ዋካንዳ ዘኢትዮጵያ
የዶ/ር ዐብይ አሕመድ መንግሥት ፈጣንና ምስጢራዊ ከመሆኑ የተነሳ ዱብዳ ርምጃዎችን በመውሰድና የሕዝብን ጆሮዎች ጭው የሚያደርጉ መረጃዎችን በመልቀቅ ይታወቃል:: ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ሰሞኑን በእነእስክንድር ነጋ በእነጃዋር መሐመድና በስድስት የህወሃት ከፍተኛ ባለሥልጣናትላይ የነበሩትን ክሶች ማቋረጡን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሰበር ዜና ያስታወቀው ድርጊት ነው:: ይህ ሰበር ዜና ድንጋጤን የፈጠረው በሁለት ሳምንታት ያሸነፍናቸው ጠላቶቻችን ምን ኃይል አግኝተው ነው መንግሥት እንደዚህ ድንገተኛ ውሳኔ ለመወሰን ያስገደደው በሚል ይመስለኛል:: በተለይ ደግሞ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው በአገሪቱ ውስጥ በሙሉ ኃይላቸው ጉልህ ተሳትፎ እያደረጉ ባሉበት ወቅትና የተለያዩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በመገናኛ ብዙሃን በመቅረብ ከህወሃት ጋር ድርድር አይታሰብም ባሉበት “ማግስት” መሆኑ ጉዳዩ ድንጋጤ ብቻ ሳይሆን ቁጣም አስከትሏል:: ይህ ጉዳይ ትልቅ የአገር ጉዳይ ነውና ኢትዮጵያውያን ሁሉ እየተነጋገሩበት ይገኛሉ:: እኔም ጉዳዩን ከሰማሁበት ጊዜ ጀምሮ በግሌም ከወዳጆቼም ጋር በመሆን ማብሰልሰሌ አልቀረም:: በተለይ ደግሞ በሁለት የአገራችን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ማብራሪያከተሰጠ በኋላ ውሳኔያችን ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ነውና እባካችሁ ተቀበሉልን የሚል የአክብሮት መማጸኛ ከቀረበልን በኋላ ለምን ሙሉ ለሙሉ መርካት አቃተን የሚለው ጥያቄ ትኩረቴን ስለሳበው በ2010 ዓ.ም የታወጀውን የምህረት አዋጅና በ2008 ዓ.ም የዓቃቤ ሕግን ሥልጣንና ኃላፊነት ለመወሰን የወጣውን አዋጅ ሳነብ በመንግሥትና በተራው ሕዝብ መካከል “ምህረት” የሚለው ቃል ፍችውና ጽንሰ አሳቡ የተለያዩ መሆናቸውን አስተውያለሁ:: እርግጥ ነውጠቅላይ ዐቃቤ ሕግዶ/ር ጌድዮን ጢሞቴዎስምህረትም ይቅርታም አላደረግንም የሆነው ክስ መቋረጥ ነው ቢሉም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ማብራሪያ ግን ክስ ማቋረጥና ምህረት ተደባልቀዋል:: ክስ ማቋረጥ፣ ምህረት፣ይቅርታ ልዩነት ቢኖራቸውም በጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ የተሰጡት ፍቺዎችና አሠራሮች ለባለሙያ ይጠቅማሉ እንጂ በተራው ሕዝብ ዘንድ የጎላ ልዩነት የላቸውም:: ምክንያቱም እውነታው ወንጀለኞች ለጊዜውም ይሁን በቋሚነት ከእስር ተፈተው በተከሰሱበት ወንጀሎች አሁን አይጠየቁም:: “ምህረት” የሕግ ቃል ብቻ ሳይሆን የኅይማኖት ቃልም ነው:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ኅይማኖተኛ ነውና ከኅይማኖቱ የወረሰው ፍቺ አለው:: ለነገሩ “የቃል ትርጉም የሚገኘው በማኅበረሰቡ ውስጥ ነው”ይባል የለ! በተጨማሪም የምህረት ትርጉም በግዕዙ ግሥ መቅጣትን ከማቅናት ጋር ያስተካክላል:: መንግሥት “ምህረት” ሲል የእንግሊዝኛ አቻው “Amnesty”ሲሆን እንደ እኔ ያለው ተራው ሕዝብ “ምህረት” ሲል የእንግሊዝኛ አቻው “Mercy” ነው:: ከእንግሊዝኛው ልዩነት ባሻገር መንግሥትና ሕዝብ በቃሉ አጠቃቀም ላይ መሠረታዊ ልዩነት አላቸው:: መንግሥት “ምህረት”አደረግሁ ሲል ወንጀለኛው በጥፋቱ መፀፀቱንና ከጥፋቱ መመለሱን ማረጋገጫ ኖሮት ሳይሆን የግለሰቡ መፈታት ለአገር ጥቅም አለው በሚል መነሻ ነው:: እንዲያውም የመንግሥትን የሞራል ልቀትን የሚያጎላ ነው:: በሕዝብ አረዳድ ግን ከምህረት በፊት ፀፀትና ንስሀ አሉ:: ስለዚህ ወንጀለኛ በመንግሥት ምህረት ተደረገለት ሲባል ሕዝብ ወንጀል ከሠራው ግለሰብ በጥፋቱ መፀፀቱንና ሁለተኛ አይለምደኝም ማለቱን ይጠብቃል::የሕዝብ ስጋት ምንጩ ለምህረት ካለው መረዳት አንጻር ስለሆነ ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር የተፈቱት ግለሰቦች እንደገና በሕዝብ ላይ ፍጅትና በደል ላለማድረሳቸው ምን ዋስትና አለ ነው:: ተፀፅተዋል? ሁለተኛ እንደ በፊቱ አናደርግም ብለዋል? ፈጣሪ እንኳን ምህረት የሚያደርገው በፍጹም ልባቸው ለተፀፀቱ ነው:: ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ አዎንታዊ ምላሽ ካልተገኘ በስንት ጸሎትና እግዚኦታ በስንት መስዋእትነት የተገላገልናቸው ሰዎች ተመልሰው በመካከላችን መከሰታቸው ምቾት አይሰጥም::መንግሥት ከፈጣሪ በላይ ርህራሄ ያሳየ መስሎ ታይቶኛል:: ሌላው ያለመግባባቱ መንስዔ መንግሥት ክሱን ያቋረጠው በዳዮችን ነጻ ለማውጣት እንጂ ተበዳዮችን ከግምት ውስጥ ሳያስገባ በመሆኑ ነው::ለውጡ በተጀመረበት ወቅት መንግሥት የብዙ ሰዎችን ክስ አቋርጧል፣ የምህረት አዋጅ አውጥቶ ምህረት አድርጓል:: በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደስ አለው እንጂ አልከፋውም፤ አልተቆጣም:: ምክንያቱም በዚያን ጊዜ ከእስር የተፈቱትና ወደ አገር ቤት የገቡት ተበዳዮች ስለሆኑ መንግሥት ደግሞ በዳይ ስለነበር ነው:: የመንግሥት ርምጃ በሕዝብ ላይ በሠራው በደል መፀፀቱን ማሳያ ነበር:: የአሁኑ ግን የተለየ ነው:: አሁን ከእስር የተለቀቁት ግለሰቦች በዳዮች ናቸው፤ ለዚያውም ሕዝብን!