myEthiopia.com
  • ደወል

የዘላለም እይታዎች 

​የምንጠብቀው ሌላ፥ የሚሆነው ሌላ

8/20/2019

0 Comments

 
ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
 
ስለ ኢትዮጵያ በፍቅር ተነድፈን የምንጠብቀው አንድም ትንሳሄ (ተስፋ) ወይም መበታተን (ስጋት) ነው። ግን ሁለቱም እየሆነ አይደለም።  ወደፊትም እነዚህ አይሆኑምና ከመንፈስ መዋዥቅ ለመውጣት ምናልባት ራሳችንን መርምረን የምንጠበቀውን ተስፋም ሆነ ስጋት ከነባራዊ ሁኔታ ጋር አስታርቀን የሚሆን የሚሆነው ላይ ማተኮር ይሻል ይሆን እላለሁ።
 
እንደ ባለ አዕምሮ ሲታይ በኢትዮጵያ ምድር እንኳን ምርጫ ማድረግ ቀርቶ፥ በሰላም አብሮ መኖር ያልተቻለበት፥ በመፈናቀል አንደኛ ደረጃ በመያዝ ዓለምን የምትመራ ሰላም የደፈረሰባት ምድር እንደሆነ ሁሉም ያውቃል።  የፖለቲካ ፓርቲ የተባሉትም ምንና ስለምን እንደሚቆሙ ውሉ የማይታወቅበትና መድረክ አግኝተው በማያስተዋውቁበት አሁን ወቅት ላይ ቆመው በማግስት ምርጫ ለማድረግ ተዘጋጅተናል ብለው ማወጃቸው ይገርማል የሚል ያልገባው ብቻ ነው። ግራ የሚገባን የምንጠብቀው ከሚሆነው ጋር ስለሚጋጭ ነው።
 
ዶ/ር አብይ መራሹ ፓርቲ (ግንባር) ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ (ማለትም ሶማሌ፥ ጋንቤላ ወዘተ ጨምሮ) አዲስ ስም ይዞ ብቅ ሊል በስራ ላይ መሆኑን ተነግሮናል።  ተቃዋሚ (ተፎካካሪ) ፓርቲዎችም እየተደመሩ (እየተዋሃዱ) በተባባሪነት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ እያየን ነው።  ኢትዮጵያዊነት እና ዘረኝነት (እንደ ውሃና ዘይት መቀላቀል ባይችሉም) በምድረ ኢትዮጵያ በአብሮነት ታቅፈው እየተሰበኩ እዚህ ደርሰናል፥ ይቀጥላልም።  ሀገር ላይ ብሔራዊ መግባባት ይኑር እያልን በየቦታው የምንጮህ ሁሉ ዲሞክራሲ ኖሮ በመናገራችን ብቻ ረክተን መቀመጥ ሳይሻለን አይቀርም።
 
ምርጫው የዛሬ ዓመት እንዳሰቡት ይካሄዳል።  የዛሬ ዓመት አዲሱ ኢሕአዴግ ራሱን ለውጦና ሌላውን ውጦ ለምርጫ ያለ ሁነኛ አማራጭ ራሱን ለሕዝብ ያቀርባል።  ለዚያ ዓይነት ምርጫ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ምርጫውን ለማካሄድ እንቅፋት አይሆንም። እኛ በባዶ ሜዳ የምንጨነቀው የሚሆነውን ሳይሆን የማይሆነውን እያሰበን ግራ ስለሚገባን ነው።
 
ሕገ መንግስቱንም በውል ያወቅነው አይመስለኝም።  ጭራሽ ይጥፋና አዲስ ሕገ መንግስት እንፃፍ የምንልም ሆነ በሕጋዊ መንገድ በሂደት ይሻሻል ብለን የምንከራከረው አሁንም በባዶ ቦታ ነው።  ሁለቱም እንዳይሆን ተደርጎ ተቆልፎ ነው የተሰራው።  በሕጋዊ መንገድ ይሻሻል ቢባል፥ በተለመደው የማሻሻያ ሂደት ሳይሆን በልዩ ድንጋጌ እንዳይቻል ተደርጎ እንደተቀመመ የሚያውቅ ማን ነው? ጭራሽ ይጥፋና አዲስ ሕገ መንግስት እንፃፍ ቢባል፥ ለሶስት አስርተ ዓመታት በኢትዮጵያ የተዘራው መርዝ ምን ያህል እንደቦረቦረን የሚያውቅ ማን ነው?  ከዚህ ሁሉ ወደ ብሔራዊ መግባባት መጥተን መውጫ መንገድ እንዳንፈልግ መካከለኛውንና የሚሆን የሚሆነውን ማየት ደግሞ እንደተሰወረብን የሚያውቅ ማን ነው?
 
