ” ናቸው:: እያንዳንዳቸው ደግሞ የተለያዩ የፍቅር አይነቶችን በውስጣቸው ይይዛሉ:: ሁሉም የፍቅር አይነቶች  በአገራችን በተጀመረው ለውጥ ላይ አዎንታዊና አሉታዊ ተፅእኖ አላቸው:: የእኛ ድርሻ አሉታዊ ተፅዕኖውን በማስወገድ አዎንታዊውን በማቀፍ ለውጡ ስኬታማ እንዲሆን “በፍቅር መደመር” ነው:: 
 
ስሜታዊ ፍቅር
 
ስሜታዊ ፍቅር በተቃራኒ ፆታዎች መካከል ወይም አዲስ ነገር ስንጀምር (ለምሳሌ ስፖርት) ወይም አዲስ ነገር ስናገኝ (ለምሳሌ ልጅ) የሚታይ ሲሆን  ላፈቀርነው ሰው ወይም  ለጀመርነውና ላገኘነው አዲስ ነገር ከፍተኛ የሆነ ጉጉትና “እፍ እፍ” ያለ ስሜት ስለሚኖረን ወሬያችንም ሆነ ህልማችን በዚሁ ዙሪያ ብቻ ይሆናል:: ይህ ፍቅር ምናባዊ የሆነ ረጅም ግብና ተስፋ ቢኖረውም ዋናው ትኩረቱ ግን በአጭር ጊዜያት በሚገኙ እርካታዎችና ውጤቶች ላይ ነው::
 
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዶ/ር ዐብይ አሕመድን ጠቅላይ ሚኒስትርነት ካፀደቀ በኋላ ዶ/ር ዐብይ በፖርላማው ፊት ከዚህ በፊት ከነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሮች በተለየ መልኩ በጎና “አዳዲስ ሐሳቦችን” በመናገራቸው “በፍቅር ተነድፎ” ያልተደመረ ማን አለ? በአገራችን ፖለቲከኞች ዘንድ እንግዳ የሆኑትንና ያልተለመዱትን ይቅርታንና ፍቅርን ሲናገሩ፣ የገዢውን ፓርቲና መንግሥት ጥፋቶች በማመን ሕዝብን ይቅርታ ሲጠይቁ፣ ተቃዋሚዎችን ተፎካካሪ ሲሉ፣ የአገርና የሕዝብ አንድነት ላይ ትኩረት ሲሰጡ፣ ሌብነትን ሲጠየፉ፣ የኢትዮጵያን የቀድሞ ክብር ለመመለስ እንደሚጥሩ፣የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ግንባታ እንደሚሠሩ ቃል ሲገቡ፣ እንደማንኛችንም እናታቸውን፣ባለቤታቸውንና ጓደኞቻቸውን ሲያመሰግኑ፣ ከአርባ ዓመታት በኋላ በከፍተኛ የአገራችን አመራሮች ፊት ፈጣሪን ሲጠሩና  ከእርሱም ዘንድ የሆነ በረከትን ለኢትዮጵያና ሕዝቧ ሲመኙ ስሜቱ ተነክቶና ብሩህ ተስፋ ሰንቆ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከለውጡ ግንባር ቀደም መሪዎችና ካነሷቸው አዳዲስ ሐሳቦችና መርሖዎች ጋር “እፍ” ያለ ፍቅር ይዞት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእነሱና ሐሳቦቻቸው ጋር “መደመሩን” ወዲያውኑ ገልጾላቸዋል:: ሕዝቡ የሚወደውን የእግር ኳስ ጨዋታ እንኳ ትቶ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ለመስማት ተመልካች አጥቶ ወደነበረው የመንግሥት ቴሌቭዥን ጣቢያ የዞረው በዚህ ፍቅር በመደመሩ ነው::
 
ከእስር ይፈታሉ ተብሎ የማይጠበቁና ሞታቸውን የሚጠባበቁ ፓለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ የመብት ታጋዮች፣ ጦማሪዎችና አክቲቪስቶች እንደ ጎርፍ ከወህኒ ቤት ሲለቀቁ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና በሽብርተኝነት የተፈረጁ ድርጅቶችና አመራሮቻቸው ወደ አገር ቤት ሲመለሱ  ያልተደሰቱ ቢኖሩ በጣም ጥቂቶች ቡድኖችና ግለሰቦች ናቸው::
 
ይህ ፍቅር ስሜታዊ ቢሆንም በሕዝቡና በለውጡ አራማጆች ዘንድ መተማመንን ፈጥሯል፤ ለመሪዎቹም ረጅም ርቀት አብረው ለመጓዝና ካሰቡት ግብ ለመድረስ የሚያስችሏቸውን ርምጃዎች ለመውሰድ ድፍረትን ሰጥቷል::ከዚህም የተነሳ የዶር ዐብይ መንግሥት የእርሳቸው ችሎታና ቁርጠኝነት ተጨምሮበት በአጭር ጊዜ ይሆናሉ ተብለው ያልተጠበቁ ስኬቶችን አስመዝግቧል:: 
 
ይህ ፍቅር ስሜታዊ ብቻ ሳይሆን “ዓይነ ስውር”ም ነው:: ይህ ባህርዩ ለዘር፣ ለቀለም፣ ለባህል፣ ለቋንቋ፣ ለእምነትና ፖለቲካዊ አመለካከት ልዩነቶች ብዙም ግድ የሌለው እንዲሆን ያደርገዋል:: ስለዚህ ሕዝብን ለማስተባበር ብርቱ አቅም አለው:: ለዚህም ነው ከዚህ በፊት ከታዩት የድጋፍ ሰልፎች የላቀ ትዕይንት ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ የታየው:: 
 
ስሜታዊ ፍቅር ለመሪዎች ብርቱ ተገን ለሕዝብ ደግሞ ብሩህ ተስፋን ቢሰጥም መጀመሪያ በነበረው ግለቱ ግን መቀጠል አይችልም:: ወረተኛ ስለሆነና ውጤትን ቶሎ ስለሚጠብቅ ይዝላል ወይም የአጭር ጊዜ ፍላጎቱን አርክቶ ይቀዘቅዛል ወይም ውጤቱና አዝማሚያው እንደጠበቀው ሳይሆንለት ይቀርና ፍቅሩ ይበርዳል:: ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች የፍቅር አይነቶች “ዓይን” ይፈጥሩለትና “ዓይነ ስውር” ለሆነባቸው ልዩነቶች ትኩረት በመስጠት ስፍራውን ለእነርሱ መልቀቅ ይጀምራል:: 
 