በሕዝብ የምህረት ጽንሰ አሳብ አረዳድ መሠረት ምህረት የሚያደርገው የተበደለው አካል ነው:: በኅይማኖቶቻችን ምህረት አድራጊው የበደልነው ፈጣሪ ነውና::ፈጣሪ ምህረት ሲያደርግ ወዶና የአጥፊውን እዳ ራሱ ችሎ ነው:: መንግሥት የወንጀለኞችን ክስ ሲያቋርጥ ለተበደሉት ምን አስቧል? የተበደሉትን ማማከር ለምን አልቻለም? በተበደሉት ስም ምህረት ማድረግ ይችላል ወይ? ለነዚህና መሰል ጥያቄዎች መልስ ስላልተሰጠ ቁጣ ብቻ ሳይሆን ሀዘንም በሕዝብ ልብ ውስጥ እየፈሰሰ ነው:: እነዚህን የአረዳድ መዛባቶች ተገንዝበን ማስተካከያ ብናደርግ ወይም በሚቀጥሉት ውሳኔዎች ውስጥ ከግምት ውስጥ ቢገቡ በመንግሥትና ሕዝብ መካከል የሚፈጠሩትን ክፍተቶች ማጥበብ ይቻላል የሚል አስተያየት አለኝ:: ሕዝብ በመንግሥት ውሳኔ ላይ እምነትን በመጣል ከቁጣና ቁጭት ይልቅ ድጋፍነቱን ይቀጥላል:: ውስብስብ ችግሮችና ግጭቶች ባሉባት አገራችን ኢትዮጵያ መንግሥት የባለሙያ ቃላት ትርጉምን ብቻ ሳይሆን በሕዝቡ ውስጥ ያለውን ፍቺ ተረድቶ ጥያቄውን ለመመለስ ጥረት ቢያደርግ ጥቅም እንጂ ጉዳት አይኖረውም:: ዶ/ር ጌድዮን ጢምቴዎስ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት በአገራችን ኢትዮጵያ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት በመደበኛ የፍትህ ሥርዓት ስለማይቻል “የሽግግርና የተሃድሶ ፍትህ” ሥርዓትን እንከተላለን ብለውነበር:: እንግዲህ በዚህ ሂደት ውስጥ የተበደሉት በቂ ውክልና እንዲያገኙ፣ ድምጻቸው እንዲሰማ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉትን እሴቶችና ጽንስ አሳቦች ከግምት ውስጥበማስገባት፣ ፍትህ፣ ምህረት፣ ይቅርታ የመሳሰሉትን ቃላት “ሕዝባዊ ትርጉም“ በመስጠት በአገራችን ዘላቂ ሰላምና እድገት የሚመጣበት ጊዜ ቅርብ እንዲሆን ምኞቴም የዘወትር ጸሎቴም ነው:: በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ማብራሪያና ተማጽኖ ያቀረቡት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተደረገው ግጭት የመጀመሪያው ሰለባ በሆኑትና የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት ለማስከበር ከሌሎች የአገራችን የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን መስዋእትነት በከፈሉና እየከፈሉ ባሉ ከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ የጦር መኮንኖች፣ ውዶቻቸውን በሞት በተነጠቁ ቤተሰቦችና ወታደሮች፣ የአገሪቱና የክልሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የውጭ አገራት ተወካዮች በተገኙበት ፊት ቆመው ነው:: የዚህን እንድምታ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ በጭንቅ መልሰን ያገኘነውን አንድነታችንን በሚያፈርስ መንገድ ትናንት ለአገራችን አንድነት የቆመና ከለላ የሆነን የመንግሥት አመራርን “አሳልፎ ሰጠን” በማለት በችኮላ ባንመዝን የተሻለ ነው እላለሁ:: ከዚህ ይልቅ በመንግሥትና ሕዝብ መካከል ያሉትን ክፍተቶች ለማጥበብ ከችግሩ ይልቅ የመፍትሔ አካል ብንሆን ለወደፊቱ ርምጃችን ጥቅም ይኖረዋል::
0 Comments
ዋካንዳ ዘኢትዮጵያ
ዳኛው ማነው? የተሰኘውን በአምባሳደር ታደለች ኃ/ሚካኤል የተጻፈውን መጽሐፍ አንብቤ ስጨርስ እርሳቸው የጠየቁትን ጥያቄ ለመመለስ ሳወጣና ሳወርድ በመጽሐፋቸው ውስጥ ብዙ“ዳኞችን”አየሁ:: ጉልበት፣ ጠብመንጃ፣ ባለጊዜ፣ አድርባይነት፣ ርዕዮተ ዓለም በአንድ ወገን ሆነው ያሻቸውን ፍርድ ሲሰጡ፥ እንደ ኩራዝ ብርሃን ጭል ጭል የምትል በጎ ሕሊና ደግሞ ግራ ቀኙን በመመልከት እፁብ ድንቅ የሚያስብል ዳኝነትን ስትሰጥ ትታያለች:: አምባሳደር ታደለችም ይህችን በጎ ሕሊና ሲያዩ “እንዴት ሊሆን ቻለ?”በማለት አግራሞትና ጥያቄ እንደፈጠረባቸው ተገንዝቤያለሁ::እኔ እንደገባኝ የእርሳቸው የ“ዳኛው ማነው?” ጥያቄ በመግቢያው ላይ የፍትሕ በመውጫው ላይ ደግሞ የታሪክ ዳኝነትን ነው:: ዳኛ፦ ግራ ቀኙን መመልከት እንዲችል መኻል ላይ ያለ ሰው ወይም ተቋም ነው:: በአገራችን የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ግን መኻል መሆን ተወዳጅ አይደለም:: በደርግ ዘመን “መኻል ሰፋሪዎች ሚናችሁን ለዩ” በማለት መኻል ላይ የቆመ ዳኛ እንዳይኖር ተደርጓል:: መኻል ላይ የነበሩ ልክ “ከወንድሞቿ በላይ ከፍ እንዳለች ማሽላ ወይ ለወፍ አለበለዚያ ለወንጭፍ” እንደሚባለው ለአንዱ ሲሳይ ሆነዋል:: በኢህአዴግ ዘመንም ቢሆን መኻል የሚባል የለም:: አንድ ሰው በቅንነት ለአገርና ለወገን ይጠቅማል ብሎ የሚናገረውን አሳብ የነ እገሌ አሳብ ነው በማለት ይፈረጃል:: ስለዚህ የአንድ ጎልማሳ ሰውን እድሜ ያክል፥ በአገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ጭል ጭል ከምትለዋ በጎ ኅሊና በስተቀርተቋሟዊ የሆነ እውነተኛ ዳኛ አለ ለማለት ያስቸግራል:: ይህ ልምምድ ለኅምሳ ዓመታት እንደ ሸረሪት ድር አእምሯችንን ተብትቦ ስለያዘው፥ዳኝነትን የምናየው ከራሳችን አቋም አንጻር ብቻ ነው:: ስለዚህ በዳይና ተበዳይን በትክክል ለመለየት አልተቻለም:: ባለጊዜ የወደቀውን ጥፋተኛ ያደርጋል፤ እርሱ ሲወድቅ ደግሞ በሌላ ባለጊዜ ጥፋተኛ ይባላል፤ ያ በመጀመሪያ ጥፋተኛ የተባለው ደግሞ ከወደቀበት አንሰራርቶ እኔ ጥፋተኛ አልነበርኩም ይላል:: እንዲህ እንዲህ እያለ እስከዛሬ ደርሰናል:: በታሪክም ሆነ በትርክት መግባባትና መስማማት አዳጋች ሆኗል:: መወገን እንጂ መኻል ላይ ቆሞ እንደ ባለ አእምሮ ማሰብ እንደ ክፉ ነገር ተወስዷል:: ከእውነተኛ ዳኝነት ይልቅ “ሕጋዊንና ሕገወጥነትን” ቀላቅሎ መሄድ እንደ ትክክለኛ የትግል አቅጣጫ ይታያል:: ከዚህም የተነሳ ዳኝነትን የሚያዛቡ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ድርጊቶችን በእለት ተእለት ሕይወታችን ማየት እንግዳ አይደለም::ከእኛ በተቃራኒ የቆሙት ላይ ሕጋዊ ርምጃ ሲወሰድ መንግሥትን ማወደስ፥ በእኛ ላይ ሲሆን ግን መንግሥትን መሳደብ ወይም የሽምግልና ጋጋታማብዛት ልማድ ሆኗል:: ለራስ የፓለቲካ ግብ ጥቅም ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥትን ማክበርም ይሁን መጣስ ምንም ልዩነት የላቸውም:: ሕዝብን ለማደናገር ሕገ መንግሥት ሲጣስም ሳይጣስም ተጣሰ ብሎ መጮህ ለጆሮ የሰለቸ “ሙዚቃ” ነው::ሰዎች በግፍ ከቀያቸው ሲፈናቀሉ ዝም ያለ “አክቲቪስት” አፈናቃዮች በቁጥጥር ስር ሲውሉ ሰብአዊ መብት ተጣሰ ይላል:: መኻል ላይ የቆሙ ሰዎችና ተቋሟት በሌሉባት አገር “ባለጊዜ” እንጂ “ዳኛ” ሊኖር አይችልም:: ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው ለውጥ ሲመጣ “ተደምረሃል?” የሚለው ጥያቄ በተራው ሰው ዘንድ በስፋት ይጠየቅ የነበረው መኻል ላይ መሆን ትክክል አይደለም ከሚለው አጉል አባዜ የመነጨ ነው:: ለለውጡ ድጋፉን ለመግለጽ አዲስ አበባን ያጥለቀለቀው የሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ሰልፍ ተሳታፊ፥ በአገር ውስጥከሚኖሩትም ሆነ ከውጭ ከመጡ ግለሰቦችና ድርጅቶች “ኪስ” ውስጥ ለመግባት ብዙም ጊዜ አልወሰደበትም:: ምክንያቱም የለመድነው ጎራ ለይቶ መጎሻሸም እንጂ መኻል ላይ ቆሞ ግራ ቀኙን መመልከት አይደለም:: ወደ ግራም ሆነ ወደ ቀኝ ፈጥኖ ከመግባት መኻል ላይ ቆሞና መዝኖ የሚበጀውን መምረጥ የተሻለ ነበር:: እንግዲህ እውነተኛ ዳኛ የምንፈልግ ከሆነ መኻል ላይ የቆሙ ግለሰቦችና ተቋሟት ያስፈልጉናል:: ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች ጋር በነበራቸውየውይይት ጊዜ “ሲቪክ ሶሳይቲ ሚዛን የሚያስጠብቅ” ነው በማለት መኻል ላይ ያለ ተቋምን አስፈላጊነት ተናግረዋል:: ይህ መኻልላይ ላሉና ለመሆን ለሚፈልጉ ትልቅ ተስፋ ነው:: ምክንያቱም ከረጅም ዓመታት በኋላ መኻልላይ መቆም ጥሩ መሆኑን ከገዢው ፓርቲና መንግሥት በይፋ ስለሰማን ነው:: ይህ መልካም ጅምር ከግብ እንዲደርስ የፓለቲካ ፓርቲዎችና መንግሥት መኻል ላይ ያሉ ተቋማትን ለራስ ፍላጎት መጠቀሚያ ከማድረግ መቆጠብ ይኖርባቸዋል:: ተቋማቱም የመንግሥትና የፓለቲካ ፓርቲዎች መጠቀሚያ ከመሆን ራስን ማጽዳት ይጠበቅባቸዋል:: ይህ ሲሆን በአገራችን ኢትዮጵያ ዳኛ ይኖራል፣ ዴሞክራሲም ያብባል፣ በጎ ሕሊና ያላቸው ትልቅ ሰዎችም ይበዛሉ:: ከዚህ በተጨማሪ ብዙ የተባለለት የፍትሕና ርትእ አካሉ መኻል መሆን እጅግ አስፈላጊ ነው:: በዚህ አካል ላይ የፓርቲዎችም ሆነ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ለቡድን እንጂ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ መልካም አስተዳደር፣ እድገትና ዴሞክራሲ ጥቅም የለውም:: በጎ ሕሊና ያላቸው፣ መኻል ላይ የቆሙ፣ ለእውነት ተገዢ የሆኑ፣ ለገንዘብ የማይጓጉ፣ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ ሰውን የሚያከብሩ፣ በሙያቸውና በስብእናቸው የተከበሩ ሰዎችን በዚህ ተቋም ውስጥ ማብዛት እውነተኛ ዳኛ እንዲኖረን ያደርጋል:: የኃይማኖት ተቋማትም መኻል ነበሩ ማለት አይቻልም:: ባለጊዜና ጉልበተኛ ወደፈለገው ሲጎትታቸው፣ እንደፈለገው ሲያምሳቸው ብዙ ዓመታትን አስቆጥረዋል:: ዛሬም ቢሆን ሳይጎተቱ ለመጎተት ራሳቸውን ያዘጋጁ፣ ጭርስኑ ጎራ ለይተው ከፓለቲከኞች የማያንስ የመከፋፈል ሥራ የሚሠሩ የኃይማኖት መሪዎች ይስተዋላሉ:: በግላቸው የፈለጉትን መሆን ይችላሉ፤ ተቋሙን ግን መኻል ላይ እንዲቆም መተው ለኃይማኖቱም ለአገርም ይጠቅማል:: ምክንያቱም የኃይማኖት ተቋማት መኻል መሆን በጎ ሕሊናና ሚዛናዊነት ያላቸው ዜጎችን በማዘጋጀት እውነተኛ ዳኞች እንዲኖሩን ያደርጋል:: በእኔ እይታ እስካሁን ድረስ በሙስሊሙም ሆነ በክርስቲያኑ ዘንድ የዳኝነትን ማዕረግ የተጎናጸፉ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ ይመስሉኛል::እርሳቸውን ያነሳሁት ታዋቂ ስለሆኑ ነው እንጂ ብዙ ሰው የማያውቃቸው፣ ሚዛናዊ የሆኑ፣ የሚመሩትን ምዕመን በጎ ሕሊና እንዲኖረውና እንዲያመዛዝን የሚያስተምሩ መኖራቸውን አውቃለሁ:: እንደ እነዚህ ዓይነት ያሉ መሪዎችን በሁሉም የእምነት ተቋማት ፈጣሪ እንዲያበዛልን ምኞቴ ነው:: ሰው አእምሮ ያለው ፍጡር ነው:: የተፈጠረውም ማመዛዘን እንዲችል ሆኖ ነው:: ስለዚህ የሰው ልጅ የሆነ ሁሉ መኻል ላይ በመቆም የሠራቸውንና የሄደበትን ጎዳና ለማየት ከሕሊናው ጋር የሚሟገትበት ጊዜ ሊኖረው ይገባል:: በራሱ ላይ ዳኛ ያልሆነ እንዴት ብሎ ሌላውን ሊዳኝ ይችላል? ሕሊናን የጣለ ሰው መሪ ከሌለው መርከብ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ከአደጋ አያመልጥም:: ሲሳሳት የማይጸጸት ሰው ሕሊናውን ጥሏልና ከሰው ተራ ወጥቷል:: መኻል ላይ የቆሙ ሰዎች ብዙዎችን ከስህተት ይታደጋሉ:: በጎ ሕሊና ያላቸውና መኻል ላይ የቆሙ ሰዎች (ወላዋይ ማለቴ አይደለም) ኖረው ቢሆን ኖሮ ብዙ ወገኖቻችን በሕይወት ይኖሩ ነበር:: በመጨረሻም፥የተጀመረው ለውጥ ግንባር ቀደም መሪዎች ከላይ የዘረርኳቸው ተቋማት ፍሬ እንዲያፈሩ የድርሻቸውን ይወጣሉ የሚል እምነት አለኝ:: ነገር ግን እንደ ቀደምቶቹ ባለጊዜዎችና ጉልበተኞች፥ መኻል ላይ የቆሙትን በማሸማቀቅ፥ የሰውም የተቋማትም ዳኞች ማፍራት እንዳንችል ቢያደርጉ፥ የታሪክ አቅጣጫን የሚዘውር፣ መንግሥታትን የሚያስነሳና የሚጥል ፈጣሪ የምን ጊዜም ዳኛ መሆኑን መርሳት የለባቸውም:: የእርሱ ዳኝነት በዚህም በወዲያኛው ዓለም ነውና በተቻለን መጠን በእርሱና በሰዎች ዘንድ በጎ ሕሊና እንዲኖረን መትጋት ለሁላችንም ይበጃል:: ዋካንዳ ዘኢትዮጵያ
