ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
ባለፉት 50 ዓመታት ብዙ አሳለፍን። ኢትዮጵያ ወንድማማችነት አልቸገራትም። የትኛውም ብሔር ስልጣን ላይ ቢወጣ በሺህ የሚቆጠር ልኂቃን ባለጊዜ ነኝ ይላል እንጂ፥ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሁሉም ገበሬ ያለ ልዩነት አንድ ላይ መከራ ያስተናግዳል። በሌላ በኩል ልኂቃን ግን ኢትዮጵያ ትፈርሳለች፥ አትፈርስም እያሉ በመነታረክ እርስ በርስ ይቀዋወማሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ በልኂቃን ታግቶ ፍዳው ሲበዛበት፥ ያምፅና አብዮት ያስነሳል። ልኂቃኑም ይፈራረቃሉ። ግን ያው ሕዝብ በሌላ ባለጊዜ ልኂቃን ታግቶ ፍዳውን ይቀጥላል። መቼም ሕዝብ ቤተመንግስት አይገባ ነገር። ለዚህ ሕዝብ ተመልካች አለ ለማለት ያስቸግራል። ተስፋ ያልተቆረጠበት እግዚአብሔር ፀሎት ይቀርብለታል። የፈጣሪ መልስ እንዲመጣ መውጫ መንገዱ ሕዝብ ራሱን መልስ ማድረግ እንዳለበት ገና አልታወቀም። ኢትዮጵያ በዲሞክራሲ ምርጫ መሪዋን ከመምረጥ በፊት፤ ኢትዮጵያ በሕዝብ መወለድ አለባት። ሕዝብ በመምከር ሕገ ሕዝብን፥ ሕገ መንግስትን፥ ማንነትንና ሕልውናውን፤ በጠቅላላ ራሱን መልስ አድርጎ ኢትዮጵያን መውለድ አለበት። ከዚያ በሁዋላ ነው፥ ዲሞክራሲና ምርጫ ውጤታማ የሚሆኑት። ይህ ደግሞ እስካሁን ያልሆነው፥ ፖለቲካውን የሚዘውሩት ልኂቃን መግዛትን እንጂ አዋላጅ መሆንን እንደ አማራጭ ስለማያዩት ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ በልኂቃን እስከታገተ ድረስ፥ ሕዝብ የራሱን ዕድል ራሱ ለመወሰን አይችልም። በመጀመሪያ ኢትዮጵያ እንድትወለድ ሕዝብን ከመታገት ነፃ የሚያወጣ አዋላጅ መሪ ያስፈልጋል። ያ አዋላጅ ደግሞ የአባትነትን ሥፍራ ወስዶ ራሱን ዘወር የሚያደርግ መሆን አለበት። ገዥነት ለአጭር ጊዜ ሲሆን መጨረሻውም ክስረት እየሆነ ዛሬ ደረስን። አዋላጅነት ግን ለዘላለም በመልካም ሲታወስ የሚያስኖር ነው። ይህን አዲስ ታሪካዊ መንገድ የሚመረጥበት ጊዜ ሲመጣልን የእፎይታ ዘመን ይሆናል። የተሰጠውን ስልጣን መልሶ ለሕዝብ በመሰዋት የአዋላጅነት ጥሪን የሚመርጥ ፈር ቀዳጅና ፋና ወጊ ያስፈልጋል። ራሱን ከምርጫ በማግለል የሚገኘውን የአባትነት ክብር መምረጥን ይጠይቃል። ራሱን እንደ ብቸኛ ቁልፍ አድርጎ በስልጣን ከመኖር ይልቅ፥ ራሱን ክዶ የኢትዮጵያ መወለድን ራዕዩ የሚያደርግ መሪ አዋቂ ነው። ሕዝብ ይህን ለየት ያለ የላይኛውን መንገድ ለመሄድ የቆረጠ መሪ ዕውን እንዲሆን ልቡን በዚህ አዲስ መንገድ ላይ ማድረግ አለበት። የምንጠብቀውንና የምንጠይቀውን ያንኑ እናገኝ ዘንድ የሚያዋጣንን ለይተን እንወቅ። የአዋላጅነት ክብር ይበቃኛል ብሎ ከምርጫ ራሱን ማግለል የሚችል ሰው ለሕዝብ ያለውን ታላቅ ከበሬታ ያሳያል። በተጨማሪም ስልጣኑን በእጁ ላስገባለት አምላክ እንደ ልቡ የሆነ ታማኝ አገልጋይ መሆኑን ያሳያል። እግዚአብሔርም የሕዝብን እንባ ለማበስ እንዲህ ያለው መሪ ፍቃዱን እንዲያስገዛለት እጅግ ይሻል። ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ሲባል፥ የሚያመለክተው ሕዝብን ነው። የኢትዮጵያን ታሪክ ከእስራኤል ጋር አናደባልቀው። የእስራኤል ጥሪ በአንድ ሰው ያውም በአብርሃም ጀማሪነት፥ በመጨረሻም በኢየሱስ ክርስቶስ የተከናወነ፥ ለዓለም ሁሉ መዳንን እንዲያመጣ የተደረገ ነው። በዚህም መሠረት አብዛኛውን የእስራኤል ታሪክ በግለሰቦች አዳኝነት የተቃኘ ነው። ሙሴ፥ ኢያሱ፥ ዳዊት እያልን ብንዘረዝር፥ ግለሰቦች አዳኝ ሆነው የተገለጡበት ነው። የኢትዮጵያ ጥሪ ከግለሰብ የተፋታ፥ በሕዝብ ላይ የተመሰረተ ነው። ሕዝብ የኢትዮጵያን መሠረት እንዲጥል፥ ስልጣኑን በመሰዋት አዋላጅ ለመሆን የተዘጋጀ መሪ መኖር አለበት። ልኂቃን አየሩን የሞሉት በመግዛት ላይ ያጠነጠነ አስተሳስብ በማራገብ ነው። የመግዛት አስተሳሰብ በልኂቃን መካከል ያመጣው አለመግባባት፥ ይህን ደግ ሕዝብ ደም እያቃባ ዛሬ ላይ ደርሰናል። ከዚህ አዙሪት ለመውጣት ሕዝብ ኢትዮጵያን የመውለድ አላፊነትን በእጁ ማስገባት አለበት። ለዚያ ደግሞ ሕዝብ አሁን በስልጣን ላይ ያለውንም መሪ ሆነ፥ ወይም ወደፊት ሊመጣ ያለው አዲስ መሪ አዋላጅ እንዲሆን መጠየቅ መጀመር አለበት። በመግዛት አስተሳሰብ ኢትዮጵያ በሁለት ጎራ ተከፍላ ጥል ላይ ትገኛለች። አንደኛው ጎራ ያለው መሪ ይግዛን ብሎ የሚያምን ሲሆን፥ ሌላኛው ወገን ደግሞ አዲስ የሚገዛን መሪ እንዲመጣ የሚታገል ነው። ግን ልብ ላለ ሰው፥ የሚያስፈልገን የሚገዛን መሪ ሳይሆን፥ በእጁ የገባውን ወይም የሚገባውን የራሱን ስልጣን ሰውቶ፥ በአዋላጅነት ሕዝብን ከእገታ ነፃ የሚያደርግ ነው። ያኔ በዚህ በተገኘው እውነተኛ ነፃነት፤ ሕዝብ ኢትዮጵያን እንዲወልድ ተአማኒነት ይጋርደዋል። አዋላጁም ባለ ስልጣን ከመሆን ይልቅ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ አባት ለመባል ይታደላል። አዋላጅ ማለት ለሚወለደው ምክንያት ሆኖ ዘወር የሚል ነው። ከስልጣን ዘወር በማለቱም በሕዝብ ልብ ውስጥ ስሙ በፍቅር የሚፃፍለት ሆኖ ይታወሳል። በእግዚአብሔርም ፊት ታማኝና ትሁት አገልጋይ ሆኖ በመገለጥ ክብርን ለፈጣሪ ለማምጣት ዕድሉን ይጠቀምበታል። ሁላችንም የሚሰራልንን መፍትኤ ትተን ሌላ መፍትኤ የምንፈልገው፥ እውነተኛው መፍትኤ ይቻላል ብለን ስለማናምን ነው። ለምድራችን መልሱን ሁሉም ያውቃል፥ ግን ያ መልስ መስዋዕትነትን ስለሚጠይቅ፥ ለዚህም ማንም ራሱን ሊሰጥ ስለማይፈልግ፥ ጭራሽ ማንሳት አንፈልግም። ታዲያ የሚሆን የሚሆን የሚመስለንን ስናነሳና ስንጥል በአለበት እርገጥ ሆኖብናል። ግን ለምን ፈራን? እንደ ሕዝብ ትልቅ ነገር ለማሰብ እግዚአብሔርን ለምን አንታመነውም? ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች። መዝሙረ ዳዊት 68፡31 www.myEthiopia.com ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
ግልፅ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ሕዝበ ቤተሰብ። በደወል 1 ዘ ኢትዮጵያ በሚድን በሽታ ተይዛ ግን በሽታው እየገደላት ያለች ሀገር ኢትዮጵያን አየን። በደወል 2 ዘ ኢትዮጵያ፥ ለዚህ በሽታ ያልተጠቀምንበትን ቀዳሚው ፍቱን መድኃኒት ምን እንደሆነ ተመለከትን። አሁን በደወል 3 ዘ ኢትዮጵያ መድኃኒት መስሎን የምንወስደው ዘረኝነት ገዳይ መርዝ እንደሆነ እናያለን። ሰው የሚድን በሽታውን ለማሻል የሚያድን መድኃኒት ይወስዳል እንጂ ጭራሽ ለሞት የሚያጋልጠውን መርዝ በመድኃኒት ስም አይወስድም። ኢትዮጵያ ግን የብሔር ብሔረሰብን እኩልነት ለማምጣት ዘረኝነትን እንደ መድኃኒት እየወሰደች የማያቆም የስቃይ ድራማና ምስቅልቅል ያለ ጉዞ ተያያዝን። የኢትዮጵያ ሕልውናም ቦግ ድርግም እያለ፥ በቁልቁለት ጉዞ ፀሐይ እስክትጠልቅባት ድረስ የሚሄደው ለዚህ ነው። መፍትሄው አንድ ነገር ነው። የዐሳብ ልዕልና መውጫ መንገዳችን ነው። የዐሳብ ልዕልና ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን፥ ሲያሸንፍ ዘለቄታ ያለው መፍትሄ ጭምር ሰጥቶ ነው። ለመግባባት አንድ መሠረት መኖሩ ወሳኝ ነው። ኢትዮጵያ በብዝሀነት የበለፀገች ናት። የሁሉም ውበት ደምቆ እንዲወጣ፥ የሁሉም ስብዕና እና እሴቶች በሙሉ በእኩልነት እንዲታዩ፥ ከዚህ አልፎ ልዩነቶቹ እርስ በርስ እየተመጋገቡ እንዲጎለብቱና በዘለቄታ እንዲዘልቁ ከተፈለገ፥ ሁላችንም አንድ መሠረት ሊኖረን ያስፈልጋል። ያም መሠረት አብሮነት ይባላል። ግን ዘረኝነት አብሮነታችንን እየገዘገዘ ብትንትናችን እንዲወጣ መንገድ ይጠርጋል። ያኔ ባለጊዜና ያሸነፈ የሚመስለው ተረኛ፥ ራሱን መሠረት ለማድረግ ይሞክራል። በዚህ ሂደት ሁሉም ይከስራል። ይህ እንዳይሆን ያልታሰበውን ማሰብ መጀመር አለብን። ያልታሰበውን ማስብ፦ የዐሳብ ልዕልና ያልታሰበውን ለማሰብና የዐሳብ ልዕልናን ለመጨበጥ፥ እኛ ራሳችንን የምናይበትን ዕይታና ሌሎችን የምናይበትን ዕይታ መቀየር አለብን። ምክንያቱም በተለመደው ዕይታ ዘረኛው ሁልጊዜ ሌላኛው ነው እንጂ እኛ አይደለንም። ለአብሮነት መሠረት ደግሞ እንቅፋት የሆነው ዘረኝነት ነው። ቋንቋችን የሚደባለቀው እዚህ ላይ ነው። አንዱ ከሳሽ፥ ሌላኛው ተከሳሽ እየሆንን ስለ ቁምነገር መነጋገር አንችልም። ነፃ የሚያወጣን ሁላችንም ወርደን ታች ዝቅ ብለን እግዚአብሔር እኛን የሚያይበትን ዕይታ ማየት ነው። ያኔ ሁላችንም ዘረኛ እንደሆንን ይታየናል። ዘረኝነት በተፈጥሮ ያለ ነገር ነው። ከዘረኝነት የምንወጣው በፍቃዳችን ነው። ያንንም በአሸናፊነት የምንወጣው፥ ሁላችንም አብረን ዘረኞች እንደሆንን ሁሉ፥ ሁላችንም ከዚያ ተላቀን ሰው መሆንን ስንፈቅድ ነው። አንዱ በብሔሩ ዘረኛ ሲሆን፥ ሌላኛው በዜግነቱ ዘረኛ ይሆናል። አንዱ ብሔሩን ሲያስቀድም፥ ሌላኛው ዜግነቱን ያስቀድማል። አንዱ የብሔር ዘረኛ የራሱን ብሔር ለብቻው ሊያገን ሲፈልግ፥ ለኢትዮጵያ አብሮነት መሠረት ውጋት ይሆናል። እንደዚሁም የዜግነት ዘረኛ ኢትዮጵያን ለብቻዋ እንድትገን ሲፈልግ፥ በጨለማ ላለ ጥቁር አፍሪካ ሕዝብ አንድነት ውጋት ይሆናል። አንድ ብሔር እንዲሰለጥን የሚፈልግ ዘረኛና፥ አንድ ኢትዮጵያን ለማግነን የሚፈልግ ዘረኛ፥ አንድ አፍሪካን ሕልም አድርጎ የሚያስቀር ነው። ይህን በማድረግ አፍሪካን ብቻ ሳይሆን፥ ዓለምን ያጨልማል። በኢትዮጵያ ዘረኝነት እንደ መድኃኒት መወሰድ የተጀመረው በጭቆና ተሳቦ ነው። ጨቋኝ ሁልጊዜ ሕዝብ ሳይሆን የተረኛ መንግስት ውጤት ነው። የጨቋኝ እናት ደግሞ በጥቁር ሕዝብ ላይ የተፈፀመው ጭቆና ነው። ኢትዮጵያ በአድዋ የነፃነት ምልክት የሆነችውና ለፓን አፍሪካ መነሻ ያደረጋት፥ እንድትመፃደቅበት ሳይሆን፥ ለእውነተኛው ጭቆና መልስ እንድትሰጥ ነው። ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦችን ጭቆና ለመፍታት እስካልተነሳች ድረስ፥ ራሷን በራሷ ተጠላልፋ የብዙዎች እንቆቅልሽ መሆን ይሆናል እድል ፈንታዋ። ያለን ዘረኝነት የብሔር ዘረኝነት እና የዜግነት ዘረኝነት ነው። እዚህ ላይ መሀል ሰፋሪ የለም። መሀል ነኝ ብሎ የብሔር ዘረኝነትን ጠባብ የሚልና የዜግነት ዘረኝነትን አሕዳዊ የሚል ፖለቲካዊ ብልጣብልጥነት ነው። አሁን ሁላችንም ብንፋቅ ወይ የብሔር ዘረኛ ነን፤ አለበለዚያ ደግሞ የዜግነት ዘረኛ ነን። እውነተኛይቷ ኢትዮጵያ የምትገለጠው ልጆቿ የተፈጥሮ ዘረኝነትን