myEthiopia.com
  • ደወል

የዘላለም እይታዎች 

​ይቅርታ እና ሕዝብ ዶ/ር አብይን ያሻግር

2/22/2019

0 Comments

 
ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
 
እስረኞች ሁሉ ተፈቱ።  ዴሞክራሲም ተወለደ።  በደስታ ሰከርን። አሁን አሁን ግን የጫጉላ ጊዜ እየጨረስን ይመስለኛል። ዶ/ር አብይ የምንቅፍብዎት አንድ ነገር አለኝ።  በሕግ የጊዜ ሂደት ሳይሆን ኢሰብዓዊ በሆነ ሁኔታ ሕዝብን በወከባ ማፈናቀል የብርሃን ስራ አይመስለኝም።  ጉዳዮን ወደ ፍርድ ቤት ይምሩትና ዜጎች መንግስትን ፍርድ ቤት ቆመው የሚሞግቱበት እውነተኛ ነፃና ፍትሀዊ ሀገር እንድትሆን ፈር ቀዳጅ ይሁኑ።  ከዚያ ባለፈ ሕዝቡን ሜዳ ላይ ከመበተን፥ የሚያርፉበትን ስፍራ ጭምር ማሰብ ኢትዮጵያዊነት ነው።  ኢትዮጵያዊ የመሆን ክብር በምድራችን እንዲነግስ አድርገው ሲያበቁ፥ በእርስዎ ብሩህ ዘመን እንዲህ ዓይነት ጭካኔ የማይታሰብ ነው።  ይህ ዓይነት ሥራ ከእርስዎ ስብዕና ጋር አይሄድም።  በዝምታ ሊያልፉትም አይገባም።  የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ በመጠየቅና ለመፈናቀል ችግር ማስተካከያ በመስጠት ይሻገሩ ዘንድ እለምንዎታለው።
 
ዶ/ር አብይ አህመድ ገና በኢሕአዴግ ሳይመረጡ “ጆሮ ያለው ይስማ” በማለት የእርስዎን ወደ ስልጣን መምጣት ስመኝ ነበር።  ምኞቴ ሰምሮ በጠቅላይ ሚኒስቴርነት መምራት ሲጀምሩ ከስጋት ይልቅ ተስፋ አይሎብኝ ብዙ ብዙ ብያለው።  እስካሁን ድረስ እርስዎ መደመርን ሲሰብኩ፥ ዘራፍ ማለትን ወደ ጎን ትተው፥ በሀሳብ ልዕልና አሸንፎ መደመርን ለማሳለጥ ትዕግስትን ጨብጠው ነውና አከብርዎታለው።
 
እኛ የለመድነው “ስንኖር ጎሣዊ”፥ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን አምክነን “አፈር” ነን ማለትን ነበር።  እርስዎ ግን ብቅ ብለው “ስንኖር ኢትዮጵያዊ፥ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን” ያሉት ራዕይ ብርሃን ፈነጠቀ።  በፍቅር ተደምረን በይቅርታ እንሻገር ብለው ያከናወኑት ድርጊቶች በታሪክ ቦታ አላቸው ብዬ አምናለሁ።  እውነተኛ ምርጫ አካሄደው ከተሸነፉ ከስልጣን ለመውረድ ቁርጠኛ እንደሆኑ አልጠራጠርም። በእኔ ግምት የተጣለብዎትን የዲሞክራሲ አዋላጅ የመሆን ሃላፊነትዎን በብቃት እንደተወጡ አምናለሁ።  ግን ይህ ሁሉ ሆኖ ዛሬ ዛሬ እርስዎ ፊት የተጋረጠው እንቅፋት እጅጉን ያሰጋኝ ጀመር።  ምክንያቱም ያስወለዱትን ዴሞክራሲ የሚገድልና ይልቁንም ወደ ብርሃን ከመሻገር ይልቅ ወደ ድቅድቅ ጨለማ እንድንዘፈቅ የሚያደርግ የዘራፍ ፈተና ውስጥ ለመግባት ዳዴ እያልን ስለሆነ ነው።
 
እስካሁን እንድንኖር የተደረገው በየጎራችን ተከፋፍለን “ሁሉም ለራሱ” በሚል እሳቤ ነበር።  ታዲያ “ስንኖር ጎሣዬ” ከሚለው አመለካከት በቃልና በስራ ሁላችንም ተግባብተን ወደ “ስንኖር ኢትዮጵያዊ” ለመሻገር፥ አሻጋሪ መንገዱን የሚጠርገው ዴሞክራሲ ብቻ ፍቱን መድሃኒት እንዲሆን ታስቦ ዴሞክራሲ ተወለደ። ታዲያ ዴሞክራሲ ተወለደ እንጂ የተወለደውን ዴሞክራሲ ተጠቅመንና በቅንጅት ተደራጅተን ራዕዩን በሕዝብ ድምፅ አሸናፊነት ዕውን ለማድረግ እምብዛም ብዙ መንገድ አልሄድንም።  እርስዎ ለማካሄድ የሚሮጡለት ምርጫ አዲስ የሕዝብ መንግስት ለመመስረት ብቻ ሳይሆን፥ የሚመረጠው መንግስት የሚያስተደዳድረው “ኢትዮጵያዊነትንም” በአብሮነትና በዴሞክራሲ ሂደት እንዲወለድ ለማስቻል ነው ብዬ አምናለሁ።
 
ዶ/ር አብይ ዘራፍ የማይሉ መሪ መሆንዎ ያስገርመኛል፥ ያስደስተኛልም።  አንዳንዴ ግን በዝምታ የሚሄዱት መንገድ ለእንቆቅልሽዎ መላ እስካልፈጠሩ ድረስ ረዥም አይሆንም ብዬ እፈራለሁ።  ምክንያቱም ዘራፍ ማለት የተጠናወታቸው ፖለቲከኞችና አክትቪስቶች አሉንና።  ሲሆን ሲሆን በተሻለ አሳብ ለመግባባት ወደ ውይይት፥ ካልሆነ ደግሞ በሕዝብ ድምፅ ለመዳኘት ወደ ፉክክር መግባት እንድንችል አቅም የሚሰጠንን ዴሞክራሲን ገና አልተዋወቅነውም።  አሁንም  የየግል አጀንዳዎቻችንን ሕዝብ ላይ ለመጫን ዘራፍ ማለት ይቀናናል።  በምድራችን የተወለደውን ለጋ ዴሞክራሲ በመጠቀምና በማሳደግ ወደ መግባባት መሄድ የሚያስችለውን የዴሞክራሲ ጉዞ ፋታ እንዳያገኝ ደንቃራ መሰናከያ ድንጋይ እንፈጥራለን።  የተወለደውን ዴሞክራሲ ገድለን ጡንቻ ማግነንን እንደ አንድ አማራጭ የያዝን ይመስላል።  ምናለበት ዴሞክራሲ ይዳኘናል ብለን የምናምንበትን ሀሳብ ለሕዝብ ማስተማርና ሁሉንም ጉዳይ ለውይይት ማቅረብ ጊዜና ቦታ መስጠት ብንችልበት?
 
ጥያቄው አሁን እንዴት ካለንበት አጥፍቶ ከመጥፋት፥ የመጠፋፋት ጨለማ ውስጥ ወጥተን፥ በፍቅር ብርሃን ተደምረን ወደፊት መሄድ እንችላለን ነው።  መልሱ ደግሞ ሲሆን ሲሆን ለተሻለ ሀሳብ ለመሸነፍ በዴሞክራሲ እሴት ወደ ውይይት መሄድ፥ ያ የሚያግባባ መፍትሄ የማያመጣ ከሆነ ደግሞ በሕዝብ ምርጫ ለመዳኘት በሁሉ መስክ ዴሞክራሲ እንዲገዛን ራሳችንን ለዴሞክራሲ መስጠትን መተግበር ነው።  ይህም ዕውን እንዲሆን ደግሞ መቀናጀቱን ማጠናከር ያስፈልጋል።
 
በዘራፍ አዋጅ ሀገር ለመንዳት ወይም እርስ በርስ ለማዋጋትና ለመዋጋት ከማሰብ፥ በመደመር ስሌት አካሄድ፥ ሲሆን በውይይት ሳይሆን በህዝብ ዳኝነት፥ መግባባት ላይ እንደርስ ዘንድ የዴሞክራሲ እሴት እንጠቀም።  ከሚያጣሉን ጉዳዮች አንዳንዶቹን ለምሳሌ ያህል ከዚህ በታች መጥቀስ ይቻላል።
 
1ኛ/ ሕዝብን የማፈናቀል አባዜ መቼና እንዴት ይቆማል?
2ኛ/ የክልል ድንበር ጥያቄ መቼና እንዴት ዕልባት ያገኛል?
3ኛ/ ራስን በክልል መንግስት የማስተዳደር ጥያቄ መቼና እንዴት መልስ ያገኛል?
4ኛ/ በሃላፊነት ስፍራ የተቀመጡ ሰዎች የጎሣዎች ስብጥር ፍትሀዊነት አለው ወይ?
5ኛ/ የሕግ የበላይነትን የማስፈን ተግዳሮቶች እንዴት ይፈቱ?
6ኛ/ ሕዝብ የሚመርጠው ፕሬዚዳንት ይኑረን ወይስ ፓርቲ የሚመርጠው ጠቅላይ ሚኒስቴር ይኑረን?
7ኛ/ ባንዲራችን የትኛው ይሁን?
8ኛ/ አዲስ አበባ የማን ናት? 
9ኛ/ የትኛው የፌዴራሊዝም ስርአት ለሁላችንም ፍትሐዊ ነው?
10ኛ/ ብሔራዊና የስራ ቋንቋዎች የትኞቹ ይሁኑ?
11ኛ/ ለአፍሪካ አንድነት ፋና ወጊ መሆንን እንደ ታሪካዊ ብሔራዊ ጥሪ እንውሰድ ወይ?
12ኛ/ ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ የሚለውን ዘይቤ እንደ ሕዝብ ዕውቅና እንስጥ ወይ?
ወዘተ
 
ዶ/ር አብይን የምንደግፍም ሆን የምንቃወም ሁሉ አንድ ነገር እናስብ።  ኢትዮጵያ ከዶ/ር አብይ በላይ ናት።  እርሳቸው መልካም አደረጉም ክፉ ያልፋሉ።  ኢትዮጵያ ግን ትቀጥላለች።  ስለዚህ ኢትዮጵያን አስበን፥ ዶ/ር አብይ የሕዝብን ዳኝነት በሚፈልጉበት ሂደት ውስጥ በምርጫ ዴሞክራሲ ማሳለጥ ሥራ ሁላችንም እንድንተባበራቸው ያስፈልጋል።
 
