myEthiopia.com
  • ደወል

የዘላለም እይታዎች 

የሞት ሽረት ማኒፌስቶ

11/2/2019

0 Comments

 
ዶ/ር ዘላለም እሸቴ

ተፃፈ በእምዬ ኢትዮጵያ ስም።  አስተዋይ ያስተውል።
​
ያልሰራናትን ኢትዮጵያ ስንናፍቅ ጉድ ሆነናል። የራሳችንን ድርሻ መወጣታችንን ከማየት እንጀምር። ብዙሃን ዝምተኛው ኢትዮጵያዊ (silent majority) ፖለቲካው ቆሻሻ ሆኖበት ቁጭ ብሎ፥ ጥቂት በፖለቲካው ያረጁና ያፈጁ ፖለቲከኞች ራሳቸውን ሰውተው፥ አቡክተውና ጋግረው የሚያመጡልንን ኢትዮጵያ 50 ዓመታት ሙሉ ስናይኖረናል። ሁላችንም ያገራችን ነገር እየከነከነን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ እነዚህ ፖለቲከኞች ጋግረው ያመጡልንን ኢትዮጵያ አልመች ብሎን፥አንዱን ስናሞግስና ሌላውን ደግሞ ስንሰድብ ሰንብተናል። ከዓመት ዓመት ይህንኑ ስናደርግ፥ ዓይናችን እያየ፥ ኢትዮጵያ ከኮማወደ ሞት ዝቅ እያለች እየሄደች ነው። ይህ አካሄድ ታሪክ ብቻ ሆኖ መቅረት አለበት። ዛሬ! 

የፖለቲካ ፓርቲ አባልና ተሳታፊ መሆንን ሁላችንም የውዴታ ግዴታማድረግ አለብን። ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፥ሁላችንም በፖለቲካ ድርጅቶች ታቅፈን መደራጀትና ትግሉን በቃልና በሥራ መቀላቀል አሁን አሁን የግድ ነው። ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሆነ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሳይሆን፥ስለ ኢትዮጵያ ግድ ብሎት ማውራት እንደ ነውረኛ የሚያስቆጥር ባህልን በህብረተሰባችን ይፈጠር። ለኢትዮጵያ የሚሰራ በዝቶ፥ ቁጭ በይ ወሬኛ ይጠፋ ዘንድ አንዳችን ሌላኛውን እንዳደፋፍር። ፖለቲካ ኤሌክትሪክ/ቅጥፈት ነው የሚል ትርክትን አፍርሰን፥ ፖለቲካ የዜግነትና የክብር ግዴታ ነው በማለት ይተካ። ይቻላል!

አዲስ ፓርቲ መመስረት፥ ወይም ሁሉንም ጨፍልቆ አንድ ማድረግ ጊዜው ያለፈበት ጉዳይ ነው። ሁሉም የየራሱን ፓርቲና አደራጃጀት ይዞ፥ ነገር ግን በአንድ ኢትዮጵያዊነት (ሰው መሆንኛ) ፍልስፍና ጥላ ስር ግንባር ፈጥረን፥ ሁነኛ አማራጭ ሆኖ መቅረብ ለኢትዮጵያ ከሞት ማምለጫ ብቸኛ መንገድ መሆኑ ግን አሁን ላይ ፍንትው ብሎ በራ። ሁሉም እኔ እኔ እያለ በሚወዳደርበት አውድ ውስጥ፥ የሁሉም እኔነት (ego)እንቅፋት በማይሆንበት ሁኔታ፥ በጥበብ ይህንንየአማራጭ ግንባር ሰብሳቢ እንዴት ወደ ብርሃን ማምጣት እንደምንችል እጠቁማለሁ።

