myEthiopia.com
  • ደወል

የዘላለም እይታዎች 

​በቃ! ይሁን አሜን

7/5/2020

3 Comments

 
ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
 
የኢትዮጵያ ችግር በሰው ሰራሽ ትርክት ኢትዮጵያዊነትን በመሳል ኢትዮጵያውያንን መመረዝና እርስ በርስ ማጫረስ ነው። በዚህም እኩይ ተግባር የተለከፉ፥ ጭራቅ እንኳን ሊሰራው የማይችለውን አሰቃቂ ግድያ ሲፈፅሙ ስናይ፥ የኢትዮጵያዊነት ማንነት የሆነው ፍቅርና ርህራሄ ላይ ያለንን ግንዛቤ እንዳይበርዙብን እንጠንቀቅ።

ምርጥ ልጆቿን መቅበር እስከ መቼ እያልን ስንቆዝም፥ አይ ኢትዮጵያ! እንዳይታረቁ ሆነው የተጠመዱ፥ እንዳይፈታ ሆኖ የተቋጠሩ፥ እንዳይታይ ሆኖ የተሰወሩ ትርክቶች ተመርዛ ሞት እየሸተታት፥ እኛ ዲሞክራሲና ልማት ስንዘፍን ተዘናግተን፥ ፈጣሪ ደረሰልን! ከእንግዲህ መርዙ እስኪነቀል፥ ያልተፈታን ቋጠሮን መፍታት፥ ያልታሰበን አስተሳሰብ ማሰብ፥ ያልተሄደበትን መንገድ መሄድ ሥራችን ይሁን።

የሕዝቡ ማንነት የሚገርም ነው። በመሪዎቻችን ማንነት ሕዝቡ ማንነቱን ተጠልፎ መነጋገሪያ የሆነው የሊሂቃን ትርክትነው። ማን ያውራ ስለደጉ ሕዝብ? ማን ያውራ በፍቅር ስለሚተሳሰበው ሕዝብ?ሲራብ አብልቶ፥ ሲጠማ አጠጥቶ፥ አብሮ ተቻችሎና ተጋብቶ ለዘመናት የሚኖረውና የሚያኖረው ሕዝብ ማንማንነቱን ያራግብለት? ያደከመን በመሪዎቻችን ማንነት ላይ የተመሰረተ የፊት ለፊት ወሬ እያወራን ስጋታችን መብዛቱ ነው። ሁሉም ዓላማውን የሚያራምደው ኢትዮጵያን የመሪዎቻችን ነፀብራቅ አድርጎ በመውሰድ ነው። ከላይ ላይ ከሚታየው ጀርባ፥ የተደበቀውና በጊዜ ተፈትኖ ያለፈው ትልቁ ጥልቅ እውነት ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቤተሰብነት ነው።

እኛ የወለድናቸው ልጆቻችን ለኢትዮጵያ ምን ሊያደርጉ ይቻላሉ ተብሎ ቢታሰብ ከአዕምሮ በላይ ነው። ልጆቻችን የእኛን መባላት ከማየት ይልቅ ፍቅራችንንና ሰላማችንን እንዲያዩ ብንፈቅድላቸው፥እነሱ ለኢትዮጵያ ለመድረስ ይበቃሉ። እኛ ሁሉን አይተን የዕድላችንን ሞክረን አንገት ለአንገት ተያይዘን ከመሬት አልተነሳንም። አሁን ግን ለልጆቻችን ዕድል ፈንታ እንሰጥ ይሆን? ዛሬ አዲስ ጅማሬ አቅቶን ተቸገርን። ነገር ግን ሌላው ቢቀር ነገ ልጆቻችን ኢትዮጵያን ሳትሰነጣጠቅ ማስረከብ እንኳን ብንችል፥ እነርሱ አዲስን ነገር ያሳዩን ነበር። ታዲያ ካለንበት አዘቅት ለመውጣት መተባበር አቅቶን ይህችን ኢትዮጵያ ሀገር እንዳትሆን እያደረግናት ይሆንን? እንዲያው አምሳአመት እንኳን ወስዶብን ከድሮ የተለየ አሰራርና አስተሳሰብ ለማሳየት ችለናልን? እንዲያው ይህችን ሀገር አጥፍተን ካልጠፋን አንነቃምን? ልጆችን የራሳቸው እድል እንዳይሞክሩበት መና ልናስቀራቸው ነውን? 