ከዚያ በተረፈ ኢየሱስ ክርስቶስን የመሰለ ስብዕና ያለውን በአንድ ወቅት ሕዝቡ ሊያነግሰው ሲፈልግና፥ በሌላ ጊዜ ደግሞ ያው ሕዝብ ሊሰቅለው ሲፈልግ አይተናልና አምላክ ከዚያ ይጠብቀን። ይልቁንም ኢትዮጵያን ለመታደግ፥ ሌት ተቀን ያለ እረፍት ደፋ ቀና የሚሉትን እኚህን የኢትዮጵያ ልጅ በቃላችን ከማፍረስ ይልቅ፥ ሲያጠፉ በመምከርና ሲያለሙ ደግሞ በማበረታት፥ በሁለቱም ረገድ ሰውን መገንባት ስራችን ማድረግ የቅንነት ምልክት ነው።  ከሁሉ በላይ በዴሞክራሲ ሜዳ ላይ ለመፋለም ሁላችንም በየፊናችን በሚያግባቡን ሀሳቦች ዙሪያ ተቀናጅተን ኢትዮጵያን ለመታደግ እንነሳ።  እኛ የነገውን ዕድል ፈንታ እንደ ሕዝብ የምወስን እኛ ራሳችን እንደሆን አውቀን የዜግነት ግዴታችንን በንቃትና በመተባበር ካልተወጣን፥ ዶ/ር አብይ በኢትዮጵያ ትንሣኤ መንገድ ላይ የተደነቀረውን ወጥመድ ጥሰው ኢትዮጵያን ማሻገር ተራራ ይሆንባቸዋል።
 
ከሁሉ በፊት ሰብዓዊነት ይቀድማልና፥ የተፈናቀሉት ሰዎች ጉዳይ አደራ!
 
እግዚአብሔር ኢትዮጵያ አሰበ።
እኛም እንወቅበት!
እግዚአብሔር አፍሪካን ይባርክ።
ኢሜል፥  Z@myEthiopia.com
0 Comments

ከኢሕአዴግ ፌዴራሊዝም ወደ መደመር ፌዴራሊዝም እንሻገር

2/18/2019

0 Comments

 
Picture
ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
 
የኢሕአዴግ ፌዴራሊዝም  በብሔር ወይም በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ነው እንዳልል ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሔሮች ሆኑ ሁሉንም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ማካተት ቀርቶ ባብዛኛው እንኳን የማያሳትፍ ስለሆነ በተለምዶ የዘር (ethnic) ፌዴራሊዝም የሚባለውን አጠራር መጠቀም አልችልም።  አሁን ያለው ፌዴራሊዝምን “የኢህአዴግ ፌዴራሊዝም ” ከማለት በቀር ሌላ ቃል ላገኝለት አልቻልኩም።  በዚያው መልክ ወደፊት እንዲኖረን የምሞግተው ፌዴራሊዝም በዓይነቱ አዲስ መሆን ያለበት ስለሆነ “የመደመር ፌዴራሊዝም ” በማለት ለመግለፅ ወድጃለሁ።
 
በኢትዮጵያ ከ 80 በላይ ብሔረሰቦች ወይም ጎሣዎች እንዳሉ እናውቃለን።  የኢሕአዴግ ፌድራላዊ መንግስት ጥቂት ጎሣዎችን አግንኖ እና ብዙ ጎሣዎችን ጨፍልቆ በክልል መንግስታት አደራጀን።  በእውነት ሁሉንም ጎሣዎች በእኩልነት የሚዳኝና የሚያስተናግድ ስርዓት አይደለም።  ከዚያም በላይ የኢትዮጵያን አንድነት ጥያቄ ውስጥ የሚከትና እርስ በርስ በማጋጨት የሚያፈናቅል ስንክሳር ሆኖ እየተገለጠ ይገኛል።  ይህንን ውጥረት ለመፍታት የብሔር ፖለቲካና የዜግነት ፖለቲካ በሚያደርጉት ሩጫ፥ መፍትሔ ከማምጣት ይልቅ ራሳቸው የእርስ በርስ ውጥረት ውስጥ ገብተዋል።  ያም የሆነው የኢሕአዴግ ፌዴራላዚም በሚያመጣው ተፅዕኖ ምክንያት ነው።  ለዚህም ነው ይህ የኢሕአዴግ ፌዴራሊዝም ራሱ ችግር መሆኑ ብቻ ሳይሆን፥ ሌላ መፍትሔም እንዳይመጣ ጭምር የሚያስረንና የማይድን የኢትዮጵያ በሽታ መስሎ የሚታየው።
 
በብሔር ፖለቲካ እና በዜግነት ፖለቲካ መካከል ያለውን ፍጥጫ በስኬት ለመፍታት፥ መደመር ላይ ከተመሰረተው ሀገር በቀል የኢትዮጵያዊነት ርዕዮተ ዓለም ውስጥ አስታራቂ የመደመር ፌዴራሊዝምን ፈልቅቆ  ማውጣት ያስፈልጋል።  ይህ መደመር ብሎ ነገር፥ ከስሜታዊ ትርክቶች አልፎ መሰረታዊ የሆኑ የማንነት ጥያቄዎቻችንን የሚመልስና በብዝሃነት አንድነት አያይዞ ወደፊት የምንሄድበትን አቅጣጫ ማመላከት መጀመር ያለበት ወቅት አሁን ይመስለኛል።
 
በአንድ በኩል ለእውነት እኩልነትና የማንነትን ጥይቄ በፍትሀዊነት ለመመለስ የመደመር ፌዴራሊዝም ስሌት መፍትሔ አለው።  ደግሞም በልዩነት የማይበጣጠስ ግን በልዩነት የሚደምቅና የሚሰምር እውነተኛ አንድነት እንዲኖረን የመደመር ፌዴራሊዝም ፋይዳ ያመጣል።  ይህም የሚሆነው የመደመር ፌዴራሊዝም የብሔር ፖለቲካንና የዜግነት ፖለቲካን አቻችሎ ሁለቱም አብረው እንዲያሸንፉ የመፍትሔ መውጫ አቅጣጫ ስለሚያስቀምጥ ነው።  በዚህም ምክንያት እንድንነካከስና እንድንጠፋፋ ከተጠመደልን ወጥመድ ሰብረን በብልሃትና በትልቅ ጥንቃቄ አንድ ላይ ተያይዘን እንድናመልጥ የመደመር ፌዴራሊዝም አቅም ይሰጠናል።
 
በአንድ በኩል ጎሣዎች የራሳቸውን እድል በራስ በማስተዳደር እንዲወስኑ እንፈልጋለን።  በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ጎሣዎች ስብጥርና በጂኦግራፊ አቀማመጥ ድብልቅ እንደሆነ እናያለን። ደግሞም 80 በላይ የሆኑ ጎሣዎች በእኩልነት እንዲወከሉና ሁሉም ድምፅና ተሰሚነት እንዲኖራቸው እንፈልጋለን።  ለዚህ አንደኛው መድሓኒት ጎሣን በዞን ደረጃ መከለል ነው።  ይህ አናሳ ጎሣዎች ሁሉ የየራሳቸው የዞን ክልል እንዲኖራቸው ዕድል ይሰጣቸዋል። ትላልቅ የሆኑት ጎሣዎች ደግሞ በየአቅራቢያቸው ዙሪያ በየቀጠናቸው እየሆኑ ከአንድ በላይ የዞን ክልሎች እንዲኖራቸው ማድረግ ይቻላል። እያንዳንዱ ዞን ራሱን እንዲያስተዳደርና ለሕዝብ ተወካዮችም ከዞናቸው በመላክ በፓርላማ መሰየም ይችላሉ።
 
ከዚያ ባለፈ እነዚህ በጎሣዎች የተዋቀሩት ዞኖች በመንግስታት ስር የሚከለሉት በጂኦግራፊ ይሆናሉ። ያ ማለት የደቡብ ክልል መንግስት፥ የሰሜን ክልል መንግስት፥ የምዕራብ ክልል መንግስት፥ የምስራቅ ክልል መንግስት፥ የደቡብ ምስራቅ ክልል መንግስት፥ የሰሜን ምዕራብ ክልል መንግስት፥ ወዘተ በማለት ማዋቀር ይቻላል።  እያንዳንዱ መንግስት በውስጡ የተለያዩ ዞኖች ይዞ “ትንሿ ኢትዮጵያ” በመሆን የገለጣል። ፓርላማ በዚህ ዓይነት የብሔር ማንነትን እና የዜግነት እኩልነትን ባስታረቀ መልኩ በሕዝባዊነት መሠረት ላይ ቢታነፅ መካከለኛ ቦታ ላይ ሁላችንንም ያገናኘናል ብዬ አስባለሁ።
 
ይህን ዓይነት በጂኦግራፊ የተመሰረተ መንግስታት እንዴት ማድረግ እንችላለን እንዳንል፥ በፍርደ ገምድልነት አንዱን ብቻ ነጥለን የደቡብ ክልል መንግስት ብለን አናሣ ጎሳዎችን አንድ ላይ ደምረን መንግስት እንዲኖራቸው ለ 27 ዓመት ያደረግን ጉደኞች ነን።  ያንን ለደቡብ ሕዝብ አድርገን ስናበቃ “ትንሿ ኢትዮጵያ” ስንል፥ በዚያው መስፈርት ራሳችንን መዝነን በሁላችንም ላይ በፍትሀዊነት ለምን አላደረግንም?  የሞራል ልዕልና ካለንና ራሳችንን ከሌላው በላይ አድረገን በእውነት ማየት የማንፈልግ ከሆነ፥ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ የመደመር ፌድራላዊ መንግስት ስር ያሉ የደቡብ፥ የሰሜን፥ የምዕራብ፥ የምስራቅ ወዘተ መንግስታት እያልን በፍትሀዊነት ማስተካከል ይጠብቅብናል።
 