ከየት እንጀምር የሚለውን ጥያቄ ለመፍታት ታስቦ የሚደረግ ጥሪ ይህ ነው።  እኔነትን (ego) እንቅፋት እንዳይሆን ጅማሬውን ታናሽ ማድረግና ከዚህ በፊት አምላክ ከሰራው ታሪክ ትምህርት መውሰድ ያስፈልጋል።  “ቀጣዩ አሻጋሪ” ማን ይሁን ብለን ባለመግባባት ከምንለያይ፥ በመጀመሪያ “ቲም ኢትዮጵያን” ለመውለድ እንሞክር። ከዚህ “ቲም ኢትዮጵያ” ወደፊት አማራጭ ግንባሩንና ሰብሳቢውን (ቀጣዩ አሻጋሪ) በጊዜ ሂደት የሚታወቁ ይሆናል።  ያም “ቀጣዩ አሻጋሪ” ለአማራጭ ግንባሩ ሰብሳቢ ይሆናል ማለት ነው።  የሚቀጥለው ጥያቄ ይህ “ቲም ኢትዮጵያ” እንዴት ይወለድ የሚል ነው።  አሁንም ከአንድ ሰው መጀመር ይቀላል።  እያወራን እርስ በርስ ስንፈራራና ሳንተማመን መንገድ ላይ እንዳንቀር መላው ምንድነው? ፅሁፍ እየፃፍንና ፅሁፍ እናነበብን እንዲሁ ሜዳ እንዳንቀር ብልሃት ያስፈልገናል።  ከምንራቆሰው ብሄር ውጭ የሆነና፥ በኢትዮጵያዊነት ላይ እንደ ወርቅ ተፈትኖ የነጠረ ከመካከላችን፥ ከኢሕአዴግ መንግስት ውጭ የሆነ ማነው?  እኔ ይህ ሰው ኦባንግ ሜቶ ይመስለኛል። እኔ ከ ኦባንግ ሜቶ ድርጅት ጋር ምንም ግኑኝነት የለኝም። ከእርሱም ጋር አልተነጋገርኩም።  እኔ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በፖለቲካ ያልተሳተፍኩና ለእርቅና መግባባት ከመሞገት ውጭ ማንንም የማላውቅ ታናሽ ሰው ነኝ። ኦባንግ ሜቶ ከፖለቲካው ውጭ ሆኖ ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚያቀነቅን እንደሆነ አያለሁ።  በተጨማሪ ደግሞ ከኦባንግ ሜቶ ብንጀምር፤ ከእርሱ የተሻለ ኢትዮጵያዊ አለ የሚል ሰው ቢኖር እንኳን፥ ኦባንግ ሜቶ ራሱ ችቦውን ለማስተላለፍ ብቃት ያለው ስብዕና ይኖረዋል ብዬ መገመት እመርጣለሁ። ቁምነገሩ ጊዜ የለንም። እጅግ አስቸኳይ ጉዳይ ስለሆነ ብቻ የመጣደፍ ጭንቀት እንዳለብኝ ታይቶ ስህተተኛ ከሆንኩም ይቅርታ ይደረግልኝ። ይህንን ሀሳብ በንፁህ ሂሊና ተወስዶልኝ፥ ከማውራት ለመላቀቅ የተደረገ ጥረት ተደርጎ እንዲወሰድና ማስተካከያ ይሰጥበት ዘንድ አደራ እላለሁ።  ብሳሳትም፥ በሞት እና በሕይወት መካከል ላለችው እናት ሀገር ሞኝ ተደርጌ ብቆጠርም ክብር ነው እላለሁ። ታዋቂ ሰው ስላልሆንኩ፥ ይህ ሀሳብ ፍሬ የሚያፈራው በተዐምር ፈጣሪ እጁን ጣልቃ ካገባበት ብቻ ነው።  ስለዚሁ ጉዳይ ምክርዎን በዚህ ኢሜል ይላኩልኝ። 
ኢሜል፡   ethioWins@gmail.com 