ኢትዮጵያ የሕዝቡ ውጤት እንጂ የመንግስታት ፍሬ አይደለችም። መንግስት ይመጣል፥ እንደመጣም ይሄዳል። ቋሚ ነገር ሕዝቡ ነው። እውነተኛውና የሚፀናውን ኢትዮጵያዊነት የሚያረጋግጠው ሕዝብ ነው። የኢትዮጵያ ጠባቂ ሕዝብ ነው። ኢትዮጵያ ሕዝቡን ስለሚወክል በራሱ እፁብ ድንቅ ነው። ሕዝቡ የኢትዮጵያን የነገውን እጣ ፈንታ ይወስናል። ማንም ኢትዮጵያን ለማወቅ ሩቅ አይሂድ፥ እናቱን ይመልከት (ከአብራኳ ወጥቷልና)። ኢትዮጵያ ላይ ቆሞ፥ ኢትዮጵያን የሚያፈርስ መርዝ እየረጩ፥ ስለ ኢትዮጵያ መፃኢ ዕድልና ፈንታ ማውራት የዲሞክራሲ መብት መጠቀም ሳይሆን፥ ሕግ አልባ በሆነ “ሀገር” መንደላቀቅ እንደሆነ የሚታወቅበት ጊዜ ያመጣ ፈጣሪ ምስጋና ይግባው።  

መሰሪዎችየሳሉልንን ትርክትይዘን ሰጣ ገባ ስንገባና ኢትዮጵያን ጥያቄ ውስጥ ስናስገባ፥ እውነተኛውን ኢትዮጵያዊነት ለመቀበል እድልና ፈንታ እንዳይኖረን እያደረገን ነው። ይህንንም ስናደርግ ኢትዮጵያን ጥያቄ ውስጥ ማስገባታችን፥ሕዝቡን ራሱን ጥያቄ ውስጥ ማስገባታችን እንደሆነ ስለማናስተውል ነው። ለዚህም ስህተት የሚዳርገን፥ መሰሪዎቹ ትርክታችንንየሚመሰርቱትመንግስታት ባደረጉት ድርጊት ላይ የሚስሉልንንኢትዮጵያን ተመርኩዘን ስለሆነ ነው። ይህን ስናደርግ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከሕዝቡ ነጥለን መንግስታትን የኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያ ፈጣሪ አድርገን መፈረጃችን እንደሆነ ይታወቅ። ይህን በማድረጋችን፥ ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያዊነትሕዝቡ ያለውን አብሮነት ዋናውን ስፍራ አለመስጠት ይሆንብናል። የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ፅናት ግን የሕዝቡ ውጤት ነውና ሕዝብ እስካለ ድረስ ለዘላለም ፀንቶ ይኖራል። እውነተኛው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ሊሂቃንበራሳቸው ዕይታ የሚስሉት ማንነት አይደለም። በራሱ በሕዝቡ የተገነባ ከመንግስታት ተነጥሎ በራሱ የቆመ ማንነት ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ፈተና ላይ ጥሎ፥ የጥላቻና ዘረኝነት መርዝ እያጠጡ፥ በዲሞክራሲ ስምኢትዮጵያን የመግደልዘመቻ ተነቃ። 

እውነተኛው ኢትዮጵያዊነት እኛ ወይም ሌላው በፍልስፍና የሚፈጥረው ነገር ሳይሆን፥ ራሳችንን (ሕዝቡን ማንነቱን) የሚተርክ እውነታ ነው። ያም የተዋበና የሚገርም ነው። እውነታው ስለ ሕዝቡ ይናገራል። የኛ ጥረት የሊሂቃንን መነፅር ከአይናችን ላይ አውልቀን የሕዝቡን ውበት እንደ ነበረና እንዳለ መመልከት መቻል ላይ ነው። ያኔ የተሰወረውን እውነተኛውን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማወቅና ለማሳወቅ ይቻለናል።