በፍቃዳቸው ለመላቀቅ የሚያስችላቸውን ሃይል እንዲላበሱ የኢትዮጵያን ተልዕኮ ሲያውቁ ነው። በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ልጆች ከዘረኝነት ወጥተን ሰው በመሆናችን፥ ለጥቁር ሕዝብ ጭቆና መልስ መሆን ተልዕኳችን መሆኑን እንወቅ። ችግራችን የሚፈታው ከራሳችን በላይ ማሰብ ስንጀምር ነው። በዓለም እስካሁን ካልታዩት የተሻለ ሥርዓት ሊያመጡ የሚችሉ አቅም ያላቸው ልጆች እናታችን ኢትዮጵያ አላት። ከዘረኝነት የምንወጣው በፍቃዳችን እንጂ በተፈጥሯችን አይደለም። የራስን ባህል ቋንቋ እሴት ማዳበር ሰውዋዊነትና ኢትዮጵያዊነት ነው። ነገር ግን የብሔር ዘረኝነት ራስን መንከባከብ ላይ ብቻ አያቆምም። ራስን በሌላው ላይ ጭኖ መግነን ነው የሚፈልገው። ጨቋኝነት ከባለጉልበታምነት (ተረኛ ባለጊዜነት) የሚመነጭ ነው። ራስን በትዕቢት ከሁሉ የበላይ ነኝ የሚል መንፈስ የእኩልነት ጠላት ነው። የብሔር ዘረኝነት የብሔርን ክብር የሚያዋርድ ነው። ብሔር ክብሩና ውበቱ የሚገለጠው በእውነተኛ ኢትዮጵያዊ አብሮነት ውስጥ ነው። የአድዋ ታሪካችን ፈጣሪ ለጥቁር ሕዝብ ፋና ወጊ እንድንሆን ዕድል የሰጠን መሆኑን የሚያሳይ ነው። ለራስ ብቻ ከመኖር ለሌሎች ለመኖር እንድንፈልግ ነው። ኢትዮጵያ ትልቅ እንጀራ እንዲወጣላት ከፈለግን ማወቅ ያለብን ነገር አለ። ያም ለአፍሪካ እንጀራ እንዲወጣላት ኢትዮጵያ እርሾ እንደሆነች ነው። ኢትዮጵያ ከእኛ በላይ ትልቅ ካልሆነች፥ በእኛው ልክ ብቻ ከሰፋናት፥ እሺ ብላ አትሰፋልንም። ይልቁንም ትበጣጠስብናለች። ሰው መሆን ማለት ምን ማለት ነው? ሰው ሰውን ገዥና ለሰው ተገዥ ሆኖ እንዲኖር በፈጣሪ አልተፈጠረም። ሰው ተፈጥሮን እንዲገዛ እንጂ። ሰው ግን ተባብሮና ተዋዶ ምድርን እየገዛ የምድርን በረከት ከመብላት ይልቅ፥ አንዱ ሌላውን ለመግዛት እየሮጠ እርስ በርስ መበላላትን መረጠ። ሰው መሆን ሲመነዘር በዜግነት የሚወሰን ሳይሆን በአህጉራችን ጥቁር ሕዝብነት ነው የሚታየው። ያኔ ነጭ ጥቁር ሳንል ለሰው ፍጡር ሁሉ ፈውስ ምክንያት እንሆናለን። አፍሪካ ስትድን ያኔ ሁላችንም እንድናለን። ይህንን መንገድ ካልመረጥን ግን በተናጥል እያንዳንዳችን በጠላት እንመታለን። አብረን ካልቆምን ለየብቻችን የዓለምን ተፅዕኖ አሸንፈን ከጨለማ አህጉርነት ወደ ብርሃን አህጉርነት አንሻገርም። ኢትዮጵያ ደግሞ ለዚህ በመሪነት እንድትቀደም በታሪክ አጋጣሚ ይሁን በፈጣሪ ፍቃድ ብቻ እሙን ነው። ዘረኝነት ራሱን አንደኛ ያደርጋል። የአብሮነት ድምፅ አልባ አጥፊ ነው። ዘረኝነት በመጨረሻ ሄዶ ሄዶ ከራሱ ጋር ይጣላል። ዛሬ ብሔሩን አስቀድሞ ከሌላው ብሔር ጋር የሚጋጭ፥ ትንሽ ቆይቶ ወደ ጎሳው ዝቅ ብሎ በብሔሩ ካሉት ከሌሎች ጎሣዎች ጋር ይጋጫል። ከዚያ እየወረደ ወደ ቤተሰብ ወርዶ ከቤተሰቡ ጋር ይጋጫል። በመጨረሻ ከራሱ ጋር ይጣላል። የዘረኝነት ሩጫ ወደ ውስጥ ነውና ሄዶ ሄዶ ከራሱ ጋር ይላተማል። የነገሩ ፍፃሜ ምንድነው? ምርጫችን የትኛው ነው? ለዘመናት “የኢትዮጵያ ሕዝብ” ስንባል ቆየን። ይህ አጠራር የዜግነት ዘረኝነታችንን ያሳብቃል። ዘመን አመጣሹ “ብሔር ብሔረሰብ ሕዝቦች” ብሎ ይጠራን ጀመር። ይህ አጠራር የብሔር ዘረኝነታችንን ያሳብቃል። ያልታሰበው ዐሳብ ደግሞ “የኢትዮጵያ ቤተሰብ” ሊለን ይፈልጋል። ክፋቱ ፖለቲካችን ለራሱ ፍላጎት የሚጠቅመውን እንዲጭንብን ያደርጋል እንጂ ለሕዝብ የሚጠቅመውን አያደርግም። ኢትዮጵያ ራሳችን እንደሆንን በዚያ ማንነታችን እንታወቅ ዘንድ አልቻልንም (Ethiopia: To Be Known As We Truly Are)። ዘረኝነት ካመጣብን ከዚህ የማንነት ጭንብል ማን ይገላግለናል? “እግዚአብሔር አንድ ጊዜ ተናገረ፥ እኔም ይህን ብቻ ሰማሁ፤ ኃይል የእግዚአብሔር ነው” (መዝሙረ ዳዊት 62፡11)። በተከታታይ እንመለከታለን፥ በደወል 4 ዘ ኢትዮጵያ እንገናኝ። ፀሐፊውን ለማግኘት: www.myETHIOPIA.com ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