ይህን ስናደርግ መደመርን በተፈጥሯዊ(organically) እንዲያድግ እንፈቅዳለን።  በመጀመሪያ ደረጃ በጂኦግራፊ በተመሰረቱት ክልል መንግስታት ውስጥ ያሉ የተለያዩ በጎሣ የተዋቀሩ ዞኖች መደመርን አቅራቢያቸው ካሉት ኢትዮጵያውያን ጋር ይለማመዳሉ።  በሁለተኛ ደረጃ በኢትዮጵያ የመደመር ፌድራላዊ መንግስት ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ መደመርን በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሳልጣሉ።  በሶስተኛ ደረጃ መደመርን ለአፍሪካ በመሸጥ ምስራቅ አፍሪካ ብሎም መላው አፍሪካ ወደ አንድነትና አብሮነት በመጠቅለል መደመር በጥቁር ሕዝብ ላይ ብሩህ ብርሃን ያበራል።  በአራተኛ ደረጃ ለዓለማችንም ይህ የመደመር ህሳቤ ገፀ በረከት ሆኖ ይተርፋል።
 
የኢትዮጵያ የመደመር ፌድራላዊ መንግስትን ደግሞ የሚመራ (ጠቅላይ ሚኒስቴር ወይም ፕሬዚዳንት) ሕዝቡ ራሱ እንዲመርጥ በማድረግ፥ የሚልቅ አሳብ የያዘ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከአናሣ ጎሳም ጭምር ለመመረጥ ፍትሀዊነት ያለው ዕድል ይኖረዋል።
 
በኢህአዴግ ፌዴራሊዝም ጣጣ ምክንያት ብዙ ቁጥር ያላቸው ጎሣዎች ሊሂቃን የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ተመልከተውና ለአናሣዎቹ ብሶት ጆሮ ዳባ ብለው የራሳቸው የሆነውን ለማግነን ተገደው ደፋ ቀና ይላሉ።  ዛሬ እኩልነትን ስናቀነቅን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲሆን ሆኖ እንዲሰራ ሳይሆን፥ ብዙ ቁጥር ያለው ሕዝብ ሊሂቃን በየፊናው ራሳቸውን የበላይ የሚያደርጉበትን ስሌት ለመቀመር በራሳቸው ዘር ላይ እንዲያጠነጥኑ ይገደዳሉ።  እነዚሁ ሰዎች ድሮ ድሮ ለጭቁን ሕዝብ ብለው ታግለው ንጉሱን የገረሰሱት በሰው መሆን ስብዕና ላይ ተመሰርተውና ተያይዘው እንጂ፥ እንደ ዛሬ በየግል ጎሣ አጥር ውስጥ ሆነው እየተራኮቱ አልነበረም።  ከዚህ ከያዘን አባዜ የምንነቃው የኢህአዴግ ፌዴራሊዝም ለሁላችንም የተለያየ መነፅር ሰጥቶንና በማይታረቅ ቅራኔ ውስጥ ከቶን የጭቅጭቅ ድራማ እንድንከውን  ያደረገንመሆኑን አውቀን ራሳችንን ከዚህ ወጥመድ ስንፈታ ነው።
 
መደመር ስሌት ላይ አተኩረን ተደምረናል ስንል የድምራችን ውጤት ዜሮ እየሆነ ያሳብቅብናል።  መደመር ውጤታማ የሚሆነው ተደምረናል የምንለው ቀናሽ ቁጥር (negative number) እስካልሆንን ድረስ ብቻ ነው።  አንዱ ሲተክል ሌላው እየነቀለ የደቦ ድምር ሆነን በዜሮ እንዳንጨርሰው እንጠንቀቅ።  ከመደመራችን በፊት ቀናሽ ቁጥር (negative number) ከመሆን ራሳችንን እናፅዳ።  ቀናሽ ቁጥር ላለመሆን ደግሞ ለራስ መቆም ብቻ ሳይሆን የወንድሞቻችን (በተለይ የተረሱትና አናሣ ለሆኑት) ፍፁም ፍትሀዊ የመሆን እሳቤ ያስፈልጋል።
 
ኢ+ት+ዮ+ጵ+ያ = ፍቅር።  ኢትዮጵያዊነት የፍቅር ቤት ነው።
 
1ኛ/ የኢትዮጵያዊነት ፍቅር ቤት መሰረት የጥቁር ሕዝብ አንድነት ፋና ወጊነት ሆኖ መገኘታችን ነው።  ኢትዮጵያዊነትን ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የጎሣዎች ስብስብ በላይ ነው።  ይህም የሆነው ኢትዮጵያዊነት በውስጡ የአፍሪካን አንድነት ያረገዘ ራዕይ ሰንቆ እንዲንቀሳቀስ ታሪክ ግድ የሚለው ስለሆነ ነው።
 
2ኛ/ የኢትዮጵያዊነት የፍቅር ቤት የማዕዘን ምሶሶዎቹ ብዙ ቁጥር ያላቸው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት ጎሣዎች ናቸው።  እነዚህም የኢትዮጵያዊነትን ግዙፍ ራዕይ ክብደት የሚሸከሙና በመስዋዕትነት ኢትዮጵያዊነትን የሚያቆሙ ናቸው።
 
3ኛ/ የኢትዮጵያዊነት ፍቅር ቤት ግድግዳው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት አናሣ ጎሳዎች ናቸው።  እነዚህም እርስ በርስ በመያያዝና ከምሶሶዎቹ ጋር በመቀናጀት ኢትዮጵያዊነትን የፈጠሩ ናቸው።
 