እውነተኛውን ኢትዮጵያዊነትን ለመተዋወቅ ከሕዝቡ እንጀምር። ሕዝቡ እውነተኛ ቅንና በጎ ነው። በጎና መልካም የሆነው ይህ ሕዝብ ማንነቱን ለማንፀባረቅና እርሱነቱን ለማብራት ያልቻለበት ሁኔታ ውስጥ ነው ለዘመናት ያለው። ኢትዮጵያዊነትን ከሕዝቡ ስብዕና ላይ ተመርኩዘን ለማወቅ ብንጥር ቤተሰብነትን ያሳየናል። ስለዚህ ጥረታችንና ሕልማችን ይህንን እውነተኛውን ማንነታችንን ለማወቅ ይሁን። ልዩነታችን ውበታችን ሆኖ ይታየን። እኩልነት የእውነተኛ ኢትዮጵያዊነት ስርና መሰረት እንደሆነ ይታወቀን። ራዕያችን እንደሆነው እንድንታወቅ ይሁን። እንደ ማንነታችን ሁሉ አቅማችንም ያንን ያህል ታላቅ መሆኑ ይግባንና ለካ ምንም አልሰራንም ብለን እንቆጭ። በዚህም ቁጭት እውነተኛውን ራሳችንን ማሳወቅ ብቻ ሳይሆን እውነተኛው አቅማችንንም መግለጥ ይብዛልን።

እስቲ የራሳችንን እውነተኛውን ማንነት ማወቅና መረዳትን እናስቀድም። የቤት ስራችን ኢትዮጵያዊነትን ማፍረስ ሳይሆን ያልተገለጠልንን እውነተኛውን ኢትዮጵያዊነትን ማስተዋል ላይ ያተኩር።መሰሪዎችየሚስሉት ኢትዮጵያዊነት ላይ ተወስነን ኢትዮጵያዊነትን አንኮንን። ይልቁንም በሕዝቡ ልብ የተሰወረውንና በየዕለት ኑሮው የሚተገበረውን ኢትዮጵያዊነት ከሽፋኑ አውጥተን ለዓለም ለማሳየት እንጣር። ፍርሃት ሳይሆን ፍቅር የሚገዛው እውነተኛውን ኢትዮጵያዊነት እናውጅ። አለመተማመን የሚነዳንና የሚያናቁረን እንዳይሆን እውነተኛውን ኢትዮጵያዊነትን ማወቅ ቤተሰብነታችንን አስረድቶን አዲስ ምዕራፍ ይክፈትልን። ቁምነገሩ ኢትዮጵያዊ ለመሆን የምንጥር ሳንሆን፥ ኢትዮጵያዊ ስለሆንን ያንን የማወቅ ጉዞ ላይ መሆናችንን ማስተዋል ላይ ነው። የሆንነውን ሆነን ለመገኘትና የተሰወረውን እውነተኛውን ኢትዮጵያዊነት በገሃድ ለመግለጥ ራሳችንን እናነሳሳ።

የኢትዮጵያ አንድነት የሚመነዘረው በሕዝቡ አንድነት እንጂበሊሂቃን ተብየዎች አይደለም። እርስ በርስ መያያዛችን ከራሳችን ከውስጥ የመነጨ ነው እንጂ ከውጭ ሌላው የሚጭንብን መከናወን አይደለም። መሰሪዎችበኢትዮጵያዊነት ላይ የጣሉትን ሽፋን ገልጠን፥ እውነተኛውን ኢትዮጵያዊነት በማንፀባረቅ እንደ ሆንነው በዚያኑ እንድንታወቅ ራዕያችን ይሁን። ያም ለዓለም ድንቅና መገረም እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ሀቅ ነው። ስለዚህ በኢትዮጵያዊነት ላይ ጎራ ይዘን ከምንተራመስ፥ እውነተኛውን ኢትዮጵያዊነት ከሕዝቡ የምንማርበትን ሂደት ላይ ግድ ቢለን መልካም ይሆንልናል። ይህ ቢበዛልን፥ የአፍሪካ ኩራት የሆነችው ኢትዮጵያ የዓለም ተስፋ እንድትሆን በር ይከፍትላታል። ስለ አንድ ኢትዮጵያ ከመጨቃጨቅ አልፈን ስለ አንድ አፍሪካ ፈር ቀዳጆች ለመሆን እንድንታደልምያደርጋል። 

የኢትዮጵያ ነገር እንቆቅልሿ የሚከብደው ጉዳዩ የውስጥ ብቻ ስላልሆነ ነው። ለሁሉ ነገር ወዳጅና ጠላት እንዳለ ሁሉ፥ ኢትዮጵያም ወዳጅና ጠላት አላት። አሻፈረኝ ብላ የጥቁር ሕዝብ ተስፋና ኩራት መሆኗን የሚያደንቁ እንዳሉ ሁሉ ነርቫቸውን የሚነካም አይጠፋም። የብዙዎች መተዳደሪያ የሆነው የውሃ ስርና መሰረት ጥንስሱ አባይ ከኢትዮጵያ ስለሚነሳ በዓይነ ቁራኛ መታየቷ አይቀሬ ነው። በዙሪያዋ እየተተራመሱ በመካከል እንደ ወጥ ቁጭ ብላ በእድገት ልትመነጠቅ የምትንደረደር ኢትዮጵያን ማየት የማይመቻቸው ይኖራሉ። በተለይ ሽብርተኛውን ከአሜሪካ ጋር እየተባበረች በአካባቢዋ አከርካሪ ሰባሪ መሆኗ ጥቁር ነጥብ በጠላቶች ዘንድ ማስጣሉ አይቀርም። ምዕራቡ ዓለም ከእጅ ወደ አፍ እርዳታ እያደረገ ለዘመናት ኖሮ ሳለ ዛሬ ቻይና በኢኮኖሚው ላይ ጫና ያለው የመሰረታዊ ልማት እንቅስቃሴ እንድታደርግ በተደረገውም ስራ ኢትዮጵያ ከተኛችበት የተነሳች እስክትመስል የሚታይበት ሁኔታ ሌላ ጠላትነት የሚያፈራ ሊሆን ይችላል። ይህ እንግዲህ በውስጥ በራሳችን ልጆች ከሚመጣው አለመግባባት መዘዝ ከሚደረገው የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው አካሄድ ጋር ሲደመር ነው ቋጠሮዋ የሚጠብቀው። 

የኢትዮጵያ ቋጠሮ ባለን ሁኔታና በሚጠብቀን ዕድል መካከል ያለው ውጥረት ነው። ያለንበት ስፍራና ልንሆንበት የሚጠራን ከፍታ አይገናኙም። በአንድ ዓይነት ሃይማኖትና በአንድ አይነት ብሔር የተዋቀረችው ሶማሊያ ከመፈራረስ አንድ አይነት መሆኗ አላዳናትም። አሜሪካ በሌላ በኩል ከዓለም ዘር ሁሉ የተውጣጡ ሕዝቦችን ይዛ በእግዚአብሔር ስር ያለ አንድ ሕዝብ ያውም ሊከፋፈል የማይችል በማለት ይምላሉ። ልዩነትን አስተናግደው ከዓለም የሚያስንቅ ዲሞክራሲን ለማራመድ ችለዋል። ይህ ሁሉ የሚያሳየን እንደ ትልቅ ነገር ይዘን የምንቆራቆስበት ትርክቶችከመጠላለፍ ያለፈ ያደረገልን ነገር የለም። 