እውቀቱ ጠፍቶን ሳይሆን፥ ከትንሳሄ ተስፋና ከመበታተን ስጋት እየዋዥቅን የምንላተመውና በመሬት ላይ ያለው እውነታ ከምንጠብቀው ጋር የሚጋጨው፥ የኢትዮጵያ ፍቅር አሳውሮን ይሆን?  የኢትዮጵያ ነገር የሚፈታው ዛሬ ሳይሆን በትውልድ ዘልቆ ቢሆንስ?  ለዚያ ራሳችንን አዘጋጅተን፥ ለሚሆን ነገር ብንተልም ይበጅ ይሆንን?

​የኢትዮጵያ አምላክ ኢትዮጵያን ያስባታል።  ትዕግስት ይስጠን።
0 Comments

​ወሎ የማን ናት?

8/10/2019

0 Comments

 
ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
 
ፕሮፌሰር ህዝቅኤል ጋቢሳ ወሎ ኦሮሞ ነው ሲል፥ታሪክ ላይ ተደግፈን ስለ ወሎ ባለቤትነት ጥያቄ መልስ ለመስጠት ከመሞከር በፊት የጥያቄው ጤንነት ይታሰብበት።
 
ጭር ሲል አልወድም ሆነና ነገሩ፥
ጫጫታው ይድራልኝ አለ በመንደሩ።
 
ያለ አዕምሮ ጠብ ጫሪ፥ “ወሎ ኬኛ”
ባለ አዕምሮ አቃፊ፥ “ኢትዮጵያ ሀገሬ ነው። ወሎ ወገኔ ነው”
 
ትላንት አዲስ አበባ
ዛሬ ወሎ
ነገ ደንቢ ዶሎ
ሰው መሆን ቀሎ
 
ሕፃን፥ ሁሉም የእኔ ነው ብሎ ያላዝናል።
ጎልማሳ፥ እንዴት በአብሮነት እንኑር ብሎ ይመክራል።
ሽማግሌ፥ ለተተኪው ትውልድ ሰላም እንዲበዛ ይተጋል።
 
ጣና ኬኛ
ወለጋ የኛ
ኬኛ የኛ
የኛ ኬኛ
ኢትዮጵያኛ
 
ኢሜል፥ Z@myEthiopia.com
0 Comments

ለዶ/ር ዐብይ ምክር

8/4/2019

1 Comment

 
ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
 
የተከበሩ ዶ/ር ዐብይ፥ ይስሙኝና!
 
ዶ/ር ዐብይ የኢትዮጵያዊነትን ትንሣኤ በውብ ቃላት ከማወደስ የሚያልፍና በሥራ ወደዚያ ለማሻገር የሚያሽችል ፍላጎት እንዳላቸው አምናለሁ።  የጠቅላይ ሚኒስቲሩን ጆሮ ባገኝ፥ የምነግራቸው ውዳሴ ወይም አፍራሽ ወቀሳ አይደለም።  በዚያ ፈንታ ድካማቸውን የሚቀርፍ የሚያንፅና የሚገነባ ሀሳብ ለመወርወር ግን እቸኩላለሁ።
 
ድካማቸውን ስዘረዝር የታዘብኩት ዋና ነገር የድካማቸው ፍሬ ነገር ራሱ የተመሠረተው በእሳቸው በጎ ሥራ ላይ ነው።  ይህ ማለት የጠነሰሱትን መልካም ሥራ ዳር ሳያደርሱት በተንጠልጠል መንገድ ላይ እንዳይቀር ለማሳሰብ ነው።
 
ዶ/ር ዐብይ በንግግር ያስዋቡትን ኢትዮጵያዊነት በሥራ ለመተርጎም ዛሬ ውለዱ ልንላቸው ባይቻልም፥ ብሔራዊ መግባባት እንዲኖር ብሔራዊ ውይይት እስካሁን እንዲኖር አለማድረጋቸው ቅር ያሰኛል።  ለ 97 ምርጫ ሰው ሁሉ የፖለቲካ ውይይት ሲደረግ የነበረውን ዓይነት አውድ፥ ለኢትዮጵያዊነት ልምላሜ ብሔራዊ ውይይት ለምን ዛሬ አይፈጥሩልንም?  ሁሉም ዳርና ዳር ቆሞ የተቀበራረቀ ነገር ከሚጮህ፥ በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ተብሎ ስለ ቀጣይ ኢትዮጵያዊነት ትምህርታዊ ውይይትና የሀሳብ ፍጭት በብሔራዊ ደረጃ የሚደረገው መቼ ነው?  ይህ ብሔራዊ የመግባባት ሂደት መርሀ ግብር በአራት ደረጃ ሊቀመጥ ይችላል።  ይህም ጉዞ በመጨረሻ ወደ ምርጫ ሲያደርሰን፥ ያኔ ይህ እርምጃ ለፖለቲካዊ መፍትኤ መንገድ ጠራጊ መሆኑን ባየን ነበር። 
 
1ኛ ደረጃ መርሀ ግብር / የሃይማኖት አባቶችን ለኢትዮጵያ ትንሣዬ ይጋብዙ።
 
ዶ/ር ዐብይ ኦርቶዶክስ፥ ሙስሊምና ፕሮቴስታንት ሃይማኖት አባቶችን በማስታረቅ ፋና ወጊ ናቸው። ሲሆን ሲሆን የሃይማኖት አባቶች ለመንግስት የሞራል ኮምፓስ መሆን ሲገባቸው፥ በሁሉም ክፍል ያሉ የሃይማኖት አባቶች ከሰማይ የተሰጣቸውን ጥሪ ሳይወጡ ቀርተው፥ በተገላቢጦሽ መንግስት የሃይማኖት አባቶች መፍትሄ ሆኖ ተገኘ።  ታዲያ ዶ/ር ዐብይ ይህንን ያላቸውን ቅቡልነት ለኢትዮጵያ መፈወስ ጭምር ለምን አይጠቀሙበትም?  ብሔራዊ የንሰሀና የእርቅ አውድ በምድራችን እንዲፈጠር፥ እነዚህ የሃይማኖት አባቶች በኢትዮጵያዊነት ተቀናጅተው፥ በየቤተ እምነታቸው ህዝብን ይዘው በፈጣሪ ስር እንዲወድቁ ለምን አያሳስቡም?  ከራሳችን እና እርስ በርስ ተጣልተን ስንባላ፥ ሰከን አድርጎን ወደ ልባችን የሚመልሰን ፈሪሃ ፈጣሪ አይደለምን?  የሁሉም ችግር ስር ብንጎረጉር መንፈሳዊ ነው።  ስለዚህ በዚህ በአምላክ ረድሄት ጉዞ ብንጀምር የሚቀጥሉት መርሀ ግብር ደረጃዎች ውጤታማ ይሆናሉ።
 
2ኛ ደረጃ መርሀ ግብር / ምሁራን በእውነት ትርክት ታሪክን እንዲያስታርቁ ይጋብዙ።
 
ዶ/ር ዐብይ የዲሞክራሲ ነፃነት እንዲያድግ መፈለጋቸው እርግጥ ነው።  ግን ይህ ዲሞክራሲ እንዲዳብርና ስኬታማ እንዲሆን ጠራጊ መንገድ ማስቀመጥ ያስፈልጋል።  እንዲሁ ልቅ የሆነና ስትራቴጂ የሌለው አካሄድ ዙሪያ ጥምጥም ይወስደናል እንጂ መልካም ቦታ አያደርሰንም።  ለምሳሌ ፖለቲከኞች/አክቲቪስቶች ወሬያቸው እጅ እጅ ሳይል መላ ይፈጠር።  እስቲ ለለውጥ ያህል ምሁራን ደግሞ ማስረጃ እየጠቀሱ እንዲያስተምሩ ድምፅ ማጉሊያውን ይያዙ።  ምሁራን እውቀትን ተደግፈው ሲወያዩና ሲከራከሩ እንስማቸው።  ብሄራዊ መድረክ ተሰጥቷቸው ኢትዮጵያን ያሳዩን።  በየጎራው የሚሰማው ድምፅ፥ የፈጠራ ታሪክ ሆነ እውነተኛ ታሪክ፥ በሕዝብ ህሊና እንዲዳኝ ለሁላችንም ጆሮ የሚደርስ፥ አንድ ወጥ የውይይት መድረክ እጅግ ያግዛል።  እውነት በእርግጥ አርነት ያወጣናል።  በሌላ በኩል ደግሞ እውነት ብቻውን አይፈውሰንም።  ለዚህም ይህ መርሀ ግብር ወደ ሦስተኛው መርሀ ግብር ይሻገር ዘንድ ያስፈልገዋል።
 
