ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
ባለፉት 50 ዓመታት ብዙ አሳለፍን። ኢትዮጵያ ወንድማማችነት አልቸገራትም። የትኛውም ብሔር ስልጣን ላይ ቢወጣ በሺህ የሚቆጠር ልኂቃን ባለጊዜ ነኝ ይላል እንጂ፥ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሁሉም ገበሬ ያለ ልዩነት አንድ ላይ መከራ ያስተናግዳል። በሌላ በኩል ልኂቃን ግን ኢትዮጵያ ትፈርሳለች፥ አትፈርስም እያሉ በመነታረክ እርስ በርስ ይቀዋወማሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ በልኂቃን ታግቶ ፍዳው ሲበዛበት፥ ያምፅና አብዮት ያስነሳል። ልኂቃኑም ይፈራረቃሉ። ግን ያው ሕዝብ በሌላ ባለጊዜ ልኂቃን ታግቶ ፍዳውን ይቀጥላል። መቼም ሕዝብ ቤተመንግስት አይገባ ነገር። ለዚህ ሕዝብ ተመልካች አለ ለማለት ያስቸግራል። ተስፋ ያልተቆረጠበት እግዚአብሔር ፀሎት ይቀርብለታል። የፈጣሪ መልስ እንዲመጣ መውጫ መንገዱ ሕዝብ ራሱን መልስ ማድረግ እንዳለበት ገና አልታወቀም። ኢትዮጵያ በዲሞክራሲ ምርጫ መሪዋን ከመምረጥ በፊት፤ ኢትዮጵያ በሕዝብ መወለድ አለባት። ሕዝብ በመምከር ሕገ ሕዝብን፥ ሕገ መንግስትን፥ ማንነትንና ሕልውናውን፤ በጠቅላላ ራሱን መልስ አድርጎ ኢትዮጵያን መውለድ አለበት። ከዚያ በሁዋላ ነው፥ ዲሞክራሲና ምርጫ ውጤታማ የሚሆኑት። ይህ ደግሞ እስካሁን ያልሆነው፥ ፖለቲካውን የሚዘውሩት ልኂቃን መግዛትን እንጂ አዋላጅ መሆንን እንደ አማራጭ ስለማያዩት ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ በልኂቃን እስከታገተ ድረስ፥ ሕዝብ የራሱን ዕድል ራሱ ለመወሰን አይችልም። በመጀመሪያ ኢትዮጵያ እንድትወለድ ሕዝብን ከመታገት ነፃ የሚያወጣ አዋላጅ መሪ ያስፈልጋል። ያ አዋላጅ ደግሞ የአባትነትን ሥፍራ ወስዶ ራሱን ዘወር የሚያደርግ መሆን አለበት። ገዥነት ለአጭር ጊዜ ሲሆን መጨረሻውም ክስረት እየሆነ ዛሬ ደረስን። አዋላጅነት ግን ለዘላለም በመልካም ሲታወስ የሚያስኖር ነው። ይህን አዲስ ታሪካዊ መንገድ የሚመረጥበት ጊዜ ሲመጣልን የእፎይታ ዘመን ይሆናል። የተሰጠውን ስልጣን መልሶ ለሕዝብ በመሰዋት የአዋላጅነት ጥሪን የሚመርጥ ፈር ቀዳጅና ፋና ወጊ ያስፈልጋል። ራሱን ከምርጫ በማግለል የሚገኘውን የአባትነት ክብር መምረጥን ይጠይቃል። ራሱን እንደ ብቸኛ ቁልፍ አድርጎ በስልጣን ከመኖር ይልቅ፥ ራሱን ክዶ የኢትዮጵያ መወለድን ራዕዩ የሚያደርግ መሪ አዋቂ ነው። ሕዝብ ይህን ለየት ያለ የላይኛውን መንገድ ለመሄድ የቆረጠ መሪ ዕውን እንዲሆን ልቡን በዚህ አዲስ መንገድ ላይ ማድረግ አለበት። የምንጠብቀውንና የምንጠይቀውን ያንኑ እናገኝ ዘንድ የሚያዋጣንን ለይተን እንወቅ። የአዋላጅነት ክብር ይበቃኛል ብሎ ከምርጫ ራሱን ማግለል የሚችል ሰው ለሕዝብ ያለውን ታላቅ ከበሬታ ያሳያል። በተጨማሪም ስልጣኑን በእጁ ላስገባለት አምላክ እንደ ልቡ የሆነ ታማኝ አገልጋይ መሆኑን ያሳያል። እግዚአብሔርም የሕዝብን እንባ ለማበስ እንዲህ ያለው መሪ ፍቃዱን እንዲያስገዛለት እጅግ ይሻል። ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ሲባል፥ የሚያመለክተው ሕዝብን ነው። የኢትዮጵያን ታሪክ ከእስራኤል ጋር አናደባልቀው። የእስራኤል ጥሪ በአንድ ሰው ያውም በአብርሃም ጀማሪነት፥ በመጨረሻም በኢየሱስ ክርስቶስ የተከናወነ፥ ለዓለም ሁሉ መዳንን እንዲያመጣ የተደረገ ነው። በዚህም መሠረት አብዛኛውን የእስራኤል ታሪክ በግለሰቦች አዳኝነት የተቃኘ ነው። ሙሴ፥ ኢያሱ፥ ዳዊት እያልን ብንዘረዝር፥ ግለሰቦች አዳኝ ሆነው የተገለጡበት ነው። የኢትዮጵያ ጥሪ ከግለሰብ የተፋታ፥ በሕዝብ ላይ የተመሰረተ ነው። ሕዝብ የኢትዮጵያን መሠረት እንዲጥል፥ ስልጣኑን በመሰዋት አዋላጅ ለመሆን የተዘጋጀ መሪ መኖር አለበት። ልኂቃን አየሩን የሞሉት በመግዛት ላይ ያጠነጠነ አስተሳስብ በማራገብ ነው። የመግዛት አስተሳሰብ በልኂቃን መካከል ያመጣው አለመግባባት፥ ይህን ደግ ሕዝብ ደም እያቃባ ዛሬ ላይ ደርሰናል። ከዚህ አዙሪት ለመውጣት ሕዝብ ኢትዮጵያን የመውለድ አላፊነትን በእጁ ማስገባት አለበት። ለዚያ ደግሞ ሕዝብ አሁን በስልጣን ላይ ያለውንም መሪ ሆነ፥ ወይም ወደፊት ሊመጣ ያለው አዲስ መሪ አዋላጅ እንዲሆን መጠየቅ መጀመር አለበት። በመግዛት አስተሳሰብ ኢትዮጵያ በሁለት ጎራ ተከፍላ ጥል ላይ ትገኛለች። አንደኛው ጎራ ያለው መሪ ይግዛን ብሎ የሚያምን ሲሆን፥ ሌላኛው ወገን ደግሞ አዲስ የሚገዛን መሪ እንዲመጣ የሚታገል ነው። ግን ልብ ላለ ሰው፥ የሚያስፈልገን የሚገዛን መሪ ሳይሆን፥ በእጁ የገባውን ወይም የሚገባውን የራሱን ስልጣን ሰውቶ፥ በአዋላጅነት ሕዝብን ከእገታ ነፃ የሚያደርግ ነው። ያኔ በዚህ በተገኘው እውነተኛ ነፃነት፤ ሕዝብ ኢትዮጵያን እንዲወልድ ተአማኒነት ይጋርደዋል። አዋላጁም ባለ ስልጣን ከመሆን ይልቅ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ አባት ለመባል ይታደላል። አዋላጅ ማለት ለሚወለደው ምክንያት ሆኖ ዘወር የሚል ነው። ከስልጣን ዘወር በማለቱም በሕዝብ ልብ ውስጥ ስሙ በፍቅር የሚፃፍለት ሆኖ ይታወሳል። በእግዚአብሔርም ፊት ታማኝና ትሁት አገልጋይ ሆኖ በመገለጥ ክብርን ለፈጣሪ ለማምጣት ዕድሉን ይጠቀምበታል። ሁላችንም የሚሰራልንን መፍትኤ ትተን ሌላ መፍትኤ የምንፈልገው፥ እውነተኛው መፍትኤ ይቻላል ብለን ስለማናምን ነው። ለምድራችን መልሱን ሁሉም ያውቃል፥ ግን ያ መልስ መስዋዕትነትን ስለሚጠይቅ፥ ለዚህም ማንም ራሱን ሊሰጥ ስለማይፈልግ፥ ጭራሽ ማንሳት አንፈልግም። ታዲያ የሚሆን የሚሆን የሚመስለንን ስናነሳና ስንጥል በአለበት እርገጥ ሆኖብናል። ግን ለምን ፈራን? እንደ ሕዝብ ትልቅ ነገር ለማሰብ እግዚአብሔርን ለምን አንታመነውም? ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች። መዝሙረ ዳዊት 68፡31 www.myEthiopia.com |
ጤና ይስጥልኝ!ዶ/ር ዘላለም እሸቴ Archives
June 2024
Categories |