ስለዚህ በስሜታዊ ፍቅር የተደመሩ ከለውጡ ጋር በመጀመሪያ በነበራቸው ግለት መቀጠል ይሳናቸዋል:: በምትኩም በዓይናማ ፍቅሮች በመነደፍ ለውጡን በነሱ መነጽር መመልከት ይጀምራሉ፤ የለውጡን መነሻና ዋና ግብ ይረሳሉ:: አንዳንዶቹም ከተለያዩ አቅጣጫዎች በለውጡ በጎ አስተሳሰብና ድርጊት ላይ በሚወረወሩት ፍላጻዎች ልባቸው በመዛሉና በመፍራት ወይም በቅጽበት በተገኙት “ድሎች” በመርካት “እንግዲህ እርሱ ያውቃል” በማለት ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርገው ወደ የዕለት ተዕለት ኑሯቸው ይመለሳሉ:: ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም “ማድፈጥ” የሚሉት ይህንን ክስተት ይመስለኛል::
 
የስሜታዊ ፍቅር “ዓይነ ስውርነት” በ“ዓይናማ” ፍቅሮች መተካቱ የተፈጥሮ ሕግ ብቻ ሳይሆን መልካምና ክፉን እንድንመለከት ስለሚረዱንም አስፈላጊም ናቸው:: እነዚህ “ዓይናማ” ፍቅሮች በማኅበረስቡ ዘንድ አዎንታዊና አሉታዊ ተጽእኖ ስላላቸው የትኞቹ እንደሆኑ ተመልክተን፣አሉታዊውን በማስወገድአዎንታዊውን በመያዝ ለሁላችንም የምትመችና የምትበቃ ኢትዮጵያን መገንባት እንችላለን::
 
በነገራችን ላይ “ሁላችሁም በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል መኖር ትችላላችሁ”፤ ከውጭ አገራት ለሚመጡ ሁሉ “እንኳን ደህና መጣችሁ” የሚል የፌደራል መንግሥት አግኝተናል፤ ነገር ግን በዓይናማ ፍቅሮች አሉታዊ ተጽእኖ ምክንያት አገር ውስጥና አጠገባቸው ለሚኖሩ ማኅበረሰቦች ይህንኑ የሚያተጋቡ ማኅበረሰቦች፣ የወረዳና የክልል መስተዳደሮች ሙሉ ለሙሉ አላገኘንም:: እንዲህ ዓይነት ተቃርኖ ካለበት ኑሮ መውጣት የምንችለው በትክክለኛው ፍቅር ስንደመር ነው:: 
 
ወገናዊ  ፍቅር
 
ወገናዊ ፍቅር ወላጆች ለልጆቻቸው፣ ልጆች ለወላጆቻቸውና ለእርስ በእርሳቸው ያላቸው ፍቅር ነው:: ይህ ፍቅር ተፈጥሯዊ ነው:: ያለ እርሱ ቤተሰብን መገንባት አይቻልም:: አንድ ቤተሰብ ተደጋግፎና ተሳስቦ መኖር የሚችለው ይህ ፍቅር በመኖሩ ነው:: የዚህ ፍቅር መሠረቱና  ሰዎችን የሚወድበት ዕይታው የሥጋ ዝምድና ወይም የደም ትስስር በመሆኑ “ዓይናማ” ነው:: ስለዚህ የሥጋ ዝምድና የሌለው ሰው ወገናዊ ፍቅርን ማግኘት አይችልም:: ይህ ፍቅር ቀስ በቀስ ወደ የቅርብና ሩቅ ዘመዶች ይደርሳል:: ባናውቃቸውም የሥጋ ዘመዶቻችሁ ናቸው ስለተባልን ብቻ ከሌላው ሰው የተለየ ፍቅር ለእነርሱ ይኖረናል:: ቁጥሩ እየጨመረ ይሄድና ማኅበረሰብ መመሥረት ይጀምራል:: 
 
የአንትሮፖሎጂና የስነልቦና ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ በሰው አዕምሮ ውስንነት የተነሳ አንድ ሰው ትርጉም ያለው ግንኙነት ማድረግ የሚችለው በአማካኝ ከ150 ሰዎች ጋር ነው:: ስለዚህ ከዚህ ቁጥር በላይ ከሆኑ ሰዎች ጋር በረጅሙም ቢሆን  ሊያስተሳስሩት የሚችሉ እንደ ቀለም፣ ባህልና ቋንቋ ያሉትን ከሳሳ የደም ትስስር ጋር አጋምዶ ከእርሱ አጠገብ የሚኖሩትንና ተመሳሳይ ቀለም፣ ባህልና ቋንቋ ያላቸውን በቅጡ ባያውቃቸውም እንኳ “ወገኖቼ”፣ “የኔ ጎሳ”፣ “የኔ ዘር”፣ በዘመኑ አባባል ደግሞ “የኔ ብሔር”፣ “የኔ ብሔረሰብ” በማለት ይህንን ፍቅር ይቸራቸዋል::
 
ወገናዊ ፍቅር ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ በራሱ ወገን መካከል ግጭትና መቃቃር ሲኖር የመፍታትና የማክሰም ኃይል አለው:: ከዚህም የተነሳ ለአንድ ማኅበረሰብ ቆመናል የሚሉ “ዘር ተኮር ድርጅቶች” በመካከላቸው የሚታዩትን ልዩነቶች ለመፍታት ለእርስ በእርሳቸው ከፍተኛ ትዕግሥት ያሳያሉ:: ለዚህም ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን በኦዴፓና በኦነግመካከል የተደረጉትና እየተደረጉ ያሉት ድርድሮች ናቸው:: ይህ ድርጊት የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ፣ ንብረት እንዳይወድምና በአጠቃላይ አገር እንዳይጎዳ ስለሚያደርግ አዎንታዊ ጠቀሜታው ብዙ ነው:: 
 
ወገናዊ ፍቅር አንድ ተጨማሪ እርምጃ ሄዶ ለሌላው ማኅበረሰብ ይህንኑ ትዕግሥትና ፍቅር ለመቸር ያለው አቅም ውስን ነው:: ከራስ በላይ ነፋስ የሚል አባዜ ስለሚጠናወተው የራሱን ወገን ጥቅም ላይ ብቻ ስለሚያተኩር ትዕግሥቱና ፍቅሩ ለሌላው ሲሆን ቶሎ ታልቅበታለች:: ለዚህም ከዋና ዋና ምክንያቶቹ ውስጥ አንዱ ያ “ዓይናማ” ዐይኑ ለቤተሰቡ፣ ለሥጋ ዘመዶቹና ወገኔ ላለው ማኅበረሰብ መጨፈኑ ነው:: ስህተታቸውን ይሸፍናል፤ ስለዚህ እውነትንና ፍትሕን ለማዛባት ትንሽ የቤተሰብ ጫና ይበቃዋል::  ከእርሱ ልዩነት ያላቸውን ማኅበረሰቦችእኩል ፍቅር መስጠት ስለሚሳነው በአድሏዊነት ወጥመድ ውስጥ ይገባል:: በአማራና በትግራይ ክልል መስተዳደሮች መካከል ያሉትን መቃቃሮች ለማርገብ የሦስተኛ ወገን ሽምግልና ያስፈለገውሁለቱም መስተዳደሮች ቅድሚያ የሚሰጡት ለራሳቸው ወገን በመሆኑ ይመስለኛል::
 
በወገናዊ ፍቅር የሚደመሩ በመጀመሪያ የሚያዩት የለውጡ መሪዎች እነማን እንደሆኑ ነው:: ፍቅራቸው ዓይናማ ስለሆነ መሪዎቹ ከእነርሱ ወገን መሆን አለመሆናቸውን ይመለከታሉ:: ከእነርሱ ማኅበረሰብ ከሆኑ ይደመራሉ ወይም ቢያንስ በቀና ዓይን ይመለከቷቸዋል:: ካልሆኑ ግን ለውጡን ባይቃወሙትም መሪዎቹን ግን መጠራጠራቸው አይቀርም:: ለምን ብለን ብንጠይቅ ምክንያቱ የሰው የተፈጥሮ ባህርይ ስለሆነ ነው:: ይህንን የሚክድ ካለ ራሱን ለጥቂት ጊዜ ቢመለከት መልሱን ያገኘዋል::
 
ወገናዊ ፍቅር ከነዚህ ፈተናዎች አምልጦ ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር ግንኙነቱን መመሥረትና በእኩል ለማየት የሚችለው የጨፈነውን ዐይን የሚገልጡለትና ዕይታውን የሚያሰፉለት ሁኔታዎች ሲኖሩ ነው:: በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል የሚደረግ ጋብቻና የንግድ ግንኙነቶች ትንሽ ይረዳሉ፤ ነገር ግን ሁሉን ለመድረስ ውስን ናቸው:: ከዚህ ይልቅ የሰውን ልጅ ክቡርነትና ተደጋጋፊነት የሚያስተምሩ ሃይማኖቶች፣  ርዕዮቶች፣ እውቀቶችና አመለካከቶች በተሻለ መንገድ ይረዱታል:: ብንቀበለውም ባንቀበለውም አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በእርሱ ካለው ፍቅር ይልቅ ወገናዊ ፍቅሩ አይሎበታል:: “እንኳን ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ” እንደሚባለው እንኳን ለራስህ ማኅበረሰብ ብቻ ተጨነቅ ተብሎ ሰው በተፈጥሮው የሚወደው “የኔ” የሚለውን ነው:: ስለዚህ ወገናዊ ፍቅርን በማጉላት፣ ለሌላው ማኅበረሰብ ንቀትን በማሳየት፣ ግዴለሽ በመሆንና ጥላቻን በመዝራት  ትልቅ አገርን ለመገንባት መሞከር ውጤቱ ውሃን የመውቀጥ ያክል ነው:: 
 
በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉና ነገ ሥልጣን ላይ ለመውጣት እየተዘጋጁ ያሉ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ዘርና ቋንቋን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ሥርዐት ባለበት አገር “ወገኔ” የሚሉት ማኅበረሰብ በሰላም ጊዜ ለሥልጣን የሚያበቃቸው በችግራቸው ጊዜ ደግሞ ሌላውን ማኅበረሰብ ማስፈራሪያቸው አድርገው ሊጠቀሙበትና ለዚህም ተግባር ሊያንቀሳቅሱት መሞከር አይገባቸውም:: ይልቁንም የተደመሩትን ከሌላው የአገሪቱ ማኅበረሰቦች ጋር አብረው በሰላም እንዲኖሩ መምከርና በወገናዊነታቸው የተለየ እንክብካቤናጥቅም እንደማይሰጧቸው ቁርጥ አድርገው መንገር ይጠበቅባቸዋል:: ለወገኖቻቸው የአንድ የስልክ ጥሪ ርቀት፣ለሌላው ማኅበረሰብ የሰማይ ያክል ርቀት ካላቸው ያው የበፊቱን ስህተት ስለሚደግሙት ውሎ አድሮ ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር ቅራኔ ውስጥ ይገቡና ለውጡ ባይቀለበስም ይጨናገፋል:: ይህ እንዳይሆን የሁሉም ማኅበረሰብ አባሎች በእኩልነት ትኩረት የሚያገኙበትን ተቋም ማቋቋም ያስፈልጋል::
 
እውነትን እንነጋገር ከተባለ በወገናዊ ፍቅር ብቻ(ብቻ ማለቴን ልብ በሉልኝ) የተመሠረተ መደመር እንኳን ለተጀመረው ለውጥ ድጋፍ ሊሆን ለራሱም የትም አይደርስም:: በአገራችን አንጋፋ የተባሉና በወገናዊ ፍቅር ብቻ የተሰበሰቡ ድርጅቶች ከፍጅትና ከፖለቲካ ኪሳራ በስተቀር ያመጡት ውጤት የለም:: አሁንም ይህንን በስፋት እያቀነቀኑ ያሉ ድርጅቶችና ግለሰቦች አገራችን ኢትዮጵያ እንድትሆንልን ለምንፈልገው የሰላም፣ የእውነተኛ ዴሞክራሲና የላቀ እድገት የሚኖራቸው አስተዋጽዖ አነስተኛ ነው፤ ይልቅኑ ከፖለቲካ ድርጅትነት ወደ አክቲቪስትነት ተቀይረው ቢንቀሳቀሱ የተሻለ ሥራ ይሠሩ ይሆናል:: በዚህ ፍቅር ላይ የተመሠረተን ትግል አላዋጪነት የተረዱ ድርጅቶች ወገናቸውን ሊያስተባብርላቸው የሚችል፣ ሌላውን ማኅበረሰብ ስጋት ውስጥ የማይከት፣ የሕዝብን አመኔታን የሚያስገኝና ዘላቂ የሆነ ውጤት ያመጣልናል ያሉትን የፖለቲካ ፕሮግራም በመቅረፅ የተሻለ አመራር በመስጠት ላይ ይገኛሉ:: 
 