3ኛ ደረጃ መርሀ ግብር / የሀገር ሽማግሌዎች እርቅና ሰላምን እንዲያሰፍኑ ይጋብዙ።
 
ዶ/ር ዐብይ የእርቅ ኮሚሽን ማቋቋማቸው እጅግ ቢደነቅም፥ መግለጫ ማውጣት ሳይሆን የሽምግልናውን ሥራ ዛሬ መስራት ያዋጣናል።  በፓርላማ ከተቀመጡት የሕዝብ ተወካዮች ይልቅ፥ ኢትዮጵያ ዛሬ የሚያስፈልጋት በእርቅ ኮሚሽኑ ክንዋኔ ከየወረዳው የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ጉባሄ ቢፈጠር ነው።  በሃይማኖት አባቶች ብሔራዊ የፆምና ፀሎት ጥሪ ሕዝብ ልቡን ወደ ፈጣሪ ከመለሰ፥ የሀገሩን ችግርና መፍትሄ በምሁራን ትንታኔ ግንዛቤን ካገኘ በሁዋላ፥ ያኔ ሕዝብ ለእርቅ ሂደት ራሱን አዘጋጅቶ ይገኛል።  ያኔ ሀገር በቀል የሆኑት ሕዝባዊ ሽማግሌዎች መፍትሄ ይሆናሉ።  ለዚህ የእርቅ ሂደት ብሔራዊው መድረክ በሶስተኛ መርሃ ግብሩ ይህን አጀንዳ ያስኬደዋል ማለት ነው።  ስለ ኢትዮጵያዊነት ፈውስ ፖለቲከኞች መፍትኤ አያመጡም።  የኢትዮጵያዊነት መታመም መንስሄው ሕዝቡ አይደለም። ፖለቲከኛ ነን ባዮች እንጂ። ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት እንዲፈወስና መካከለኛ ቦታ እንዲይዝ ከተፈለገ፥ ከፖለቲካው ትህይንት በፊት፥ ሕዝብ መሪነቱን ቦታ እንዲይዝ የሃይማኖት አባቶች፥ ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች ይቅደሙ። 
 
4ኛ ደረጃ መርሀ ግብር / ፖለቲከኞች በዲሞክራሲ ምርጫ እንዲፎካከሩ ይጋብዙ።
 
ከዚህ በፊት ይተጠቀሱትን ሶስቱን ሕዝባዊ መርሀ ግብሮችን ስናካሄድ፥ ጊዜው ይሄድና ወደዚህ አራተኛ ደረጃ ያደርሰናል።  ያኔ ፖለቲከኞች ካረፉበት ቤት (ካስቻላቸውና ዝም ብለው ከተቀመጡልን) የየራሳቸውን ፕሮግራም ለማስተዋወቅና ለሕዝብ ምርጫ ራሳቸውን ለማቅረብ የሚፎካከሩበት ብሔራዊ መድረክ ይሆንላቸዋል። 
 
ለነዚህ አራት ውይይቶች ግብሃት እንዲሆን ብሔራዊ የመግባባት ሚዲያ ኮሚሽን ማቋቋም ያስፈልጋል።  ምክንያቱም ለዚህ ግብሃት የሚሠራው አንድ የመንግስት ሚዲያ ከመንግስት ቁጥጥር ስር ብቻ ሆኖ ማድረግ ፍትሀዊ አይሆንምና ነው።
 
የተከበሩ ዶ/ር ዐብይ፥ ይሰማል?
 
የኢትዮጵያ አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ!
ኢሜል፥ Z@myEthiopia.com
1 Comment
    Picture

    Archives

    December 2022
    August 2021
    July 2020
    November 2019
    October 2019
    September 2019
    August 2019
    July 2019
    June 2019
    April 2019
    February 2019
    December 2018
    October 2018
    August 2018
    July 2018
    June 2018
    May 2018
    April 2018
    October 2016

    Categories

    All

    RSS Feed

Copyright © 1999 - 2023
  • ደወል