4ኛ/ የኢትዮጵያዊነት የፍቅር ቤት ጣሪያው የኢትዮጵያ አምላክ ነው።  ፈሪሃ ፈጣሪ ያለው ሕዝብ እርስ በርስ ሰላምታ በሰጠና በተቀበለ ቁጥር የፈጣሪን ስም የሚጠራ ሲሆን በረከትን ከሰማይ ይለምናል።  ከስንት ጉድ እያወጣን ለዛሬው ብሩህ የተስፋ ጭላንጭል ቀን ያደረሰን ፈጣሪም ዳር ሳያደርሰን አተወንምና በስጋት ከመሽመድመድ ይልቅ ተስፋ በማድረግ መደሳሰት ይቀናናል።
 
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰበ።
እግዚአብሔር አፍሪካን ይባርክ።
ኢሜል፦Z@myEthiopia.com
0 Comments

​አዲስ አበባ የእኛ አይደለችም

2/11/2019

1 Comment

 
ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
 
ትላንትንና ዛሬን እያጣቀስን አዲስ አበባን በባለቤትነት ለመውረስ የምናደርገው ትርምስ ይገርማል። አንዱ የኦሮሞ ናት ሲል፥ ሌላኛው የአዲስ አበቤዎች ናት ይላል፥ ደግሞ ሌላኛው የኢትዮጵያ ናት ይላል።  ዛሬ ላይ ቆመን ይህንን ማሰባችን አሁንም ነገን እያገናዘብን እንደማንራመድ ያሳያል።  ነገ የሚሆነውን አዲስ ታሪክ ለመፃፍ ከመነሳት ይልቅ፥ አሮጌ ታሪክ ወይም ዛሬው ያስረናል።  ታዲያ መድረሻችንን የማናውቅ ሆነን ሳለ፥ በለውጥ ጎዳና ላይ ነን ማለት ጥቅሙ ምንድነው?
 
አዲስ አበባ የኦሮሞ፥ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ህብረት መዲና ሆና ዛሬ እያገለገለች ነው።  ነገን ብናይ ደግሞ አዲስ አበባ የእኛ አይደለችም። ነገ የምስራቅ አፍሪካ አንድነት ብሎም የመላው አፍሪካ አንድነት ህልውና ከሕልምነት ወደ እውንነት ስለሚለወጥ፥ አዲስ አበባ ለዚያን ወቅት እየተሞሸረች ያለች የጥቁር ሕዝብ ሁሉ ዋና ከተማ ልትሆን ያለች ናት። ነገን ዛሬ እንዳየ ሕዝብ፥ ሁላችንም አዲስ አበባን በዚህ መነፅር አይተን፥ አዲስ አበባን ለጥቁር ሕዝብ የምስራችና የድል ዜና አብሳሪና ተስፋ ሰጭ ማዕከል እንድትሆን እንፍቀድላት። 
 
የራሳችን ጎሣ እንደ ትንሽ ደሴት በልፅጎና አድጎ ለብቻው በጨለማው ኢትዮጵያ ላይ እንዲገን እንፈልጋለን?  ኢትዮጵያ እንደ ትንሽ ደሴት በልፅጋና ተመንድጋ ለብቻዋ በጨለማው አፍሪካ ላይ ገና እንድትታይ እንመኛለን?  ካለንበት አዘቅት አንዳችን በአንዳችን ላይ ተረማምደንና ሁሉንም ወደ ዋላ ጥለን፥ ራሳችንን ብቻ ይዘን ወደ ላይ መውጣት አንችልም።  የራስ ጎሣ ተኮር ሆኖ ሁሉንም በዚያ መነፅር ማቀንቀን ጠባብነት እንደሆነ ሁሉ፥ ኢትዮጵያ ተኮር ብቻ ሆኖ ሁሉንም በዚያ መነፅር ማቀንቀን መጥበብ ነው።
 
በኢትዮጵያዊነት ስም አብሮነትንና አንድነትን ስናስብ፥ ጥቁር ሕዝብ ሁሉ እንዲያሸንፍ እናልም።  እኛ በጎሣ ተከፋፍለን እርስ በርስ ስንነካከስ፥ ልዩነታችንን እናገናለን እንጂ በዓለም ዕይታ ሁላችንም አንድ ጥቁር ሕዝብ ነን።  የኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ባስገባንበት ባሁኑ ወቅት፥ የአፍሪካን አንድነት ማሰብ ጅልነት ነው ይባል ይሆናል።  ነገር ግን ነገራችንን ከአፍሪካ አንድነት ሳንጀምር ቀርተን፥ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ መነታረካችን፥ ለመራኮታችን ምክንያት ቢሆንስ?  የተጠራንለትን ታላቅ ጥሪ ችላ ብለን፥ በመንደር ህሳቤ እርስ በርስ ስንበላላ እንዳንጠፋፋ ፈጣሪ ይርዳን። 
 
የነገው የምስራቅ አፍሪካ ብሎም የመላው አፍሪካ ዕምብርት ለመሆን ዕድል ያላት አዲስ አበባን ለዚህ ታላቅ ጥሪ እንድትመረጥ ታሪክ ስላደላት፥ ኦሮሞም ሆን፥ አዲስ አበቤዎችም ሆን፥ ኢትዮጵያውያንም ሆን፥ ሁላችንም በአዲስ አበባ ልዩ ታላቅ ጥሪ ልንኮራ ይገባል እንጂ፥ አሸናፊና ባለቤት ለመሆን እርስ በርስ አንጣላ።  አዲስ አበባ ከእኛ በላይ የሆነች ለጥቁር ሕዝብ ምልክት ናት።  ይልቁንስ ለአፍሪካ መድሃኒት ሆነን ራሳችንን እንድንፈውስ፥ ለጥቁር ሕዝብ ልዕልና ፋና ወጊ እንሁን።
 