ስንቶቻችን አስተውለን እንደሆነ ባላውቅም፥ ዘርንና እምነትን መሠረት ያደረጉ አንዳንድ ጥቃቶች የተፈጸሙት ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እግራቸው ከኢትዮጵያ ወጣ ሲል ነው:: በነዚያኑ ጊዚያት በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ያሉ ሥልጣናቸውን ያጡና ሥልጣን ላይ ለመውጣት የቋመጡ ሁሉ እኩዩን ድርጊት ሳያወግዙመግለጫ በማውጣት በፌዴራል መንግሥቱ ላይውርጅብኝ ያወርዱበታል:: ብዙ አዳማጭ እንደሌላቸው ቢያውቁትም በፕሮፓጋንዳ ኃያልነት እምነት ስላላቸው ለመላው የኢትዮጵያ “ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” በመንግሥት ላይ እንዲነሱ ጥሪ ያቀርባሉ:: ለውጡን፣ የለውጡን ግምባር ቀደም መሪዎችና ጠቅላይ ሚንስትሩን ከሚደግፈው ሕዝብ ለመነጠል እነርሱ በሚቆጣጠሯቸው፣ በሚዛናዊነት ስም የሁሉንም ድምፅ እኩል እናሰማለን በሚሉና ወሬ ካገኙ ምንም ይሁን ምን በሚያናፍሱ የመገናኛ ብዙሃንና ማኅበራዊ ሚድያዎች አማካኝነት ከፍተኛ ዘመቻ ያደርጋሉ:: እነዚህን የመሳሰሉ የተቀነባበሩ፣ ተደጋጋሚ ሴራዎችና ድርጊቶች ሲፈጸሙ የዚች ድሀ አገርና ሕዝብ ንብረት ወድሟል፣ ሁላችንም በፍርሃት ተውጠናል፣ ንፁሃን ወገኖቻችንን አጥተናል:: ሰሞኑን የሆነውም ይኸው ነው:: የሴረኞቹ እኩይና ዘላቂ ዓላማ ግቡን ባይመታም የአገራችን የፍትህ ሥርዓት ቀርፋፋ በመሆኑ፥ ወንጀለኞች ተገቢውን ቅጣት ሲያገኙ ባለመታየታቸው፥ ዘረኞችና መሰሪዎች የልብ ልብ አግኝተው በሐሳብ ነፃነት ስም ደረታቸውን ነፍተው ይመላለሳሉ:: ዘረኝነት ዋልታ ረገጥ አስተሳሰብ ነው ብሎ ማለት ስህተት ነው:: ዘረኝነት እኩይና አስጸያፊ ነው:: በጥቂት አገሮች ተሞክሮ አንድም መልካም ውጤት አላመጣም:: ታሪክ የሚያስተምረን ዘረኝነትና ዘረኞች ብዙ ጥፋት ካደረሱ በኋላ እነርሱም መጥፋታቸውን ነው:: በየትኛውም አገር ዘረኞች ቢኖሩም ደረታቸውን ነፍተው እንደልባቸው የሚመላለሱት ግን አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ነው:: በሌሎች አገራት ግን ብቅ ሲሉ ዘረኝነትን የሚኮንኑ ሲረባረቡባቸው ወደ ጉድጓዳቸው ገብተው ሲያሴሩ ይውላሉ:: ዘረኝነት ሰዎች ያልሆኑትን ናችሁ ብሎ እንዲያብጡና እንዲኮፈሱ በማድረግ፥ ሌላውን እንዲንቁና እንዲጠሉ የሚያስተምር የሰው ልጆች ጠላት ነው:: ዘረኞች መርዝን በማር፣ ጥላቻን በፍቅር ለውሰው በራሳቸው ማሰብ ላቆሙ ተከታዮቻቸው ያጎርሳሉ:: ዘረኝነትና ወገናዊነት ልዩነት አላቸው:: ወገናዊነት ወገኑን ከመውደዱ የተነሳ ለወገኑ እኩልነት፣ እድገትና ብልፅግና የሚደክም ነው:: ዘረኝነት ግን ሌላው እንዲጠፋ፣ እንዲቆረቁዝና እንዲደኸይ ሌት ተቀን የሚለፋ ነው:: ዋልታ ረገጥ ወገናዊነት ደግሞ ወደ ዘረኝነት ለመቀየር ጫፍ ላይ የደረሰ አስተሳስብ ነው:: ዘረኞች የማኅበረሰብጠንቅ (Sociopath)እናወፈፌ (Psychopath)ስለሆኑ ቦታቸው ክብር ሳይሆን የሥነ ልቦና ሕክምና ቤት ነው:: ስለዚህ የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የክልል መስተዳደሮች ዘረኝነትንና ዘረኞችን መታገስ የለባቸውም:: “…ቀኝጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤” የሚለው የወንጌል ትምህርት ለግለሰቦች እንጂ ለመንግሥት የተሰጠ ኃላፊነት አይደለም:: የመንግሥት ኃላፊነት ክፉ አድራጊዎችን መቅጣት መልካም አድራጊዎችን ደግሞ ማመስገን ነው:: ክፉ አድራጊዎችን ለመቅጣት እንዲችል አስፈላጊው የሕግ ማእቀፍና አቅም “ሰይፍ” ስለያዘ ሊጠቀምበት ይገባል::የመንግሥት ባለሥልጣናት በግላቸው ሌሎች ላደረሱባቸው በደል መታገስ ይችላሉ፤ ምርጫው የራሳቸው ነው:: በደል አድራሾች ግን በሕግ መጠየቃቸውን የእነርሱ ትዕግስት ማስቀረት የለበትም:: የፍትህ ሥርዓቱ “ማንም ሰው ከሕግ በላይ አይደለም” በሚል መርህ ላይ መቆሙ ለምንመኛት ኢትዮጵያ ጽኑ መሠረት ነው:: የፌዴራል መንግሥትና የክልል መስተዳደሮች በሚያስተዳድሩት ሕዝብና ግለሰቦች ላይ ክፉዎች በደል ሲያደርሱ “በትዕግስት” ሲያልፉ፥ መልካም አድራጊዎችን መቅጣታቸውና ክፉ አድራጊዎችን መሸለማቸው መሆኑን ሊረዱ ይገባል:: ፈጣሪም ሕዝብም የሚወደው፥ መንግሥት ክፉ አድራጊዎችንና ወንጀለኞችን የሚቀጣ ሲሆን ነው:: በቀጠሮ ብዛት የሚታወቀው የአገራችን የፍትህ ሥርዓት በክፉ አድራጊዎች ላይ በፍጥነት ፍርድ መስጠት ይኖርበታል:: ፍትህ ለአንድ ሕዝብና አገር እጅግ አስፈላጊ ነው:: ክፉዎች ፍርድ አላገኙም ማለት በተበደሉ ላይ እንደመቀለድ ይቆጠራል:: ፍትህን የፖለቲካ መሣሪያ ማድረግና በሰበብ ባስባቡ ማጓተት ወንጀለኞችን ማበረታታት ነው:: እኩዮችን በተለይ ዘርንና ሃይማኖትን መሠረት አድርገው ጥቃት የፈጸሙትን ፍርዳቸውን ከነአሳፋሪ ድርጊቶቻቸው ለሕዝብ ግልፅ ማድረግም አስፈላጊ ነው:: እንደ ሰሞኑ ዓይነት ያሉ ጥቃቶች የጅምላ ጭፍጨፋ ታናሽ ወንድሙ እንጂ “የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” መብት መከበር አይደሉም:: የዘረኞች ኃይል እንደ እሳት የሚለበልብ ምላስና እንደልብ የሚበተን ገንዘብ ናቸው:: እነዚህ ከሌሏቸው ሽባ ናቸው:: መንግሥት የተደራጀ መዋቅሩንና የዲፕሎማሲ ግንኙነቱን በመጠቀም ምንጮቻቸውን ማድረቅ ይኖርበታል:: የዘረኞች ዕውቀትና ገንዘብ ለጥፋት እንጂ ለልማት ውሎ አያውቅም፤ በአገሪቱ ውስጥ እስካሁን የታየውም ይኼው ነው:: መጋቢት 18 ቀን 2011ዓ.