ወገናዊ ፍቅርን ከሰው ሕይወት ውስጥ ማስወገድ አይቻልም፤ የተፈጥሮ ፀጋና ለሰው ልጆች ፍቅር ለመስጠት እንድንችል መሠረት ነው:: በቅርብ ያሉትን ወንድሞችና እህቶቻቸንን መውደድ ካልቻልን በሩቅ ያሉትን መውደድ እንዴት ይቻላል? ወገናዊ ፍቅርን የተለያዩ መጥፎ ቅጥያዎች በመስጠት ለማጥፋት መሞከር ትርፉ ድካም ነው፤ አይጠፋም:: ነገር ግን የፍቅር አድማሱን ማስፋትና ሚዛናዊ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል፤ ለዚህም እንዲረዳው ሌላ ዓይናማ ፍቅር ያስፈልገዋል:: ይህ ፍቅር የጓዶች ፍቅር ነው::
 
የጓዶች ፍቅር
 
የጓዶች ፍቅር “ዓይናማ”ሲሆን ከወገናዊ ፍቅር ግን የተሻለና የሰፋ ዕይታ አለው:: ምክንያቱም የጓዶች ፍቅር መሠረቶች የጋራ ዓላማ፣ ርዕዮት፣እምነት፣ ሃይማኖትና አስተሳሰብ ስለሆኑ ነው:: ይህ ፍቅር የዘር፣ የቆዳ ቀለም፣ የባህልና የቋንቋ ልዩነቶች ሳይገድቡት ከእርሱ እሳቤ ጋር የሚመሳሰሉትን ሁሉ ይወዳል::በተለይ በጋራ እምነታቸው ላይ ተቀራርበው የሚሠሩ ሰዎች በመካከላቸው  የሚኖራቸው የጓደኝነት ፍቅርና መግባባት ጥልቅ ስለሚሆን መልካምሥራ ለመሥራት የሚያስችል ትልቅ አቅም ይኖራቸዋል:: ይህ ፍቅር ከለውጡ ጋር ለመደመር ዋናው መስፈርቱ የለውጡን ግንባር ቀደም መሪዎችን የፖለቲካ አቋማቸውን፣በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ፓሊሲ፣ ርዕዮታቸውን፣ ባህርያቸውን፣ ምግባራቸውን፣ ሚዛናዊነታቸውን፣ ለተቃዋሚዎቻቸው ያላቸውን ዕይታና የመሳሰሉትን እንጂ ዘራቸውንና የሚናገሩትን ቋንቋ አይደለም::
 
የጓዶች ፍቅር እንደ ስሜታዊ ፍቅር ወረተኛና ግልብ፣እንደ ወገናዊ ፍቅር በአንድ ማኅበረሰብ ጉያ ስር የተሸጎጠ አይደለም:: ነገር ግን  ሁኔታዎችን ለመተንተንና አቋም ለመውሰድ ችሎታ ያለው፣ በአመክንዮና የሐሳብ ፍጭት የሚያምን፣ ከተለያዩ ማኅበረሰቦች የመጡ ሰዎችን ለትልቅና አገር አቀፋዊ ዓላማ ማሰለፍ የሚችል ነው:: የዚህ ፍቅር ትልቁ ኃይሉ የሐሳብ ልዕልናና የአዕምሮ ነፃነት ነው:: ስለዚህ ለውጡ ስር ሰድዶ ወደታለመለት ግብ እንዲደርስ ታላቅ ሚና ይጫወታል:: ሁላችንም እንደምናውቀው በሰላማዊና መንገድና በነፍጥ ከመንግሥት ጋር ይፋለሙ የነበሩ ተቃዋሚ ድርጅቶችና ግለሰቦች የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው ወደ አገር ቤት ገብተዋል:: አብዛኛዎቹይህንን ያደረጉበት ዋነኛ ምክንያት የተጀመረው የሰላም፣ የዴሞክራሲና የአገር ግንባታ እሳቤ የእነርሱም አጀንዳ በመሆኑ የድርሻቸውን ለማበርከት ነው እንጂ በስሜት ወይም በወገናዊ ፍቅር  ተነሳስተው አይደለም::
 
በኢትዮጵያ ውስጥ የፓለቲካ ፕሮግራም በመቅረጽ ከተለያዩ ማኅበረሰቦች የተውጣጡ ሰዎችን ያቀፉ ድርጅቶችና የፓለቲካ ፓርቲዎች አሉ:: አንዳንድ ዘር ተኮር የሆኑ ድርጅቶችም ከሌላው ማኅበረሰብ ዘር ተኮር ከሆኑ ድርጅቶች ጋር የጋራና አገር አቀፋዊ ግብ እስካላቸው ድረስ አብረው ለመሥራት በመስማማት ወገናዊ ፍቅር የጎደለውን ዕይታ አስፍተውለታል:: ይህ አቅጣጫ ለተጀመረው ለውጥ ብርቱ ድጋፍ ነው:: ነገር ግን የፓርቲዎቹ ቁጥር መብዛትና አቅም ማነስ ግዙፍ ለሆነው ገዢ ፓርቲ ያለተቀናቃኝ ስልጣን በቀላሉ ይዞ እንዲቀመጥና ህዝቡ ጥሩ አማራጭ እንዳይኖረው በማድረግ ለውጡ የታለመለትን ግብ እንዳይመታ ያደርገዋል:: 
 
የመጪው ምርጫ ክርክሮች ከወሰን፣ ከማንነትና ከአዲስ አበባ አጀንዳዎች ሻገር ሊል የሚችለው በጓዶች ፍቅር በተሰባሰቡ ድርጅቶችና ፓርቲዎች አማካኝነት ስለሆነ የተበታተኑት ሰብሰብ ብለው ሞቅና በሳል ክርክር ለማድረግ ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል:: ይህንን ካላደረጉ ግን ጭቆና ያንገፈገፈውና እውነተኛ ዴሞክራሲ የተራበውን የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ “በአዲስ አበባና በፊንፊኔ”፣ “በወልቃይትና ራያ አማራነትና ትግሬነት” ለመሳሰሉ ውዝግቦችና አማራጮች አሳልፈው በመስጠት ትልቅ የታሪክ ስህተት ይሰራሉ:: የምርጫ ካርዳችንን የምንሰጠውተወዳዳሪዎች ስለ ዴሞክራሲ፣ ኢኮኖሚ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ውጭ ጉዳይ፣ የአገር ደህንነትና መከላከል ፣ ሴቶችና የመሳሰሉት ላይ በሚኖራቸው ፓሊሲ መሆኑ ቀርቶ ለወሰን አስማሪዎች ከሆነ መጪው ምርጫ በአለም አቀፍ ደረጃ አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን የህፃን ጨዋታ ይሆናል:: ምክንያቱም ወሰን አስማሪዎችን ለመምረጥ ምርጫ ማድረግ አላስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ለእውነተኛ ዴሞክራሲ መጎልበትና የአገር እድገት የሚኖረው አስተዋፅዖ እጅግ ውስን በመሆኑ ነው:: በዴሞክራሲ የጎለበቱ አገራትና አለም አቀፍ ማኅበረሰብ “ኋላ ቀር ለሆነ ጥቁር ህዝብ በቂው ነው” የሚለውን አሽሙር ሰንዝረው ቀጣዩን ርምጃችንን ይጠባበቃሉ:: ተስፋችን ግን ብልህና ብዙ ኃላፊነት የሚሰማቸው መሪዎች፣ ድርጅቶች፣ ፓርቲዎችና ግለሰቦች በአገራችን ስላሉ ከዚህ ጉድ ይታደጉናል የሚል ነው::
 
የወሰንና የማንነት ጉዳዮች ተገቢ ጥያቄዎች መሆናቸው አልጠፋኝም፤ የብዙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ስሜት የሚነኩ ናቸው:: ነገር ግን እውነተኛ መፍትሔ የሚያገኙት በምርጫ ሳይሆን በይቅርታና በፍቅር ብቻ ነው:: ይቅርታና ፍቅር በሰዎች መካከል መቀራረብን፣ መቀባበልንና መተሳሰብን ስለሚያመጡ የራስ ዳሸን ተራራ የመሰለው ችግራችን የምስጥ ኩይሳ ይሆናል:: በህዝብና ህዝብ መካከል ፍቅርና ይቅር መባባል ካለና አብረን ለመኖር ከተስማማን ምድርስ ወሰንስ ምንድነው? ምድር ለሰው ተፈጥሯል እንጂ ሰው ለምድር አልተፈጠረም:: ምድርስ ያለ ሰው ምን ዋጋ አለው?
 
የጓዶች ፍቅር የሚከስመው በውስጡ የሚነሱ አዳዲስ ሀሳቦችን ማስተናገድ ሲሳነው፣ እኔና እኔ ብቻ ትክክል ነኝ ማለት ሲጀምርናጓደኛሞቹ ለወገናዊ ፍቅር እጅ ሲሰጡ ነው::  ይህ በሚሆንበት ጊዜ ትልቅ ራዕይ ያለው የጓዶች ፍቅር ወደ ጭፍን የድርጅትና ወገናዊ ፍቅር ዝቅ ይላል:: በዚህም ሳይወሰን ሌላ እሳቤ ያላቸውን ሁሉ በጠላትነት በመፈረጅ ያለውን አቅም ሁሉ አሰባስቦ “የጡንቻ” ፖለቲካ ውስጥ ይገባና ለለውጡም ሆነ ለአገር ደንቃራ ይሆናል:: በአሁኑ ወቅት “በዚህና በዚህ ጉዳይ ድርድር የለም” የሚሉ አባባሎች የእውቀት ማነስና የሐሳብ ድህነትን ማሳያ ከመሆናቸው በላይ የዚህ ፍቅር መልካምነትን ወደ ጨለማነት የሚቀይሩ ናቸውና ከአገራችን ፓለቲካ ውስጥ መወገድ ይኖርባቸዋል:: የሌላው ሐሳብ ከእኛ ሐሳብ ከላቀ የራሳችንን ብንተው ምን ጉዳት አለው? ደግሞስ በዴሞክራሲ ካመንን የህዝብ ድምፅ ይዳኘን የለ? ስለዚህ ከእኛ በተለየ ሐሳብ አንሸበር፤መንገድ አንዝጋ፤ ሰው አናፈናቅል፤ ይልቁኑ ሐሳብን በማመንጨት የሰውን ልብና አዕምሮ እንማርክ::
 
በቅርቡ የአማራና የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳደሮች አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በሃይማኖት መሪዎችና በአገር ሽማግሌዎች ፊት በሁለቱ ክልሎች መካከል የተከሰቱትን ችግሮች በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በጋራ ቃል በገቡበት ወቅት ዶ/ር ደብረጽዮን “ከገዱ ጋር ወንድማማቾች ብቻ አይደለንም፤ በፓለቲካም ጓዶች ነን፤ ከወንድምነት በላይ ነው ግንኙነታችን” ብለው ነበር:: ይህንን ያሉት ከልባቸው ይሁን ወይም አይሁን በጊዜ ውስጥ የሚታይ ቢሆንም፤ ይህ ከወንድምነት በላይ ያለ ግንኙነት የጓዶች ፍቅር ነው::  ዶ/ር ደብረጽዮን በተደጋጋሚ “አዝኛለሁ” ሲሉ የነበረው ይህ ፍቅር ከወገናዊ ፍቅር የተሻለ ሆኖ እያለ በሁለቱ ክልሎች መካከል ያሉትን ችግሮች ያለ ሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት መፍታት ባለመቻላቸው ይመስለኛል::
 