የመጀመሪያውን አሻጋሪ ለቀቅ፥ ቀጣዮን አሻጋሪ ጠበቅ
ምስጢሩ ሁለት አሻጋሪ እንደሚያስፈልገን ማስተዋል ነው። ነፃ አውጭ ሙሴው ዶ/ር ዐብይ ከባርነት ቀንበር የ “ኤርትራን ባህር” አሻግሮጥሪውን በዲሞክራሲ አዋላጅነትለማጠናቀቅ ሲጥር፥ እኛ በምድረ በዳ እንዳንቀር፥ የ “ዩርዳኖስን ባህር” አሻግሮ ወደ ተሰፋይቱ ኢትዮጵያዊነት ምድርየሚያስገባን፥ ከዶ/ር ዐብይ ትይዮ የሚሰለፍና አማራጭ ግንባሩን የሚመራ “ኢያሱ” እንዲወጣ ሁላችንም አንድ ልብ እንዲሰጠን ፀሎቴ ነው። እግዚአብሔር ዐብይን ለኢትዮጵያ ሰጠ። አሁን አምላክ ከእኛ የሚፈልገውየኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ አንድ ሆነው ቀጣዩ አሻጋሪእንዲገለጥመተባበር መቻል ነው። ዐብይን የሚያምነው ሰው፥ እውነት ዐብይን ከወደደ፥ ለ “ቀጣዩ አሻጋሪ” መገለጥ ይስራና፥ ዐብይ የሚወዳትን ኢትዮጵያን ይርዳ። ዐብይን የሚጠረጥረው ሰው፥ እውነት ኢትዮጵያን ከወደደ ለ “ቀጣዩ አሻጋሪ” መገለጥ ይስራና የሚወዳትን ኢትዮጵያን ይርዳ። ዶ/ር ዐብይ ላይ ብቻ ተጠምዶ ሰው ቁጭ ካለ፥ በምድረ በዳ አልቆ፥ የእስራኤልን ታሪክ ዳግመኛ በራሳችን ላይ እንዳንደግም እንፍራ! አሁን አሁን ዶክተር ዐብይ መደገፍም ሆን መቃወም አይጠቅማቸውም። አይጠቅመንምም። ይልቁንስ እንልቀቃቸውናበራሳችን ሥራ እንጠመድ።ያኔ ጠቅላይ ሚኒስቴሩም ጉልበት አግኝተው በበጎነት ይገለጣሉ እንጂ ክፉ ሆነው ክፉ አያደርጉም።

ዶ/ር ዐብይ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ናቸው ብለው ምንም እንከን በሳቸው ላይ ላለመመዝገብ የተገዘቱ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ዶ/ር ዐብይ አስመሳይ መሰሪ ናቸው ብለው የሚምሉና ፍርድ ቤት የቀረቡ ይመስል፥ የማስረጃ ትንታኔ ላይ ተጠምደው ጊዜያቸውን ያቃጥላሉ። የተለመደው የፖለቲካ ጥበባችን የሚመክረን እውነታዎች በሁለቱ አካሄድ በኩል እየፈረጀን እስከመቼ እንደሚሸውደን አላውቅም። ብናስተውል በዚህ ሰሞን የተከሰተው የጃዋር ግርግር፥ ለኢትዮጵያ ታላቅ አዘን ቢያስከትልም፥ የፈሰሰው ደም ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር ከፈለግን፥ ከዚህ ሰቅጣጭ ሀዘን ውስጥ በሁለት ጎራ ተከፍለንየምንሞግትዶ/ር ዐብይ ተኮር ዜጎች (ተቃዋሚና ደጋፊ)፥ ዶክተሩን ለቀቅ አድርገንናበህብረት ሆነን ለአንድ ዓላማወደ ሥራ እንግባእላለሁ።

ኢትዮጵያዊነት ስለተሰበከ ሀገር ሁሉ በፍቅርና በተስፋ እንደተነቃነቀ አምና አይተናል። ግን ምን ያደርጋል ከተበታተነ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ይልቅ፥ በወደቀራዕይና ዓላማ አንድነትን የፈጠረ ድርጅትየበለጥ ሃይል ኖሮት ለእርስ በርስ እርድ እያዘጋጀን ይገኛል። ግና!