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰበ።
እግዚአብሔር አፍሪካን ይባርክ።
Email: Z@myEthiopia.com
1 Comment

​ከምርጫ በፊት ሪፈረንደም

2/6/2019

0 Comments

 
ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
 
ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ሕዝቡ መሪውን ራሱ እንዲመርጥ የሚያስችለውን አሠራር  (ፕሬዚዳንታዊ መንግስት) ወይም ደግሞ እንደ አሁኑ ፓርቲው መሪውን እንዲመርጥለት የሚያደርገውን አሠራር (ጠቅላይ ሚኒስቴራዊ መንግስት)፤ ከሁለቱ መንገዶች አንዱን መርጦ ፈቃዱን እንዲያስታውቅ ለሕዝቡ በሪፈረንደም ዕድል ይሰጠው ዘንድ ለመሞገት አራት ማስረጃዎች አቀርባለሁ።
 
1ኛ/ ሕዝቡ አዋቂ ነውና እናውቅልሃለን ከእንግዲህ አይሰራም 
እናውቅልሃለን የሚሉ ሊሂቃን አንዴ ንጉስ፥ አንዴ ፕሬዚዳንት፥ አሁን አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር እያሉ መንግስት መሰረቱ።  የለውጥ አየር እየነፈሰለት እፎይታን በማጣጣም ላይ ያለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በእሳት ተፈትኖ አዋቂ የሆነ ነውና፥ ዛሬ ላይ ቆመን ቀንበር እንደ በፊቱ ባናሸክመው መልካም ነው።  ጊዜውን የሚመጥን አካሄድ በመከተል ሕዝቡ መሪዉን ብቻ ሳይሆን የመንግስቱን ዓይነት /system/ጭምር እንዲመርጥ ቢደረግ የሚመሰረተው መንግስት የሕዝብ መንግስት ለመሆኑ ዋስትና በመስጠት ያፀናዋል።  ሊሂቃን የትኛው እንደሚበጅ በየፊናቸው ጥናታቸውንና አመለካከታቸውን ለሕዝብ በውይይትና በክርክር ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።  ከዚያ ባለፈ ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ ብቃት ባገናዘበ ሁኔታ፥ እኛ እናውቅልሃለን ብለው ከመወሰን ተቆጥበው፥ ፍርዱን ለሕዝብ እንዲተው ለሂሊናቸው አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ።  ይህን አዋቂና ትልቅ ሕዝብ በማክበር ሕዝቡ ያለው እንዲሆን ውሳኔውን ለሕዝብ ይለቃሉ የሚል እምነት አለኝ። 
 
2ኛ/ ሕገ መንግስቱን ማስታመም
ሕገ መንግስቱ ተዐማኒ እንዲሆን ሕዝብ በመረጠው ሞግዚትነት ይፈተሽ ዘንድ ይገባዋል።  ስለዚህ የሕዝብ መንግስት እስኪኖረን ድረስ ወደድንም ጠላንም በዚህ ሕገ መንግስት ታስረናል።  ዝም ብለን በዚህ ሕገ መንግስት ደግሞ ወደ ምርጫው እንዳንሄድ የሕዝብ መንግስት ለመመስረት ብቃት አይሰጠንም።  ስለዚህ ቢያንስ ቢያንስ ምርጫውን በተመለከተ ሕገ መንግስቱ ይፈታን ዘንድ ማሻሻያ ማድረግ የግድ ነው።  ይህን የምርጫ ማሻሻያ ለማድረግ ደግሞ ያለው ፓርላማ አሁንም የሕዝብ ስላልሆነ (በሀቀኛ ምርጫ) ውሳኔ ሊያስተላልፍልን አቅም የለውም።  ስለዚህ ሕገ መንግስቱን የማሻሻያ አውድ ሕዝቡ ራሱ እንዲሰጥ የመንግስትን ዓይነት ለመወሰን (ፕሬዚዳንት ወይስ ጠ/ሚኒስቴር) የሚለውን እንዲረዳ ይህን ሪፈረንደም ማድረግ የሕዝብን መንግስት ለመውለድ ተዐማኒነት ይሰጣል። 
 