ሕገመንግስታችን የትላንትን ፍርሃት የሚናገር እንጂ የነገን ራዕይ የሚያውጅ አይደለም። ትላንት ስለተበዳደልን ዛሬ እስከ መገንጠል የሚል መብት አስቀመጥን። የምንተነብየው ያ ነገር ይሆናል። ዛሬ ላይ ቆመን ነገን ስናይ ምን ይታየናል? ፍርሃታችን ሳይሆን ተስፋችን እንዲመራን ለምን አላረግንም? አንድ ሕዝብ ተብለን የሕዝቦች መብት አለመጠበቁን ለማስመር ሕዝቦች ብለን ለምን እንደመድማለን? ለመሆኑ ተጋብተን ተዋልደን የኖርን አይደለምን? መሬት ታች አውርደን ካየን እንደ ወንድምና እህት ተከባብረን ስንቱን አብረን አሳለፍን? ደግነት እና ትህትናችን ለምን ዋጋ አጣ? አብረን ደምተን ዳር ድንበር አስጠብቀን፥ እስላምና ክርስቲያን ተባብለን ሳንገፋፋ አብረን ስንቱን አሳለፍን? መንግስታት ሲቀያየሩብን ድህነት እና ችግርን እርስ በርስ ባንረዳዳ እዚህ እንደርስ ነበር ወይ? ሲሆን ሲሆን ኢትዮጵያ አንድ ሕዝብ ናት ማለቱ ራሱ ስህተት ነው። ምክንያቱም አንድ ቤተሰብ ነንና።

ብዙ ሰው መላ ሲሰጥ ይታያል። ያ መላ መልካም ሆኖ ሳለ፥ ጆሮ ሰሚ ሳያገኝ በግራና በቀኝ መንገድ ላይ ወድቆ ባከነ። ችግራችን የመፍትሔእጦት አይደለም። የመግባባት መተላለፍ እንጂ። ስለዚህ መግባባትን ከመጨረሻው ላይ ቆመን ከመፍትሔው ጎራ ከመፈለግ፥ ግና ከመጀመሪያው ከችግሩ ጥንስስ ላይ ቆመን የችግሩን ስም በማውጣት ላይ እንስማማ። የችግራችንን ስም ሁላችንም የተስማማንበትን ስም አውጥተን ስናበቃ፥ያ የችግሩ ግንዛቤ መግባባት አንድ ቋንቋ ይሰጠናል። ያኔ ችግሩ ላይ ከተስማማን ሁላችንም ከአንድ ስፍራ እንጀምራለን ማለት ነው። በአንድ ስፍራ ለመሆናችን ምክንያቱ መላ ስላገኘን ሳይሆን ቋጠሮውን በአዲስ ግንዛቤ ስለገነባነው ነው። ያኔ ሁላችንም ቋጠሮውን ለመፍታትከአንድ ስፍራ ስለምንነሳ ወደ አንድ አቅጣጫ ለመሳተፍ ይቀላል። 
​
ኢትዮጵያ የታሪክ እስረኛ አይደለችም። ምክንያቱም ከታሪክ ተምረን አዲስን አቅጣጫ ለነገ ዛሬ መተለም ይቻለናልና። ይልቅስ መርዝ ሆኖ የተቀመመው ሰው ሰራሽ ትርክት ላይ የተጠመደው ቤተሰብነታችንን የሚንድ የኢትዮጵያ በሽታ ነው። ሁላችንም ለዶ/ር አብይ በፀሎትና በሥራ አጋርነታችንን በቃ! ይሁን አሜን ብለን እንደግፈው።
3 Comments
Betty
7/6/2020 12:03:49 pm

Well said, and true that there’s beauty amongst our people and we’re not a slave to history but make a better one for our children.
Thanks,
Betty

Reply
Berhanu Mengistu
7/6/2020 01:07:49 pm

Excellent timely piece.
Thanks for sharing and I hope and 🙏 that those who want power at expense anything including the killing of our family members to reconsider their respective positions.
The life of any one and everyone matters!

Reply
Kedest
7/7/2020 06:08:40 pm

Well said, keep educating us! The silence of many Ethiopians on today's matter is hurting our country! Silence is compliance!

Thank you!

Reply



Leave a Reply.

    Picture

    Archives

    December 2022
    August 2021
    July 2020
    November 2019
    October 2019
    September 2019
    August 2019
    July 2019
    June 2019
    April 2019
    February 2019
    December 2018
    October 2018
    August 2018
    July 2018
    June 2018
    May 2018
    April 2018
    October 2016

    Categories

    All

    RSS Feed

Copyright © 1999 - 2023
  • ደወል