ችግሮቻቸውን መፍታት ያልቻሉበት መሠረታዊ ምክንያት ወይ መስተዳደሮቹ በተሻለ መንገድ ተባብረው ከክልሎቻቸው ባሻገር ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሆን ቁም ነገር መሥራት የሚያስችላቸውንና ያፋቀራቸውን የጋራ አመለካከት ወደ ጎን ብለው በወገናዊ ፍቅር ስለተሸበቡ ነው፤ አለበለዚያ ለጓዳዊ ፍቅራቸው መሠረት የሆነው የጋራ አስተሳሰብ ዛሬ በመካከላቸው ባለመኖሩ ሊሆን ይችላል::ስለዚህ የሁለቱም ክልሎች መስተዳደሮች የጎንዮሽ ላይ ያሉትን አናሳ ጉዳዮች እንደ ዋና አጀንዳና መነጋገሪያ ከማድረግ ይልቅ መሠረታዊ በሆኑት ችግሮቻቸው ላይ በትሁት ልብ ተነጋግረው፤ ካስፈለገም ሐሳብን በማቻቻል ለክልሎቻቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዘላቂ ሰላምንና እፎይታን  እንደሚያመጡ ተስፋ አደርጋለሁ:: ዛሬ ብቸኛ አማራጮች ናቸው የተባሉት ነገ የሚያረጁና ላይሆኑ እንደሚችሉ ለመረዳት የሰው ልጅ ከምንም ተነስቶ ዛሬ የደረሰበትን መመልከት በቂ ነው::
 
እስካሁን ካየናቸው ፍቅሮች የጓዶች ፍቅር ለጋራ ዓላማ ብዙ ማኅበረሰቦችን በማካተትና በሐሳብ ልዕልና በማመኑ የተሻለ ቢሆንም ለራሱ ጓዶች አድልዖ ከማድረግ ግን ነፃ አይሆንም::    በተለይ በአገራችን ያሉ ድርጅቶችና ፓርቲዎች ከሌላው ለመማር ያላቸው ፍላጎት አናሳ ነው:: ልክ እንደ ወገናዊ ፍቅር ለራሳቸው የድርጅትና የፓርቲ አባላት በማድላት ሌሎቹ ተፎካካሪዎቻቸው የእነርሱን ጉድለት የሚያሳዩ መስተዋቶች እንደሆኑ ለመቁጠር ይቸገራሉ:: ለሚመጣው ምርጫ ዝግጅት የሚደረጉት ክርክሮች በተለያዩ ርዕዮቶች፣ የኢኮኖሚ፣ የአገር ግንባታ፣ የህዝብ አስተዳደር አማራጮችና የመሳሰሉት ላይ እንዲሆኑና የዴሞክራሲ ባህላችን እንዲያድግ በማድረግ በጓዶች ፍቅር ላይ የተመሠረቱ ድርጅቶች ትልቅ ድርሻ አላቸው:: ይህንን ሳይዘነጉ የአገራችንና የለውጡ ትልቁ የቤት ሥራ የሆነውን ሁላችንንም የሚያፋቅረን የጋራ እሳቤማካተት ይገባቸዋል:: የጓዶች ፍቅር ለወገናዊ ፍቅር ዕይታውን እንደሚያሰፋለት ሁሉ የጓዶች ፍቅር አድማሱን የሚያሰፋለት ፍቅር ያስፈልገዋል:: ይህን ፍቅር “እያየ የማያይ ፍቅር” ብዬዋለሁ::
 
እያየ የማያይ ፍቅር
 
ይህ ፍቅርሰዎች በፆታ፣ በቀለም፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በሃይማኖት፣ በርዕዮት፣ በሀብት፣ በእውቀት፣ በሥልጣንና በመሳሰሉት የተለያዩ እንደሆኑ በሚገባ ያውቃል:: ስለዚህ “ዓይናማ” ነው:: ነገር ግን ሰዎች ሁሉ ውድና ክቡር የሆነ የጋራ ነገር እንዳላቸው ስለሚረዳ ልዩነቻውን ወደ ጎን ትቶ ሁሉንም ይወዳል:: ስለዚህ “አውቆ ዓይነ ስውር ነው”::  እያየ የማያይ ፍቅር ከወገናዊና ከጓዶች ፍቅር የሚበልጠው ሰዎችን የለያያቸው ከእነርሱ ቁጥጥር ውጪ ያሉ ነገሮች መሆናቸውን አውቆ ለሰዎች ሁሉ ፍቅር በመለገሱና በብይኑ ሚዛናዊ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን የሚጠላው “ጥላቻን”ስለሆነ ነው::የሰዎች ውድና ክቡር የሆነው የጋራቸው ሚስጢር “ሰዎች” መሆናቸው ነውና እያየ የማያይ ፍቅር ሰዎችን አይጠላም:: ይህን ፍቅር ለማግኘት ሰው መሆን በቂ ነው::
 
ለምሳሌ ድሀንና ባለፀጋን እንውሰድ:- በሀብት እንጂ በሰውነት እኩል ናቸው:: ሁለቱም ራቁታቸውን ከእናታቸው ማሕፀን ይወጣሉ፤ ልዩነቱ የሚጠቀለሉበት ጨርቅ ነው:: ሁለቱም ይበላሉ፤ ልዩነቱ የምግቡ ዓይነት ነው:: ሁለቱም ይፀዳዳሉ፤ ልዩነቱ የመፀዳጃ ቦታው ነው:: ሁለቱም ይማራሉ፤ ልዩነቱ ትምህርት ቤቱ ነው:: ሁለቱም ይለምናሉ፤ ልዩነቱ የሚለምኑት ነገር ነው:: ሁለቱም ይለግሳሉ፤ ልዩነቱ የልግስናው መጠን ነው:: ሁለቱም ይሰርቃሉ፤ ልዩነቱ የሚሰርቁት አይነቱና ብዛቱ ነው:: ሁለቱም ይታመማሉ፤ ልዩነቱ የበሽታው ዓይነትና የሚታከሙበት ቦታ ነው:: ሁለቱም ይሞታሉ፤ ልዩነቱ መቃብሩና የቀባሪው ብዛት ነው:: ሰዎችን የሚለያቸው ከእውነተኛ ማንነታቸው ውጭ ያሉ ነገሮች ናቸው:: እውነተኛ ማንነታቸው አንድ ዓይነትና እኩል ነው:: ስለዚህ ሰውን ሁሉ ማክበርና መውደድ ራስስን ማክበርና መውደድ ነው:: በሌላ አባባል ሌላውን የሚንቅና የሚጠላ ራሱን የናቀና የሚጠላ ነው::እስቲ ወላጆቹን፣ ዘሩን፣ ፆታውን፣ ቀለሙን፣ ቋንቋውን፣ ባህሉን፣ ሃይማኖቱን፣ የሚኖርበትን አገር  ከካታሎግ ላይ መርጦ ወደዚች ዓለም የመጣ ማነው? ካልሆነስ ለምን ባልመረጠው ጉዳይ ይገፋል?
 