3ኛ/ ሁሉ አቀፍ መግባባት ወሳኝ ነው
ዶ/ር አብይ እንደ ሽግግር መንግስት ለማገልገል አሁን አይችሉም።  በአሁን ወቅት ተልዕኳቸው የዲሞክራሲ አዋላጅ መሆን ብቻ ነው።  ከአምባገነንነት ወደ ሕዝብ መንግስትነት የሚያሻግረን በመጀመሪያ ምርጫ የሚመሰረተው የሕዝብ መንግስት ነው።  የመጀመሪያ የሕዝብ መንግስት ለወደፊቱ መሰረት የሚጥል፥ ሕገ መንግስቱን ሕዝባዊ የሚያደርግ፥ አሻጋሪ መንግስት ነው።  ስለዚህ የመጀመሪያው ምርጫ ወደፊት ከምናደርጋቸው ምርጫዎች የተለየና ፈር ቀዳጅ ነው።  ስለዚህ ወደዚህ በዓይነቱ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ አዋላጅ ወደሆነው ምርጫ ስንሄድ ከሞላ ጎደል ሁሉ አቀፍ መግባባት መኖር አለበት።  ለምሳሌ ፕሮፌሰር መራራ ምርጫ እንዳይራዘም ሲሉ፥ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ሊራዘምም ይችላል ሲሉ ይታያሉ።  ሁለቱም የተፈተኑ ንፁህ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፥ ልባቸው ለኢትዮጵያ ደህንነት እንዲሆን በማለት ብቻ ይህንን ተቃራኒ አሳብ ያነሳሉ።  ታዲያ ሪፈረንደም በሚደረግበት ጊዜ፥ ለዋናው ምርጫ ግብሃት የሚሆን መረጃ /data/ በሁለቱም ጎራ ለተሰለፉ የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች ይኖራቸዋል።  ሪፈረንደም ሲደረግ የምናየሁ ሁኔታ ምርጫውን ለማድረግ መቼ መቻልን እንደምናገኝ ፍንጭ በመስጠት መግባባት ላይ ያደርሰናል። 
 
4ኛ/ እንከን የለሽ ምርጫ የግድ ነው
ከዚህ በፊት እንደጠቀስኩት የመጀመሪያው ምርጫ የተለየ ነው። እንከን የለሽ መሆን ያለበትና ውዝግብ የማያመጣ ፍፁምነትን የተላበሰ ምርጫ ማካሄድ እንዳለብን ለድርድር አይቀርብም።  ታዲያ ከዚህ በፊት የተደረጉት ምርጫዎች ውሸት ስለነበሩ የምንማርበት ሆነው አይጠቅሙንም።  ሪፈረንደም ብናደርግ ግን፥ ለወሳኙ ምርጫ መማሪያና ወደፊት ምርጫም ሲደረግ እንከን የለሽ እንዲሆን ቀደም ተብሎ ማስተካከያ ለማድረግ ዕድል ይሰጣል።  ሪፈረንደም ማድረጉ ከታለመለት ዓላማ ተጨማሪ ድምፅ የመስጠት ልምድ የምንቀስምበትና ራሳችንን በብቃት ለምርጫ የምናበቃበት አድማስ ያሰፋልናል።
 
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰበ።
ይጎበኛታልም።
Email: Z@myEthiopia.com
0 Comments

IDEALS: Trump vs Abiy

2/3/2019

0 Comments

 
Zelalem Eshete, Ph.D.
 
I never thought there would come a time where would I admire an Ethiopian prime minister over a United States president.  It is a strange time.  President Trump is stripping away inherited ideals that long existed in United States while PM Dr. Abiy Ahmed is instilling ideals in Ethiopia that didn’t exist in the first place.
 
United States is founded upon timeless ideals. Yes, there is prejudice and racism but that doesn’t speak to America as a whole.  Instead, that can be attributed to the fallen state of humanity.  America has been on a journey to enlighten and deal with such ignorance.  That progress is the beauty of America, one victory at a time.  That is why America is an inspiration for the world, and a sanctuary for the persecuted. America’s soul speaks of such priceless identity.
 
Now the president single handedly undermines those ideals to re-invent America and in doing so, he is making America lose her soul. It is an oxymoron for an immigrant president (albeit his ancestors) to turn around and label Mexicans that aspire to come here as drug dealers and criminals.  Ensuring legal immigration through secure borders is a noble thing, but dehumanizing immigrants to sell his agenda by holding the united states hostage is insane. 
 
When the highest office in the land debases the ideals of America, it is an American identity crisis.  Being the super-power of the world or the super-rich of the world is meaningless and short lived unless one can be the super model of the world.  There have been many rises and falls of civilization in history: Axum, Egypt, Athens, Rome, Great Britain.  America is not meant to join this list.  America’s soul dictates that America will keep herself from the fall through wisdom and understanding.  At the time wisdom and understanding is a hard commodity in the White House, we need to look for guidance at the faraway, unlikely place known as a “dark continent” (what the president calls “shit hole countries”).
 
There, we find Ethiopia: grabbing the imagination of not only Ethiopians but Africans and the world at large.  PM Abiy Ahmed espouses regional integration and openness to the world. He champions Ethiopianism within the context of “medemer” (coming together).  His “love wins” philosophy had the power to end the twenty-year hostility with Eritrea, practically overnight.  All political prisoners have been set free.  All parties have put their arms to rest and are roaming Addis Ababa in freedom.  Every morning, the impossible is becoming possible.  There is distinct joy and aura of hope in the air.  What has enabled each of these historic changes is one and the same: the fact that PM Dr. Abiy Ahmed is instilling timeless ideals for Ethiopia. That is what makes or breaks a nation.
0 Comments
    Picture

    Archives

    December 2022
    August 2021
    July 2020
    November 2019
    October 2019
    September 2019
    August 2019
    July 2019
    June 2019
    April 2019
    February 2019
    December 2018
    October 2018
    August 2018
    July 2018
    June 2018
    May 2018
    April 2018
    October 2016

    Categories

    All

    RSS Feed

Copyright © 1999 - 2023
  • ደወል