በሺዎች ዓመታት እንደ አልማዝ ተፈትኖ ነጥሮ የወጣው ኢትዮጵያዊነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ራዕይ ጥላ ስር ተሰባስበን፥ አንድ ሁነኛ አማራጭ ግንባር የምንፈጥርበት ቀን ደረሰ።ኢሕአዴግ የተለያየ ፓርቲዎችን በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ጠፍሮናግንባር ፈጥሮ 27 ዓመት ሲነግስ አይተን ስናበቃ፥ ዛሬ ደግሞ ይህ ኢሕአዴግ የተለያየ ፓርቲዎችን በመደመር ንግግር ጠፍሮናግንባር (ውህደት) ፈጥሮ ሌላ 27 ዓመት ሊገዛ ሲደራጅ፥ በትናንሽ ራዕይና በተበታተነ ፓርቲዎች እርስ በርስ ፉክቻ መዳከር ሊያበቃ ነው።ዝምተኛው ብዙሃን ኢትዮጵያዊ ዶ/ር ዐብይን በመደገፍና በመቃወም እየተዋከበ፥የኢትዮጵያን ትንሣኤ በምትሃትይመጣል ብሎመጠበቅ ሊቀር ነው ከእንግዲህ።

ሌላው ቀርቶ ኢሕአዴግ አጋር ፓርቲዎች እያለ ለዘመናት የሚያላግጥባቸውን፥ዛሬ ዛሬ ሊያቅፋቸው ላይ ታች ሲል፥ ይህ አማራጭ ግንባር ዕውን ሆኖ እነዚሁኑ የተገፉ ሕዝቦች ለአባልነት ይጋበዛሉ።  አሮጌ ነገር እያረጉ አዲስ ነገር መጠበቅ የሰለቸን ጊዜ ላይ ደርሰናልና እንንቃ! ዶ/ር ዐብይን የሽግግር መንግስት ምናምን እያልንበመግለጫና በጥያቄ ከምናዋክባቸው፥ዶክተሩን ለቀቅ አድርገን፥እኛ “የሽግግር” አማራጭ ግንባር ለውድድር እንዲቀርብ የምንፈጥርበት ወቅት ይሁን።ኢሕአዴግ በፌድራሊዝም አግባብ ሲጣሉ፥ እኛ በኢትዮጵያዊነት ላይ የተገነባውንና ፍፁምነት ጭምር የተላበሰውን“ኢትዮጵያዊ ፌድራሊዝምን”እናስተዋውቃለን።ጠቅላይ ሚኒስቴሩን እንዲህና እንዲህ አድርጉ እያልን አዳዲስ አሳቦችን እንዲቀበሉን መወትወት ትተን፥ ያንኑ አዳዲስ ሀሳቦች በራሳችን ላይ አውለን አማራጭ ግንባር ሆነን እንገለጣለን። 

እርማችንን እናውጣና ሀቁን እንቀበል 
እስቲ ሀገራችንንከማየት እንጀምር። ሀገራችንጃንሆይ ያስራቧት፥ ደርግ ያቆሰላትና ኢሕአዴግ ኮማ ውስጥ የከተታት እምዬ ናት። ጠላቶቿ ግባ መሬቷን ከአሁን አሁን አየን እያሉ ቢጠብቁም፥ ፈጣሪ ከእሷ ጋር ጉዳይ አለውና ይሄው ኢትዮጵያ እየተባለች ስሟ ከመጠራት እስካሁን አልቀረም። ምድረ በዳ ሆና ባንዲራዋ በሰማይ የሚታይ ሆናለች። ሰው የዶክተር ዐብይን ልብ ለማወቅ ይመራመራል።  የትኛውም ልብ ይኑራቸው አሁን ያለችሁን የኮማ ኢትዮጵያ ነፍስ ሊዘሩ አይችሉም። ይመስለናል እንጂ ማንም አይችልም።ወደድንም ጠላን ኢትዮጵያ በሰው እጅ ሥራ እንዳንታሰራራ ተደርጎ በኮማ ውስጥ እንድትገባ ተደርጋለች። እርማችንን እናውጣና ይህን ሀቅ ማለትም በሰው እንደማይቻል እንቀበል።ምክንያቱም ያሳለፍነው ጉድ ከሰውነት አውጥቶን እንደ ባለ አእምሮ ማሰብ እንዳንችል አድርጎናል። ሀገሪቱን የሚዘውሩት ሊሂቃን ተብዬዎች ሁሉ፥ ሁሌ ጥል ላይ ያለንና ሁከት ውስጥ የምንዋኝ ያልታወቀልን “እብዶች” ነን። በደመ ነፍስ የምንመላለስ ሆነናል። መርገም ይዘን በረከት እንዲወርድልን ስንባዝን ከርመናል። ንፁህና ትልቅ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በእኛ ዳተኝነት ታግቶ፥ መጨረሻዬ ምን ይሆን ብሎ ጉዳችንን ከማየት ያለፈ ነገር ማድረግ እንዳይችል ሆኖ በስጋት ተቀምጧል።  