በደወል 1 ዘኢትዮጵያ፥ ኢትዮጵያ በሚድን በሽታ ተይዛ ግን በሽታው እየገደላት እንደሆነ ተመለከትን። አሁን ደግሞ ይህንን በሽታ ተመልክተን እንነቃበት ዘንድ ደወል 2 ዘኢትዮጵያን እንመለከታለን። በሽታውን ስናውቅ መድኃኒቱ ይታየናል። ይህንን ለማድረግ በኢትዮጵያ ያሉትን ሦስት ገፀ ባህሪያት ለምሳሌነት እንውሰድ። አንደኛ የኢትዮጵያ ሕዝብን ተጠያቂ የሚያደርግ ሰሚ ያጣ ፈጣሪ አለ። ሁለተኛ የኢትዮጵያ ልሂቃንን ተጠያቂ የሚያደርግ ሰሚ ያጣ ሕዝብ አለ። ሦስተኛ ብዙ ሰሚዎችን ያገኙ የጠብ ገበሬዎች አሉ። ሰሚ ያጣ ፈጣሪ፦ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠየቅ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኑሮ ጋር እየታገለ ቀን ያልፍልኛል በማለት ተስፋ የሚያደርግና ተስፋ ባለመቁረጥ የሚታወቅ ነው። ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው፥ ሰውን በሰውነቱ በማየት ከተለያዩ ብሔር ተወላጆች ጋር በጋብቻ የተገመደ ነው። አስቸጋሪ የሆነውን ኑሮ በአብሮነት እየተረዳዳና እየተደጋገፈ፥ ሃይማኖትና ዘር ሳይለየው ለዘመናት በፍቅር የኖረ ነው። ተረኛ ባለስልጣናት እየነገሱ ቢፈራረቁበትም፥ ሕዝብ ሁሉም ያለ ልዩነት የመከራን ገፈት እየተጋፈጠና ለሀገሩ ደሙን እያፈሰሰ ኢትዮጵያን እስካሁን ያቆየ ነው። ሲቸግረው አመፅ አድርጎ መንግስት ቢቀየር፥ ቤተመንግስት አይገባ ነገር፥ ወደ ቤቱ አደራ ሰጥቶ ይመለሳል። ይሁን እንጂ ባለ አደራው መንግስት አደራውን ቀርጥፎ እየበላ ሕዝብን ባዶ እጁን ያስቀረዋል። ይህም ሳያንስ መንግስት ሕዝብን ምረጥ እያለ ያታልለዋል። ሕዝብ ስልጣን ተሰጠኝ ብሎ ቢመርጥም፥ ወይ ምርጫው ይሰረቃል፥ አለበለዚያም በሐቅም ተመረጠ ቢባል እንኳ አደራው ይበላል። ኢትዮጵያ በመልካም ሕዝብ፥ በለምለም ምድር፥ በውብ የአየር ፀባይ ብትታደልም፥ እጣ ፈንታዋ ድህነት ሰቆቃና ሞት ሆነ። ሕዝብ መውጫ ቀዳዳ አጥቶ፥ ሀገሩ እስር ቤት ሆኖበት፥ የቻለው ለመኮብለል ይናፍቃል። እንባውን ለፈጣሪ እያፈሰሰ ለዘመናት ኖረ። በሌላ በኩል ሰማይ ጥሪ ያቀርብልናል። ፈጣሪ እኛን እንዲሰማን እንደምንፈልግ ሁሉ፥ ፈጣሪም እርሱን እንድንሰማው ይፈልጋል። የሕዝብ ሀብትና ንብረት ብቻ ሳይሆን የሚዘረፈው፥ የተስፋ ቃሉ እንኳን ሳይቀር በባለተረኞች ይሰረቃል። ኢትዮጵያን በከፍታ ስፍራ የሚያስቀምጣት ፈጣሪ ራሱ ነው። ግን በኢትዮጵያና በፈጣሪ መካከል እየገባ ቦታውን የሚወስድ ባለጊዜ ባለስልጣን ነው። ያንን ደግሞ ሳያውቅ የሚያደርገው ሕዝብ ራሱ ነው። የቀድሞ መሪን የይሁዳ አንበሳ ብለን ማስተጋባት ስናበቃ፥ የአሁኑን መሪ ደግሞ መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ሙሴ ብለን አረፍን። የእስራኤልን ዓላማ ኢትዮጵያ መኮረጅ አትችልም። የእስራኤል ሕዝብ ጥሪ በአንድ ሰው ያውም በአብርሃም ላይ የተመሰረተ ነው። ስለሆነም ያዕቆብ እስራኤል በመሆን የቃል ኪዳኑን ሕዝብ መሰረተ። ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች [1] ማለት፥ ጥሪው የቀረበው ለሕዝብ እንደሆነ ያሳያል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ጥሪ በሕዝብ ላይ የተመሰረተና ከእርሱ ጋርም የተያያዘ ነው። ለኢትዮጵያ ሙሴ ትላንት አልነበረም፥ ዛሬም የለም፥ ወደፊትም አይመጣም። ፈጣሪ ኢትዮጵያን በግለሰብ እጅ ሳይሆን በሕዝብ እጅ ያሻግራታል። ለዚያ ጥሪው የቀረበለት ደግሞ ሕዝብ ነው። ኢትዮጵያን የሚያሻግር የሰው ሙሴ እንደሌለ ሁሉ፥ ኢትዮጵያን የሚበታትን የሰው ሰይጣንም የለም። ለደጉም ለክፉም ግለሰብ ላይ መንጠልጠላችን ይቅር። ይልቁንስ የኢትዮጵያ ሕዝበ ቤተሰብ መለኮታዊ ጥሪውን ለመቀበል ይነሣ። ያኔ ፈጣሪም ይነሣል። ቅዱስ ቃሉ እንዲህ ይናገራል፦ “ስለ ድሆች መከራ፥ ስለ ችግረኞች ጩኸት እግዚአብሔር፦ አሁን እነሣለሁ ይላል፤ መድኃኒትን አደርጋለሁ፥ በላዩም እገልጣለሁ” [2]። ሰሚ ያጣ ሕዝብ፦ የኢትዮጵያ ልሂቃን ይጠየቁ የኢትዮጵያ ልሂቃን ከኢትዮጵያ ሕዝብ አብራክ የወጡና እሴቱን የሚያንፀባርቁ ናቸው። ራሳቸውን መስዋዕት በማድረግ ይህ ሕዝብ ያልፍለት ዘንድ እንደ ሻማ እያለቁ የሚያበሩ ናቸው። በጥበብና በዕውቀት የተካኑ ትልቅ ሰዎች ናቸው። ያም ቢሆን እስካሁን አልተሳካላቸውም። ብርሃኑ እንዳያበራ ንፋሱ ሻማውን ያጨልመዋልና። ሁሉ ከንቱ ሆኖባቸዋል። ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ትርፍ ለሌለው ነገር ማንከራተት ሆኖባቸዋል። ምንም ያህል ሐቀኛና ታታሪ ቢሆኑ የሚያመክናቸው ነገር መኖሩ ነው። ልፋት ብቻ። ሁሉ ነገር የአንድ ሰሞን ጉዳይ ሆነ። ብርታታቸው ራሳቸውን መስዋዕት ማድረጋቸው ነው። ድክመታቸው ደግሞ የራሳቸውን ግላዊ ራዕይ መሰዋት አለመቻላቸው ነው። ሰው ብዙ ዋጋ እየከፈለ ግን መነሻ አሳቡ ስህተት ከሆነ ኢላማውን አይመታም። ሰው ሊሞት ይችላል። ብዙ መከራ ሊቀበል ይችላል። ያም ሆኖ የግልን ራዕይ ጥሎ፥ በአንድነት ለኢትዮጵያ ባለመነሳቱ ብኩን ሆኖ ሊቀር ይችላል። ዋናው ቁምነገር ከጀርባው የሚገፋው ሃይል ከእኔነት መፅዳቱ ነው። በእኔነት ከተነዳን አንድ ሆነን መቆም አንችልም። አንድነት እንዲመጣ ራስን ክዶ፥ ከሌላው ጋር በትሁት ልብ ሆኖ፥ ለሕዝብ ጥቅም ሙሉ በሙሉ መሰጠት አለብን። ፍሬያማ የመሆን ምስጢር ያለው ለእኔነት ሞቶ፥ ከሌላው ጋር በአንድ ልብ መያያዝ መቻል ነው። በልብ እልከኝነት ያለ ፍሬ እንዴት ዕድሜያችንን እንጨርሳለን? አንቆ የያዘን ከእኛ ውጭ ያለው ሳይሆን፥ በእኛ ውስጥ የተደበቀው እኔነታችን ነው። አስተሳሰባቸውና አመለካከታቸው የተለያየ መሆኑ ችግር አይደለም። ይህ የአሳብ ልዩነት ፀጋ ነው። ግን የዚህ የአሳብ ብዝሃነት ፀጋ የሚገለጠው መነጋገር ሲኖር ነው። መነጋገር ደግሞ ወደ መግባባት አምጥቶ ራሳቸውን የሰውለትን ለውጥ ማምጣት ያስችላል። ደግሞ መግባባት ችግር አይሆንም ነበር። ምክንያቱም በልባቸው ያለው ራዕይ ለሕዝብ ስለሆነ፥ ያ የጋራ ጥቅም ለማግባባት አቅም አለው። ውይይት ቢኖር ልዩነቱ ተጋጭቶና ተፋጭቶ መድኃኒት ይወጣው ነበር። አሁን የተያዘው መጮህ ነው። እንደ ገደል ማሚቶ። ጩኸቱን ሌላው አይሰማም። የሚጮህ ራሱ የራሱን ጩኸት ይሰማል። ነገር ግን ይህ ሁሉ ታሪክ የሚቀየርበት ጊዜ አለ። ያም የኢትዮጵያ ሕዝብ ፈጣሪን ሰምቶ ለተሰጠው መለኮታዊ ጥሪ ራሱን መልስ አድርጎ ሲቆም፥ ልሂቃንም እንደዚሁ ሕዝብን ሰምተው በአንድ ልብ ለመገለጥ ግድ ይላቸዋል። ብዙ ሰሚዎችን ያገኙ የጠብ ገበሬዎች ፈጣሪና ሕዝብ ባልተሰማበት ሁኔታ እነዚህ ግን ብዙ ሰሚዎችን አገኙ። እነዚህ ሰርጎገብ ናቸው። የኢትዮጵያ አይደሉም። የግላቸው ናቸው። ሁሉም ውስጥ ተደብቀው ሀገር እንዲታመስ ምክንያት የሚሆኑ ናቸው። የትም ከለላ ውስጥ ቢሆኑ የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር ነው። ያም ለግል ጥቅም የሚኖሩ ናቸው። ፖለቲከኛ ሽፋን ውስጥ ሲገኙ ራሳቸውን ለማኖር እንጂ ለሕዝብ ሊኖሩ አይደለም። ሃይማኖት ውስጥ ሲሸሸጉ ለፈጣሪ ክብር ሊያመጡ ሳይሆን ለራሳቸው ክብር ለማምጣት ነው። ሕዝብ ውስጥ ሲደበቁ ለሕዝብ ተቆርቁረው ሳይሆን፥ ብሔራቸውን መነገጃ ለማድረግ ነው። እነዚህ ኢትዮጵያን ለማቃጠል እሳት የሚጭሩ ክብሪት የሆኑ ናቸው። ሥራቸው የጠብ ግብርና ነው። የሚዘሩት ዘር ደግሞ ጠብ ይባላል። ቃሉ ስለነዚህ እንዲህ ይላል፡ “እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፥ ሰባትንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፤ ትዕቢተኛ ዓይን፥ ሐሰተኛ ምላስ፥ ንጹሕን ደም የምታፈስስ እጅ፥ ክፉ አሳብን የሚያበቅል ልብ፥ ወደ ክፉ የምትሮጥ እግር፥ በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር፥ በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ” [3]። ፈጣሪ ከሃጢያት ሁሉ ይበልጥ ነፍሱ አጥብቃ የምትፀየፈው በወንድማማች መካከል ጠብ የሚዘራ መሆኑን ልብ እንበል። በወንድማማች መካከል የሚዘሩት ጠብ የሚያበቅለው ሁለት አይነት ፍሬ ይታጨዳል። በአንድ በኩል ሕዝብ አለመደማመጥና አለመግባባትን እያጨደ እርስ በርስ ይበላላል። በሌላ በኩል በሕዝብ ሰቆቃ ላይ የጠብ ገበሬዎች ሀብት ዝናና ስልጣን እያጨዱ ለራሳቸው ጥቅም ትርፋቸውን ይበላሉ። የነገሩ ፍፃሜ ምንድነው? ሲጀመር የሚሰማ ጆሮ ይኑረን። መሰማት ያለበትን አስቀድመን እንስማ። የሕዝብ ጆሮ ሰሚ ያጣውን ፈጣሪ ለመስማት ይከፈት። የልሂቃን ጆሮ ሰሚ ያጣውን ሕዝብ ለመስማት ይከፈት። ያንን ከሰማን ወደ እርስ በርስ መደማመጥ እንመጣለን። ስንደማመጥ ደግሞ ወደ መግባባት እንደርሳለን። ስንግባባ አብረን እንደ አንድ ሆነን እንቆማለን። አንድ ላይ አንድ ሆነን ስንቆም፥ ያኔ ከመድኃኒታችን ጋር እንገናኛለን። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። በተከታታይ መመልከታችንን እንቀጥላለን። በደወል 3 ዘኢትዮጵያ እንገናኝ። ፀሐፊውን ለማግኘት: www.myETHIOPIA.com ተጠቃሽ፦ [1] መዝሙረ ዳዊት 68፡31 | [2] መዝሙረ ዳዊት 12፡5 | [3] መጽሐፈ ምሳሌ 6:16-19 ዶ/ር ዘላለም እሸቴ ይቅርታ፥ እርቅ፥ ምክክር፥ መግባባት። የማንለው የለም። ግን የሚደረግ ነገር የለም። ለምን? አንድ ነገር ለማድረግ ቀርቶ፥ ለመነጋገርም የማይቻልበት ደረጃ ላይ ነን። ማስረጃ ቢባል በሦስት ረድፍ ላስረዳ። አንደኛ ንግግር መጀመር አይቻልም። ሁለተኛ ንግግር ቢጀመር እንኳን መቀጠል አይቻልም። ሦስተኛ ንግግር መቀጠል እንኳን ቢቻል፥ መጨረስ አይቻልም። በዚህ ዓይነት የመፍትኤ ሀሳብ እንዳይወለድ (እንዳይሰማ) በሦስት ደረጃዎች መላን የሚያጨናግፍ ብዙ ጩኸቶች አሉ። 1ኛ/ ንግግር እንዳይጀመር ፈንጂ ተጠመደ