እኛ ኢትዮጵያውያን ዐይናችንና ማስተዋላችን ተደፍኖብን ካልሆነ በስተቀር ይህ ሊጠፋን አይችልም:: ምክንያቱም የምንከተላቸው ሃይማኖቶች ሁሉ የሚያስተምሩት ይህንን ነውና:: ይህንን ለማወቅ የሃይማኖት መሪ መሆን አያስፈልግም፤ የሚያዳምጥ ጆሮ፣ የሚያነብ ዐይንና የሚታዘዝ ልብ እንጂ::ከምንከተላቸው ሃይማኖቶች በስተጀርባ የሁላችንም ፈጣሪ አለና የፈጠረውን ሰው በመጥላታችን፣ በማፈናቀላችንና በመግደላችን ይጠይቀናል:: ይዘገይ ይሆናል እንጂ የዘራነውን ማጨዳችን አይቀርም:: ፍቅርን ዘርተን ከሆነ በረከትን፣ ጥላቻን ዘርተን ከሆነ እርግማንን እናጭዳለን:: ፈጣሪ አይዘበትበትም::
 
እያየ የማያይ ፍቅር ለለውጡ ብቻ ሳይሆን ለአገርም ምሰሶና ፈውስ ነው:: በኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች ጉዳይ እንደተራገበው ጎን ለጎን የሰዎች እኩልነትና ክቡርነት ተራግቦ ቢሆን ኖሮ ዛሬ መፈናቀል አይኖርም ነበር::እውነተኛ የብሔር ብሔረሰቦች መብት የሚከበረው በሰው ልጆች እኩልነት ከልብ በማመን ነው:: የፍቅርም የጥላቻም ምንጩ የሰው አዕምሮ ነውና መቀየር ያለበት የሰው አስተሳሰብ ነው:: የሰው ልጆችን መከባበርና መፋቀርበውጫዊ መንገድ ለማምጣት መሞከር ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም:: የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን ማክበር መፍትሔ ቢያመጣ ኖሮ ዛሬ ዓለም የሚያውቀን በፍቅራችን  እንጂ በተፈናቃዮች ብዛት አይሆንም ነበር:: “ከመቅረት ዘግይቶ ወደ ቀጠሮ ቦታ መድረስ ይሻላልና” ዘግይተንም ቢሆን አሁን ብንጀምረው የምንመኛትን አገር መገንባት እንችላለን:: ኔልሰን ማንዴላ “ሰዎች ጥላቻን መማር ከቻሉ ፍቅርንም መማር ይችላሉ”እንዳሉት በአገራችን ያሉ የሃይማኖት መሪዎችና ተከታዮቻቸው፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ የወረዳና የክልል መስተዳደሮች፣ ትምህርት ቤቶች፣ መገናኛ ብዙሃን፣ የፓለቲካ መሪዎች፣ ልሂቃንና አክቲቪስቶች በፍቅር ዙርያ በሚጠበቅባቸው ልክ ቢንቀሳቀሱ በሰው አስተሳሰብ ውስጥ ብዙ ለውጥ ያመጣሉ::
 
ሰዎችን ማክበርና መውደድ ስንጀምር የምንሠራው ሁሉ ጥራት ይኖረዋል:: ሌሎች የሚጠቀሙበትቢሆንምእንኳ ለራሳችን እንደሆነ ስለምናስብ መልካም ነገርን ሠርተን እናቀርባለን:: በትንሿ ዱባይ የአውቶብስ መጠበቂያ ስፍራዎች ያማሩና የአየር ማቀዝቀዣ ያላቸው ናቸው:: የዚህ ተጠቃሚዎች እነማን ናቸው? ብንል፦ መኪና ወይም የሞተር ቢስክሌት ገዝተው መንዳት የማይችሉ፣ በታክሲ ተሳፍረው ለመሄድ በቂ ገንዘብ የሌላቸው፣ ቤተሰቦቻቸውንና አገራቸውን ትተው ያልፍልናል ብለው የመጡ ድሆች ናቸው:: የዱባይ የመንገዶችና ትራንስፖርት ባለሥልጣኖች ይህን ያደረጉት ከተማዋን ለማስዋብ ብቻ ሳይሆን እነዚህ ድሆች እንደ ባለፀጋዎቹ ሰዎች መሆናቸውን ስለተረዱ ነው:: 
 
ሰዎችን ስንወድ እውነተኛ የአገር መውደድ ይኖረናል:: በኢትዮጵያዊነት ላይ ውዝግብ ሊኖር ይችላል፤ በኢትዮጵያ ላይ ግን ሊኖር አይገባም፤ አይችልምም:: ምክንያቱም ኢትዮጵያ መላው የዓለም ማኅበረሰብ የሚያውቃት፣ በዓለም ካርታ ላይ ድንበሮቿ ተከልሎ የምትታየው ያቺ ምድር ናት:: ይህንን ለመረዳት የተማረና የተመራመረ መሆን አይጠይቅም:: በዚች አገር የምንኖር ወይም ዜግነት ያለን ሁሉ ኢትዮጵያውያን ነን:: እኛም ሆንን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያምነው ኢትዮጵያውያን ሁሉ በዚች ግዛታቸው ውስጥ ያለምንም ገደብ መኖር እንደሚችሉ ነው:: አለመታደል ሆኖ ዛሬ በየትኛውም ቦታ እንደፈለግን ለመሄድ፣ ሳንሸማቀቅ ለመኖር፣ ሠርተን ሀብት ለማፍራት አንችልም:: አውቀንም ይሁን ባለማወቅ ይህ ድርጊታችን መሠረታዊ የሆነውን የሰው ልጅን መብት መጋፋት ነው፤ በህግሲያስጠይቅ ባልሰማም በፈጣሪ ዘንድ ግን ያስጠይቃል:: ሰውን ስናከብርና ስንወድ ኢትዮጵያውያንን እንወዳለን፤ ኢትዮጵያውያንን ስንወድ ኢትዮጵያን እንወዳለን:: ያኔ በአንድ ልብ ለኢትዮጵያ እንሰራለን:: በበጎ ሐሳብ የተጀመረው ለውጥም ስኬታማ ይሆናል::
 