​ልብ እንግዛና የኢትዮጵያን አምላክ ከማየት እንጀምር። የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋው ፈጣሪ እንደሆነ እሙን ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ቤተሰብ እንደሆነ እውነትነው። ነገር ግን ባለፈው 50 ዓመታት የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚዘውሩት አምላክን ዜሮ እንዳረጉት የአደባባይ ሚስጢር ነው። በእጃቸው ያለው ደምና በልባቸው ያለው መከፋፋት አምላክን ለረድኤቱ እንዳይጠሩ እንቅፋት ሆኖባቸዋል። ያለፈውን በደልና ቁርሾ ማውራትና በቁስል ላይ እንጨት መስደድ እንጂ፥ በአምላክ ፍቅርና ረድኤት በይቅርታ ያለፈውን ፋይል ዘግቶ መፈወስ እንዳለ አይታሰብም። የጎሳውን ወገን “ወንድማችን” ይላል እንጂ፥ መላው ኢትዮጵያዊ ወንድሙ እንደሆነ ዘንግቶ፥ በወንድማማች መካከል ጠብ መዝራት ፋሽን ነው። እርግማን ተይዞ በረከት መጠበቅ ሞኝነት ነው። የበረከትን ምንጭ የሆነው አምላክ ተንቆና ገሸሽ ተደርጎ፥ መድሃኒት እንዲመጣ መልፋት ባዶነት ነው።

እንዲሳካልንና ምድራችን የተዐምር ምድር እንድትሆን ከፈለግን፥ እኛ ከቁጥር የማናስገባውን የኢትዮጵያ አምላክ ሕዝቡ ታምኖበታልና፥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘወትር እንደሚያደርገው ሁሉ እኛም ራሳችንን ዝቅ ማድረግ ያስፈልገናል። ለሰው የማይቻል ለፈጣሪ ይቻላልና። ሁላችንም በመመለስየኢትዮጵያን አምላክ የኢትዮጵያ ንጉሥ እንዲሆን በአደባባይ ለሁሉ እናውጅ። ያኔ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች የሚለው ትንቢት እውነት ይሆናል። የአሜሪካ አባቶች እግዚአብሔር ላይ ተደግፈው የእግዚአብሔርን ስም በዶላራቸውና በሳንቲሞቻቸው ላይና በብሄራዊ መሀላቸው ውስጥ አስገብተው ፈጣሪን ሲያከብሩ፥ እነሆ የዓለም ንጉስ ሆነው አረፉት። የሚያሳዝነው ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ፥ መሪዎቹበፈጣሪ የሚያፍሩመሆናቸውነው። የፈጣሪ በረከትና ረድኤት እንዲደርሰን የፖለቲካ መሪዎቻችን ራሳቸውን ከማማው ላይ አውርደው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚታመንበትን ፈጣሪ ከፍ እንዲል ያድርጉ።  አምላክን በንግግር መጨረሻ ላይ ጣል የምናደርገው ብቻ ሳይሆን፥ አማራጭ እንዲሆን በሕብረት የምንፈጥረው ግንባርየአምላክን ረድኤት እንደ ዋና መሪ ቃል ማስቀመጥአለበት። አምላክን የምንማፀነው፥ የሃይማኖት ጉዳይ ስለሆነ ሳይሆን (ሃይማኖት የግል ነው)፥ ያለ ፈጣሪ ረድኤት የኢትዮጵያ ትንሳኤፍፁም በሰው ሃይል እንደማይሳካ ከልብ ስለገባን መሆን አለበት። ይህ ድርጊት ደግሞ መድሃኒትነቱ በእኛ ብቻ የሚወሰን አይደለም።  ለምሳሌ መሪ ቃላችን፥ “ፈጣሪ ኢትዮጵያን አስባት” ብለን ብንነሳ፥ አምላክ ይህንን ለምልክት አድርጎት የሚባርከን እኛን ብቻ ሳይሆን፥ እኛን ለዓለም በረከት በማድረግ ምድርን ሁሉ በክብሩ ይሞላል።