የተቀበረ ፈንጂ ስለማይታይ ሰላም ነው ብሎ በመሬት ላይ የሚራመድ ሰው ሁሉ ላይ አደጋ ያደርስበታል። ዛሬ ላይ የፈውስ ሀሳብን ማንሳት እጅግ የሚያስቸግርበት ሁኔታ እየሆነ ነው። የተናጋሪው ስም እንደ ታፔላ (ፈንጂ) ይሆናል። የሰው አስተሳሰቡ በራሱ እንዳይመዘን በማድረግ፥ የተናጋሪውን አስተሳሰብ እንዲመክን ይደረጋል። አንዱ የሚናገረው ነገር ጆሮ ለመክፈት እንዳይችል ፈንጅ እንቅፋት ነው። ገና ከመነሻው ሥር እንዳይዝ የሀሳብ ፍሰት ማጥለያ (filter) ይደነቀርበታል። ደግሞ የተወሰኑ ኮድ ቃላቶች እንደ ፈንጂ ያገለግላሉ። በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ተናጋሪው ሀሳቡን ሊያብራራ ይቅርና የሀሳቡን ርዕስ እንኳን ለመግለፅ እንዳይችል ያደርጋሉ። አንዳንዶቻችን ከነገሩ ጦም እደሩ ብለን በግል ሕይወታችን ላይ ብቻ እንድናተኩር ተገደናል። 2ኛ/ ንግግር እንዳይቀጥል ቋንቋ ተደበላለቀ በባቢሎን ከተማ ሰዎች ሰማይ የሚደርስ ሐውልት ሊሰሩ ተነሱ። ፈጣሪ ከዓላማው ጋር የሚሄድ ራዕይ ስላልሆነ ቋንቋቸውን ደባለቀ። አንድ ልብ ሆነው እንዳይሰሩ፥ ቋንቋ ተደበላልቆ መግባባት እንዳይችሉ አደረጋቸው። ከዚያ ሁሉን ትተው በዓለም ዙሪያ ተበተኑ። ይህ ታሪክ በእኛ ተደገመ፥ በፈጣሪ ሳይሆን በክፉው። ኢትዮጵያ በአብሮነት እንድንትገነባ በጎ ፍቃደኝነት እና ቅን ልቦና በኢትዮጵያ ልጆች ላይ አለ። ሁሉም የሀገሩ ነገር እንቅልፍ አሳጥቶት የሚታትርና የሚጥር እንደሆነ ይታወቃል። ግን ሁሉም የሚያውቀው ብዙ ዘርቶ ትንሽ ማጨዱን፥ ብዙ እየለፋ የሚታፈስ ነገር ግን ማጣቱን ነው። ኢትዮጵያን ለማዳን ላይ ታች በማለት በተስፋ ብንጠመድም፥ ትርፍ ሳይሆን ከዕለት ዕለት ኪሳራ ሆነብን። በዚህ ውስጥ አንዱ ንግግር መጀመር ከቻለ፥ የሚቀጥለው ፈተናው ደግሞ ንግግሩን መቀጠል ነው። ምክንያቱም ቋንቋ ስለተደበላለቀ ንግግሩን ያቆመዋል። አማርኛ እየተናገርን የምንለው ግን የተለያየ ሲሆን ቋንቋችን ይደበላለቃል። አፋን ኦሮሞ እየተናገርን የምንለው ግን የተለያየ ሲሆን ቋንቋችን ይደበላለቃል። ሌላውም እንደዚሁ። ቃላቶች ትርጉማቸውን ከደበላለቁብን፥ እንደ ባቢሎን ዘመን አልሆንምን? 3ኛ/ ንግግር እንዳይጨረስ በሰበር ዜና ፋታ ጠፋ የቁም ነገር ንግግርና ሚዛን የሚደፋ ሀሳብ የሚሰማ ጆሮ ብቻ ሳይሆን የሚያስተውል አዕምሮ ይፈልጋል። ለማስተዋል ሰከን ብሎ ማዳመጥና አውጥቶ አውርዶ ውሳኔ ለመወሰን ጊዜ መውሰድን ይጠይቃል። ታዲይ ሰብር ዜና ለዚህ ፋታ አይሰጥም። ከአንዱ ሰበር ዜና ወደ ሌላኛው እየተቀባበለ ለማሰብ ፋታ እንዳይኖረን ያደርጋል። እንደ ጉም በየጊዜው እየተነነ በማይጨበጥ ነገር እያደናገረን ጊዜያችንን ብቻ ሳይሆን እኛን ራሳችንን እየመዘመዘ ይበላናል። ሁልጊዜ እሳት ላይ እንደተጣድን ነው። እፎይታ የለም፥ ለማሰብ ፋታ የለም። ሰብር ዜና እኛን የሚሰባብር ዜና ቢባል ጥሩ ነበር። የነገሩ ፍፃሜ ምንድነው? የሁሉንም ጆሮ ቀልብ ይዞ አንድን አሳብ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ማድረስ ካልተቻለ፥ እየተነጋገርን አይደለም ማለት ነው። እስካልተነጋገርን ድረስ ደግሞ መግባባት ፈፅሞ አንችልም ማለት ነው። ካልተግባባን ደግሞ የሚድን በሽታችንን ማከም ስለማንችል፥ በሽታችን የምንኖር እስኪመስለን እያታለለን፥ ወደ ሞት ይወስደናል ማለት ነው። ታዲያ ምን ይሻላል? በተከታታይ እንመለከታለን፥ በደወል 2 ዘኢትዮጵያ እንገናኝ። |
ጤና ይስጥልኝ!ዶ/ር ዘላለም እሸቴ Archives
June 2024
Categories |