ማጠቃለያ
 
ፍቅር መልካም ነው:: ፍቅር ጥላቻን ከወለደ ግን አውዳሚ ነው:: ስለዚህ የፍቅርን አሉታዊ ተጽዕኖ ከልባችንና ከመካከላችን ማውጣት ያስፈልጋል:: በፍቅር የተሸፈነን ጥላቻ ከውስጥ ፈልቅቆ ለማውጣት እራሳችንን መመርመር ይጠይቃል:: ሌላውን በመጥላት የተጀመረ ፍቅር ዘላቂ አይሆንም:: ያ የጋራ “ጠላት” በሽንፈትም ይሁን በፈቃደኛነት ሲወገድ ጥሉና ጥላቻው በፍቅረኞች መካከል ይሆናል:: የለውጡ መሪዎች ከተለያየ ማኅበረሰብና ድርጅት የተውጣጡ ናቸው:: ያፋቀራቸው ጥላቻ ከሆነ ይዋል ይደር እንጂ ለውጡ ይጨናገፋል:: ስለዚህ በተደጋጋሚ በመገናኘት ልባቸውንና አቅጣጫቸውን  ማስተካከል ይገባቸዋል::
 
በፍቅር ተደምረናል የምንልሁሉ ፍቅራችን በጥላቻ ተለውሶ ከሆነ ለምንመኘው እኩልነት ዴሞክራሲና ብልጽግና መሰናክል ስለሚሆን ራሳችንን እናስተካክል:: ለውጡ የሚሳካው በቂምና በጥላቻ ሳይሆን በይቅርታና በፍቅር ብቻ ነው:: ለታማኝ በየነ ያለን ፍቅር ለጃዋር መሐመድ ጥላቻን ከወለደ፣ ለጃዋር ያለን ፍቅር ለእስክንድር ነጋ ጥላቻን ካለበሰን ፍቅራችን “በማር የተለወሰ ኮሶ” ነው:: እነዚህ ለአብነት ያነሳኋቸው ግለሰቦች የተለያየ እሳቤ ቢኖራቸውም ሰዎች ናቸው:: እንደነሱ በግንባር ቀደምትነት የተሰለፉ ግለሰቦች፣ የፓለቲካ ድርጅት አመራሮች፣ መገናኛ ብዙሃን፣ አክቲቪስቶች ፣ ልሂቃን፣ የፌደራል መንግሥት፣ የወረዳና የክልል መስተዳደሮች ባለሥልጣናት ጥላቻ ቢያስተምሩ ምግባራቸውንና ትምህርታቸውን ሳንከተል እነርሱን ግን መውደዳችንን እንቀጥል፤ ሰዎች ናቸውና!ለእኩይ ትምህርታቸውና ምግባራቸው ግን ከፈጣሪም ከህግም ብይን ያገኛሉ::
 
ማንኛውም ህዝብ በሌላው ህዝብ ላይ ዝም ብሎ አይነሳም፤ አይጠላምም:: የሚያነሳሱትና ጥላቻን የሚዘሩት የራሳቸው ዓላማ ያላቸው ጥቂት ሰዎች ናቸው:: የጀርመን ህዝብ በዓለም ህዝብ ላይ አልተነሳም፤ ያነሳሱት ናዚዎች ናቸው:: ከናዚዎችም እውነተኛውን ምክንያት የሚያውቁት ከላይ ሆነው የናዚ ፓርቲን የሚመሩት ነበሩ:: ለዓላማቸው ማስፈጸሚያ የተጠቀሙት በአገር ፍቅር የተለወሰ ጥላቻ ነበረ:: ጥላቻ ተከታይ የሚያገኘው በጎና አጓጊ ተስፋዎችን በመስጠት ነው:: ነገር ግን የገባውን የተስፋ ቃል መፈጸም አይችልም፤ አቅምም የለውም:: ምክንያቱም በጎና አጓጊ ነገሮችን መገንባትና ማምጣት የሚቻለው በፍቅር ስለሆነ ነው:: የጥላቻ ተስፋዎች ከእርሱ ባህርይ ጋር ስለሚጋጩ ወደ ህልውና አይመጡም:: በአገራችንም ጥላቻን በወገናዊ ፍቅር ጠቅልለው የሚያጎርሱ ሰዎች ለሐሳባቸውና ምኞታቸው ማስፈፀሚያ እንዲሆን ለሚጠቀሙበት ህዝብ የሚሰጡት ተስፋ “ምድራዊ ገነት”ን ነው:: የዚች “ምድራዊ ገነት” ተቋዳሾች ጥቂት ግለሰቦች ሊሆኑ ቢችሉም በእርግጠኛነት ግን  ህዝቡ አይደለም:: እስቲ ወንድሞቹንና እህቶቹን አፈናቅሎና ገድሎ ኑሮው የተቀየረ ማኅበረሰብና ህዝብ፤ ኢኮኖሚው ያደገ ክልልና አገር የትኛው ነው?
 
የመጀመሪያው ወርቃማው ቃል ግን እንዲህ ይላል:-
“ለእናንተ እንዲደረግላችሁ የምትፈልጉትን ሁሉ ለሌሎችም አድርጉ”፤ 
ሁለተኛው ደግሞ:-
“በእናንተ ላይ እንዲደረግባችሁ የማትፈልጉትን ሁሉ በሌሎችም ላይ አታድርጉ”:: 
 
ጥላቻን የሚጠላ ፍቅር ያሸንፋል፤ ሁልጊዜም ተፈላጊ ነው::የሰላም ሚኒስቴር ሰላም ከመጣ በኋላ በሌላ ይተካል፤ የእርቅ ኮሚሽንም እርቅ ከወረደ በኋላ ይፈርሳል፤ የማንነትና የወሰን ኮሚሽንም ተልዕኮውን ከፈጸመ በኋላ ይበተናል፤ ሰዎችን ሁሉ የሚወድና ጥላቻን የሚጠላ ፍቅር ግን ሁልጊዜም ይኖራል::
 ​
0 Comments



Leave a Reply.

    Amharic

    Archives

    October 2020
    August 2020
    April 2020
    November 2019
    September 2019
    July 2019
    April 2019
    November 2018
    October 2018
    September 2018
    August 2018
    July 2018

    Categories

    All
    Current Affairs
    Sport
    The God Factor Forum

    RSS Feed

Copyright © 1999 - 2019
  • Home
  • Forum
  • Amharic
  • English
  • Zelalem