በቸልተኝነት አይለፍብን፥ ይልቁንስጊዜውን ከማየት እንጀምር። በአብዮትትርምስ ውስጥ የነበረ ትውልድ በሞት አልቆ አዲስ ትውልድ ሊመጣ ያለበት አፋፍ ላይ ደርሰናል። ከጥቂት ዓመታት በሁዋላ የጃንሆይ ጊዜ ግርግርን የሚያውቅ ሰው በሕይወት የሌለበት ዘመን ሩቅ አይደለም። ባለፉት አምሳ ዓመታት ስለነበረው ቀውስ ሂሳብ በይቅርታ ዘግተን፥ አዲሱን ትውልድ መክረንና መርቀን፥ የኢትዮጵያን አይቀሬ ታላቅነት በጭላንጭል አይተን፥ ወደማንመለስበት ሞት ኢትዮጵያን ተሰናብተን በእፎይታ እንድንሄድ ፈጣሪ ምህረት እንዳደረገልን ስለ ጊዜው ምንነት ማወቅ ተስፋ ሰጭ ነው። 

ጊዜው በጠላታችን ሤራ ኢትዮጵያ እንድትጠፋ ቀጠሮ የተያዘበት ብቻ ሳይሆን፥ በይበልጥ ጊዜው ለውድ እናት ሀገራችን ልዩ የመዳን ቀን ለመሆኑምልክቱ ብዙ ነው። አብዮት ሳይፈነዳ በለውጥ ጉዞ ላይ መሆናችንመለኮታዊ እጅ እንዳለበት የሚጠራጠርና ለውጡን እኔ በአመፅ አመጣውት ብሎ የሚፎክር ፊት ፊቱን ብቻ የሚያይ ፍጡር ነው። በመጀመሪያ አካባቢ ሕዝብን በተስፋና ደስታ ፍንጣቂ ኢትዮጵያዊነትን ቦግ ብሎ እንዲበራ ያንተገተገው የዶክተር ዐብይ ስብዕናብቻ ነው ብሎ የሚያስብ፥ የማይታየውን የመለኮት እጅ የማያገናዝብ ሰው ነው። በመጨረሻ ያገሩ ሰዎች የሆንን ስንቀዘቅዝ፥ በዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማት ያስታቀፋቸው፥ ይህ ስኬት ስለ ዶክተሩ የሚናገርብቻ ሳይሆን መለኮት “አስተውሉ! ጊዜውን!” እያለን ለመሆኑ ማወቅ የሚሳነው የማያስተውል ሰው ብቻ ነው። 

ባጭሩ የነገሩ ድምዳሜ ይህ ነው፡ ያም ጊዜው በማያሻማ ሁኔታ የኢትዮጵያ ነው። የምንተኛ እንንቃ! የስብራታችንን ጥልቀት ላስተዋለው፥ የጨለማውን ድቅድቅነት ለተመለከተው፥ ሊነጋ እንዳቅላላ እርግጠኛ መሆን ይችላል።
​
ከቅዱስ ቃሉ የተወሰደ፡ 
·      የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ 
·      አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ፤ ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው። 
·      ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች። 
0 Comments



Leave a Reply.

    Picture

    Archives

    December 2022
    August 2021
    July 2020
    November 2019
    October 2019
    September 2019
    August 2019
    July 2019
    June 2019
    April 2019
    February 2019
    December 2018
    October 2018
    August 2018
    July 2018
    June 2018
    May 2018
    April 2018
    October 2016

    Categories

    All

    RSS Feed

Copyright © 1999 - 2023
  • ደወል