ም ታትሞ በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ “በየትኛው ፍቅር እንደመር?” በሚለው ጽሑፌ የአገራችንን ፖለቲካ ለዜጎች መተዉ እንደሚገባ “አንቺ ምንቸገረሽ ሁለት አባት አለሽ፣ አንዱ ቢሞትብሽ በአንዱ ትምያለሽ፤” በማለት ጽፌ ነበር:: በተወካዮች ምክር ቤትማክሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)ይህንኑ ጉዳይ አንስተውት ነበር:: የሌሎች አገራት ዜግነት ያላቸው ፖለቲከኞችና አክቲቪስት ነን ባዮች አገራችን በእሳት ብትጋይ የሚሄዱበት አገር አላቸው:: እኛ ግን ያለችን ይቺው አንድ አገር ናት:: በትውልዳቸው ኢትዮጵያውያን ስለሆኑ ከሌሎች የውጭ አገራት ዜጎች በተለየ ሁኔታ መታየታቸው አግባብ ነው:: ይህ አግባብ ግን በአገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ እንጂ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት አልፎም የመንግሥትን ሥልጣን በግርግር እንዲይዙ አይደለም:: መንግሥት፥ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሆነው የሌሎች አገራት ዜግነት ያላቸውን ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት እንዲሰናበቱ፣ አሉታዊና አፍራሽ ድርጊት የሚጫወቱትን በሕግ ጠይቆ የተፈረደባቸውን ብይን ሲጨርሱ ወደ አገራቸው ማሰናበት ይኖርበታል:: ይህ ርምጃ ፍትሐዊ እንጂ አምባገነንነት አይደለም:: የመንግሥት ጆሮና ዐይን ሕዝብ ነው:: የአሁኑ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት ሕዝብ ስጋቱን ገልጾ ነበር:: ሰሚ ግን አላገኘም:: የአገር መከላከያ በዋናነት የተቋቋመው ከውጭ የሚመጣ ጠላትን ለመከላከል ነው:: በአገር ውስጥ ላሉት ችግሮችና ወንጀሎች ግን የፖሊስና ሚሊሻ ኃይል በቂ ናቸው:: እነዚህ ኃይሎች ውጤታማ የሚሆኑት ከዘረኝነት ነፃ መሆናቸው ሲረጋገጥና ከሕዝብ ጋር ተቀናጅተው ሲሠሩ ነውና ሕዝብን በጸጥታና ደህንነት ጥበቃ ውስጥ ተሳታፊ ማድረግ ለዘላቂ ሰላም ዋስትና ነው:: ለውጡ በታለመለት መንገድ እንዲሄድ የብዙሃኑ ፍላጎት ነውና በዚህ ለመሳተፍ ወደ ኋላ የሚል የለም::ለውጡ ቢጨናገፍ የሚተካው ሥርዓት ያለፈው ሳይሆን የባሰና የከፋ ነው:: ክግብፅ ሁለተኛው አብዮት ውድቀት እንማር:: የዘረኝነት ሰለባ የሆኑትን አዛውንቶች፣ ጎልማሶችንና ወጣቶችን ሥነ ልቦናና አስተሳሰብን ለመቀየር ብርቱ ትግልና ሥራ ይጠይቃል:: የእርቀ ሰላም ኮሚሽን በተለያዩ ደረጃዎች ከሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች፣ አባገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ በአገር ውስጥና ውጭ ከሚኖሩ ምሁራን፣ የክልልና ወረዳ አስተዳደሮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የሚዲያ ባለቤቶች፣ አክቲቪስቶች፣ የፖለቲካ ሰዎች፣ ወዘተ ጋር በመቀናጀት መጠነ ሰፊ የሆነ ሥራ ይጠብቃቸዋል:: የእነርሱ ሥራ አመራር መስጠት እንጂ ሥራው የሚሠራው በሌሎች መሆኑን ተገንዝበው የእርዳታ ጥሪ ቢያደርጉ መልካም ነው:: በሙያው የተካኑ ባለሙያዎችና የእርቀ ሰላምን ወቅታዊነት የተረዱ ሰዎች የተቻላቸውን ለማገዝ ይፈልጋሉ:: ነገር ግን እንዴት አድርገው ከኮሚሽኑን ጋ እንደሚገናኙ አያውቁም:: በጣም አስፈላጊ የሆነው ጉዳይ ተገቢውን ትኩረት አላገኘም ብዬ አስባለሁ:: ምክንያቱም የእርቀ ሰላሙ ኮሚሽን በሚዲያ አማካኝነት ወደ ሕዝብ ብቅ የሚለው ከብዙ ወራት በኋላ ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ስለሆነ ነው:: በአዳስ አበባና አካባቢዋ በፌዴራሉ መንግሥት አማካኝነት አጓጊ የሆኑ ፕሮጀክቶች ታቅደው እየተሠሩ ነው:: እነዚህ ፕሮጀክቶች ወጣቱ ጉልበቱንና ዕውቀቱን ለመልካም ነገር እንዲጠቀምበትና እርሱም እንዲጠቀም ያግዛሉ:: ክልሎች እርስ በእርስ ከመቆራቆስ ይልቅ፥ ተመሳሳይ እቅዶችና ፕሮጀክቶችን ነድፈው ቆመንለታል ለሚሉት ሕዝብ በተለይ ለወጣቱ የሥራ እድልና ተስፋ ቢፈጥሩ፥ ወገኖቹ ላይ የሚሰነዝረውን ገጀራና ዱላ ራሱንና ወገኑን በሚጠቅም ተግባር ላይ ያውለዋል::ዕውን ሊሆን የሚችል ተስፋ ለሰው ልጅ ምግብ ነው:: የዛሬው ጨለማ በነገው ብርሃን እንደሚተካ የሚያይበት መነጽር ነው:: በአዲስ አበባ ላይ የታየው ብርሃን በክልሎችም እንዲታይ የክልሎችና ወረዳ መስተዳደሮች ስብሰባንና ሴራን ቀንሰው መሬት የሚወርድ ሥራ ላይ ቢተጉ ይሻላል:: በመጨረሻም፥በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ ድረ ገጾችና ማኅበራዊ ሚዲያዎች አገራቸውንና መላውን ሕዝቧን የሚወዱ፣ ከተለያዩ ማኅበረሰብ የወጡ፣ የተለያየ የዕውቀትና የትምህርት ደረጃ ያላቸው ዜጎች ለኢትዮጵያ ይጠቅማል ብለው ያሰቡትን ጊዜ ወስደው ይጽፋሉ፣ ይናገራሉ፤ይመክራሉ:: የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት እነዚህን ሐሳቦች ጨምቆ ለሚመለከተው አካል ያስተላልፋል የሚል ግምት አለኝ፤ እርግጠኛ ግን አይደለሁም:: ምክንያቱም ሐሳቦቻቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የላኩ ጽሑፎቻቸው ለሚመለከተው መድረሳቸውን የሚገልጽ ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳላገኙ ከማውቃቸው ለመረዳት ስለቻልኩ ነው:: ሥራ ከበዛባቸው ቢያንስ “ራስ-ሰር ምላሽ” ከምስጋና ጋር ማድረግ ይገባቸዋል:: መንግሥት መናገር ብቻ ሳይሆን ማዳመጥ፥ ማዳመጡንም ማሳወቂያ መንገድ መቀየስ አለበት:: ዋካንድ ዘኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊከ (ኢፌዴሪ) ሕገ መንግሥት አዋጅ ታውጆ በተግባር ላይ ከዋለ 24 ዓመታትን አስቆጥሯል:: አሁን የመጣው ለውጥ ከመጀመሩ በፊት በገዢው ፓርቲና በመንግሥታዊ መዋቅሮቹ ሲነገር የነበረው “የማንነት ጥያቄዎች መልስ አግኝተዋል፤ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት ሙሉ ለሙሉ ተረጋግጧል፤ ሕዝቦች በመከባበርና በመቻቻል የሚኖሩበት ሥርዓት ተዘርግቷል፤ ከዚህ በኋላ ትኩረታችን ዋነኛ ጠላታችን የሆነውን ድህነት ለማጥፋት ልማት ላይ ነው” የሚል ነበር:: የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችና ካድሬዎቻቸው ይህን ቢሉም ይህ አባባል ከፕሮፓጋንዳ በስተቀር ሌላ ፋይዳ እንዳልነበረው እንኳን የኢትዮጵያ ሕዝብ እነርሱም ያውቁታል:: በግምባሩ ውስጥ ያሉት ድርጅቶችና አጋሮቻቸው “ነፃ ወጥተን ነፃ አውጥተናል” እያሉ “ነፃ አውጪ” የሚለውን ስያሜያቸውንየሙጢኝ ማለታቸው በሚናገሩትና በሚያምኑበት መፍትሔ ሙሉ እምነት እንዳልነበራቸው ማረጋገጫ ነው:: የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት ሙሉ ለሙሉ ከተረጋገጠ ነፃ የሚወጡት ከማን ነው? እንወክለዋለን የሚሉት ሕዝብ መብቱ ተከብሯል ካሉ ትኩረታቸው መሆን ያለበት ኢትዮጵያን መገንባት ላይ መሆን አልነበረበትም? ከለውጡም በኋላ ቢሆን፦ ተሸብበው የነበሩት ምላሶች ሲፈቱ፣ ታስረው የነበሩት እጆችና እግሮች ሲለቀቁና ተሰደው የነበሩት ወደ አገር ቤት ሲመለሱ ለዋናው ችግራችን ምላሽ ሰጥቷል ተብሎ ሲነገርለትና ዓመታዊ ፌስቲቫል ሲደረግለት የነበረው መፍትሔ እውነት እንዳልነበር በአገራችን የተከሰቱት ግጭቶችና ግድያዎች፣ መፈናቀሎች፣ የክልልነት፣ የማንነትና የወሰን ጥያቄዎች፣ በክልል መስተዳደሮች መካከል የተከሰቱት የእርስ በእርስ ውንጀላዎች፣ ሕዝብ በሕዝብ ላይ እንዲነሳና እንዳይተማመን የሚደረጉ የጥላቻ ቅስቀሳዎችና የጦርነት ነጋሪቶች ወዘተ ምስክሮች ናቸው:: እነዚህ ተሞክሮዎች መጥፎ ቢሆኑም የሚያስተምሩን ቁም ነገር ግን አላቸው:: ይኸውም የሰዎችን መብት የሚጥሰውም ሆነ የሚያከብረው፣ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጨውም ሆነ የሚያቀራርበው በወረቀት ላይ የሰፈረው ሕገ መንግሥት ሳይሆን ሰዎችመሆናቸውን ነው:: ይህ እውነታው ቢሆንም በአገራችን ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶችና ተከታዮቻቸው ዘንድ ሕገ መንግሥቱ በራሱ ችግራችንን ይፈታ ይመስልራሳቸውንከችግሩ ነጥለው ግዑዙን ሕገ መንግሥት ትልቅ የመነጋገሪያ ርዕስ አድርገውታል፤ እንደ ፖለቲካ አመለካከታቸውም የተለያየ ትርጉም ይሰጡታል:: ለአንዳንዶቹ “የአምላክ ቃል” ነው:: የአፈጻጸም ችግር እንጂ በይዘቱ እንከን አልባ ነው:: ስለዚህ ምንም መሻሻል ሊደረግበት አይገባም ባይ ናቸው:: ለአንዳንዶች ደግሞ “ሰምና ወርቅ” አለው:: “ሰሙ”ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አብረው እንዲኖሩ የሚያደርግ ሲሆን “ወርቁ”ደግሞ አገር መበተኛ ሰነድ ነው:: ስለዚህ በሴረኞች የተቀረጸ ስለሆነ መቀየር ወይም መሻሻል አለበት ይላሉ:: ለአንዳንዶች ብዙ “አንድምታዎች” አሉት:: በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያለ እያንዳንዱ አንቀጽ ትርጉሙ “አንድም እንዲህ አንድም እንደዚያ” ሊሆን ይችላል:: ስለዚህ አስፈላጊ ሲሆን ከእነርሱ የተለየ ቋንቋ የሚናገሩትን ወገኖቻቸውን ከቀያቸው ያፈናቅሉበታል ሲያሻቸው ደግሞ ሌላ ክልል ሄደው ይሄም የእኛ ነው ይሉበታል:: ለአንዳንዶች ደግሞ “መንፈስ” ነው:: ሕገ መንግሥት ሰው ይሁን ቁስ ይሁን ኢህአዴግ ይሁን አይታወቅም:: የማይታይ፣ የማይጨበጥ፣ “ሁሉ በሁሉ የሆነ” ኃይል ነው:: ብቻ ሕገ መንግሥቱ ተጣሰ ሲባል የጣሰውን “ጋኔን” መቀመቅ ለማውረድ አገርን ቀውጢ ያደርጋሉ:: አንድን ችግር ለመፍታት የሚሰጥ መፍትሔ ሌላ ያላሰብነውን ችግር ሊያስከትል ይችላል:: ለምሳሌ አምፖል የተሠራበት ዓላማ ብርሃን እንዲሰጥ ነው:: አምፖል የተፈጥሮ ብርሃን በማይኖርበት ጊዜ ብርሃን በመስጠት የተሠራበትን ተግባር ሲፈጽም ሙቀት በማመንጨት ያላሰብነውን ችግር ይወልዳል:: ይህንን ያልታሰበና እርሱ ደግሞ የሚወልዳቸውን ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ሳይንቲስቶችና መሐንዲሶች ያለማቋረጥ ምርምር በማድረግ መፍትሔ ይፈልጋሉ:: ኢትዮጵያን ለማዳን የሰጠነው መፍትሔ ሌላ ያላሰብነውን ችግር ቢፈጥር እንደ ባለ አእምሮዎች ላልታሰበው ችግር መፍትሔ መፈለግ እንጂ በችግሩ መደሰት ወይም መቆዘም ወይም ለሥልጣን መወጣጫ መጠቀም ለአገርና ሕዝብ ምንም ጥቅም አያስገኝም:: አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት የተረቀቀው ከቅንነት ነው ብለን ገምተን እንደወረደ ስንመለከተው በመግቢያው ላይ በግልፅ የተቀመጡ የታሰበለት(intended)ዓላማዎችና እምነቶች አሉት:: በመግቢያው መደምደሚያ ላይ:- የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች “ገነት” የምትመስል ኢትዮጵያን አብረው ለመገንባት ያስችላቸው ዘንድ ከላይ ለተጠቀሱት ዓላማዎችና እምነቶቻቸው በማሰሪያነት እንዲያገለግላቸው ሕገ መንግሥቱን መርጠው በላኳቸው ወኪሎቻቸው አማካኝነት ማጽደቃቸውን ያበስራል::እነዚህን ዓላማዎችና እምነቶችን ማሳካት ይችሉ ዘንድ ከመሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች አንስቶ እስከ “የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን እስከ መገንጠል ድረስ ያለምንም ገደብ”መብት እንዳላቸው በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ተደንግጓል:: ሕገ መንግሥቱ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን መብት በማስከበር ኢትዮጵያን እንዳትበታተን ያደርጋታል በሚል እሳቤ እንደተቀረጸ የሕገ መንግሥቱ ጠበቃ ነን ከሚሉ ወገኖቻችን ለብዙ ዓመታት ሲናገሩ ሰምተናል:: ይህን ንግግራቸው እውነት ነው ብለን በቅንነት ብንወስደው ሕገ መንግሥቱ የረቀቀውና የጸደቀው ትልቅ አገርን ለመገንባት እንጂ ትልቁን አገር ትንሽ ለማድረግ አይደለም ብለን መደምደም እንችላለን:: ስለዚህ ሕገ መንግሥቱን በመንተራስ የአገሪቱን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት የሕገ መንግሥቱ ዓላማ ስላልሆነ እንደ ችግር ተወስዶ መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል:: ላልታሰበ (unintended) ችግር መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ዛሬ በሕገ መንግሥቱ ስም ለውጡን ቀልብሶ የሕዝብን ተስፋ ለማጨለም፣ ተጣሰ በማለት ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማጋጨትና ኢትዮጵያን ለመበተን የሚፈልጉ የፖለቲካ ተዋንያን አሉ:: እነዚህ ድርጊቶች ግን የሕገ መንግሥቱ ዓላማዎችና እምነቶች አይደሉም:: አገርን ለመገንባትና አብሮ ለመኖር እንጂ ለመበተንና ሕዝብን ለማጋጨት ተሰብስቦ ሕገ መንግሥት ማርቀቅ አያስፈልግም:: ባልና ሚስት በቃል ኪዳን የሚተሳሰሩት ተቻችለው በደስታ አብረው ለመኖር እንጂ ለመፋታት አይደለም:: ፍቺ የጋብቻ ቃል ኪዳን ያልታሰበ(unintended)ክስተት ነው:: ሕገ መንግሥቱ ሲጸድቅ በከፍተኛ የደስታ ስሜት ሲጨፍሩ የነበሩት ተወካዮች ያስጨፈራቸው አንቀጽ 39 ያውም “…እስከመገንጠል…” የምትለዋ ቃል ከነበር ትልቅ ስህተት ሠርተዋል ምክንያቱም ያ ድርጊት ተጋቢዎች በሰርጋቸው ዕለት ልንፋታ እኮ መብት አለን ብለው ከመጨፈር ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ነው:: በምሣሌነት በአሁኑ ወቅት መነጋገሪያ የሆነውን የቋንቋን ጉዳይ እንመልከት:: “ማንኛውም ብሔር ብሔረሰብ ሕዝብ በቋንቋው የመናገር የመጻፍ ቋንቋውን የማሳደግ …መብት አለው” የሚለውን መልካም ሀሳብ ዘረኞች ሕዝብንና ሕዝብን ለማራራቅ በመጠቀም ያልታሰበ(unintended)ችግርን ይፈጥሩበታል:: ጤነኛ አእምሮና ለአገራችን በጎ ሀሳብ ካላቸው ሰዎች የሚጠበቀው ግን ከሕገ መንግሥቱ የታሰበለት(intended)ዓላማዎች ውስጥ አንዱ የኢኮኖሚ ትስስር መፍጠር ነው፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ መግባባት ያስፈልጋል፤ ስለዚህ ምን ማድረግ ይሻለናል? ብለው መምከርና መመካከር ነው:: በሕዝብ ስም መናገር አልችልም:: የእኔና የእኔ ብጤዎችአጀንዳግን ሕገ መንግሥቱ ይሻሻል ወይስ አይሻሻል፣ መጪው ምርጫ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ይደረግ ወይስ ይራዘም አይደለም:: እነዚህ የፖለቲከኞች አጀንዳዎችሲሆኑ የእኛን ቀልብ ስበው ድጋፋችንን ለማግኝት የሚጠቀሙባቸው ስልቶች ናቸው:: ከለውጡ በኋላ በተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች መካከል እየተደረጉ ያሉት ክርክሮች ከምርጫ 97 የቀጠሉ ትእይንቶች ይመስላሉ፤ አዲስ ነገርና የተሻሻለ ሀሳብ የለባቸውም:: ያ ትእይንት ደግሞ በምን እንደተጠናቀቀ ከሁላችን በላይ እነርሱ ያውቁታል፤ ዋጋ ከፍለውበታል፤ አስከፍለውበታልም:: ሕገ መንግሥቱን እንኳን ተራው ሕዝብ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እንኳ እንዳላነበቡት ከሚናገሯቸው ንግግሮች መገመት ይቻላል:: መሻሻል ካለበት ከሁሉም በፊት መሻሻል ያለበት በወረቀት ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ሳይሆን የእኛ በተለይ በአገራችን ፖለቲካ ወሳኝ ሚና ያላቸው ወገኖቻችን ውስጣዊ ባሕርይ ነው:: ላለፉት አርባ ዓመታትና ከዚያም በላይ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ድባብ የተቆጣጠሩት ፖለቲከኞች በሕይወታቸው ብዙ ውጣ ውረድ አጋጥሟቸዋል:: ለአብነት ያክል:- በተለያዩ መንግሥታት ታስረዋል፣ ተገርፈዋል፣ ጸያፍ ስድብ ተሰድበዋል፣ ተሰቃይተዋል፣ ቤተ ሰቦቻቸውንና ዘመዶቻቸውን በሞት አጥተዋል፣ ክተደገሰላቸው የሞት ድግስ ተርፈዋል፣ ጓደኞቻቸው ከአጠገባቸው ተወስደው ተረሽነዋል፣ አንዳንዶቹም ፊታቸው ተገድለዋል፣ የጓዶቻቸውንና የጠላቶቻቸውን ሬሳ ተራምደው አልፈዋል፣ እርስ በእርሳቸው ለሞትና ለግርፋት አሳልፈው ተሰጣጥተዋል፣ አንዳንዶቹ የዘረኛነት ሰለባ ሆነው ሌላውንም በክለዋል፣የልጅነትና የወጣትነት ጊዜያቸውን በትግል ውስጥ በመሆን በዱር በገደሉ አሳልፈዋል:: እነዚህ ወገኖቻችን ምንም ያክል ጥንካሬ ቢኖራቸውም ሰዎች ስለሆኑ ከእነዚህ ገጠመኞቻቸው የተነሳ የስነልቦናዊና ማኅበራዊ ቀውሶች ሰለባ እንደሆኑ ብንገምት ከእውነቱ አንርቅም:: እነዚህን ቀውሶች ከሕይወታቸው ለማስወገድ ምን እንዳደረጉ ባላውቅም ሁሉም በተለይ አገርን ለመምራት በፉክክር ላይ ያሉት እልባት ቢያደርጉለት መልካም ነው:: ቢፈልጉ በእምነታቸው መሠረት ወደ ውስጥ የሚመለከቱበትን ጊዜና ሁኔታ አመቻችተው ቢያንስ ከራሳቸውና ከፈጣሪያቸው ጋር ታርቀው እንደ “አዲስ” ሰው ወደ መድረክ ብቅ ማለት ይችላሉ:: ነገር ግን ሁሉም ይህንን መንገድ ይከተላሉ ማለት ስለማይቻል ፈቃደኛ ከሆኑ (የእኔ ምክር ግን አስገዳጅ እንዲሆን ነው) ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የስነልቦና አዋቂዎችን እርዳታና ምክር አግኝተው ውስጣዊ ተሃድሶ ቢያደርጉ ለእነርሱም ለኢትዮጵያ ሕዝብም ጠቃሚ ነው:: ዛሬ ቴክኖሎጂ በጣም ያደገበት ዘመን በመሆኑ የስነ አእምሮ የዕውቀት ዘርፍ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አድጓል:: የስነ አእምሮ እድገት ደግሞ የስነ ልቦናን ዘርፍ እንዲያድግ ረድቶታል:: የስነ ልቦና አዋቂዎች እንደሚሉት ከሆነ መጥፎ ወይም ክፉ ነገር ከሰው አእምሮ ውስጥ ሊጠፋ አይችልም፤ በመልካም ነገር ሲተካ ብቻ ነው በባሕርያችን ላይ ያለው ተፅእኖው የሚቀንሰው:: ቅዱስ መጽሐፍም “አሮጌውን ሰው አስወግዱ…በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ…አዲሱን ሰው ልበሱ” ይላል:: በይቅርታ እንሻገር፤በፍቅር እንደመር የሚለውመርህ በአንድ ዓመት ውስጥ ተረስቶ ቂምና ጥላቻ እያመረቀዙ ነው:: ለምን ብንል ይቅርታንና ፍቅርን ለመተግበር በሕይወታችን ውስጥ የተፈጠሩት ስነልቦናዊና ማኅበራዊ ቀውሶች አቅም ስላሳጡን ነው:: የበደሉንን ይቅር ለማለትና ሰዎችን ሰው በመሆናቸው ብቻ ማፍቀር የምንችለው ውስጣዊ ማንነታችን ሲቀየር ብቻ ነው:: ይቅርታና ፍቅር ቂምንና ጥላቻን ሲተኩ እኛም እንፈወሳለን፤ ኢትዮጵያም እፎይ ትላለች:: ስለዚህ ከሕገ መንግሥቱ በፊት መሻሻል ያለብን እኛ ነን:: ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል የእኛ ክፉ ባሕርያት ከውስጣችን መወገድ ቅድመ ሁኔታ ነው:: ሕገ መንግሥቱን ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ለማሻሻልም ሆነ ለመቀየር መቀባበል፤ የሌላውን ችግርና ስጋት እንደራስ ችግርና ስጋት መመልከት፤ መደማመጥ፤ መከባበር፤ ያለፈውን በይቅርታ መዝጋትና እንደ አዲስ መጀመር፤ ሰውንና አገርን መውደድ፣ በአጠቃላይ በጎ ባሕርያትን መላበስ ይጠይቃል:: ሕገ መንግሥቱን ያነበባችሁ ሁሉ ምን ለማለት እንደፈለግሁ ይገባችኋል:: በዚሁ አጋጣሚ መልካም አዲስ ዓመት ከአዲስ አስተሳሰብና ውስጣዊ ማንነት ጋር ለሁላችን እመኛለሁ:: ዋካንዳ ዘኢትዮጵያ
በከባድ ክብደት የዓለም የቦክስ ሻምፒዮን የነበረው ታዋቂውማይክ ታይሰን “የመጀመሪያውን ቡጢ እስኪቀምስ ድረስ ሁሉም ቦክሰኛ እቅድ አለው”ብሎ ነበር:: ቦክሰኞች ተፎካካሪያቸውን ለማሸነፍ የሚያስችላቸውን ዘዴዎች በደንብ አጥንተውና ተዘጋጅተው ወደ ፍልሚያው ቦታ ይገባሉ:: ሆኖም ከባድ የሆነ ቡጢ ፊታቸው ላይ ሲያርፍ ምድርና ሰማዩ ይዞርባቸውና የተዘጋጁበት እቅድ ሁሉ እንደ ጉም ብን ብሎ ይጠፋባቸዋል:: ማይክ ታይሰን ወደ ግጥሚያ ከመግባቱ በፊት እንዲህ ዓይነት ተግዳሮት እንደሚገጥመው በሚገባ እንደሚያውቅ ከዚህ አነጋገሩ መረዳት ይችላል:: የንግግሩ ዋናው ጭብጥ ግን አንድ ቦክሰኛ አሸናፊ መሆን የሚችለው ፊቱ ላይ ያረፈበትን ቡጢ በጽናት ተቋቁሞ፣ ይዞት የመጣውን እቅድ ከነባሪያዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ለድል መብቃቱ ላይ ነው:: በአገራችን ኢትዮጵያ “በድንገት” የተከሰቱት የለውጥ አራማጆች:-“በይቅርታእንሻገር፣ በፍቅር እንደመር” የሚል መርሕ ይዘው ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግናና እውነተኛ ዴሞክራሲ ለመምራት ከተነሱ ከዓመት በላይ ሆነው:: በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በለውጡ ላይ ብዙ “ቡጢዎች” አርፈውበታል::ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰኔ 24 ቀን 2011ዓ.ም ከተወካይ ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ ከዘረዘሯቸው ቡጢዎች በተጨማሪ በክልሎችና በፌዴራል መንግሥት መካከል ያሉ አለመግባባቶችና ተግዳሮቶች፣ በአንዳንድ ክልሎች መካከል ያሉና የነበሩ የጦርነት እምቢልታና ነጋሪቶች፣ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ከፍተኛ የሆኑ የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎች፣ ውዥንብሮች፣ በምናምንቴዎች የሚነገሩ ተራ ስድቦች፣ አሉባልታዎች፣እርሳቸው እንዳሉት እኛ የማናውቃቸው ሌሎች ሴራዎች በለውጡና በመሪዎቹ ላይ ከተሰነዘሩት ከባድ፣ መካከለኛና ቀላል “ቡጢዎች” ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው:: እነዚህ ቡጢዎች በውድ ወገኖቻችን ላይ የሕይወት፣ የአካልና የሥነልቦና ጉዳት፣ በአገራችን ላይ ብርቱ ጠባሳ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ደግሞ ድንጋጤንከዚያም ሐዘንን ከዚያም ስጋትን ከዚያም ውዥንብርን ከዚያም ተስፋ መቁረጥን እንደ ደረጃቸው አስከትለዋል፤እያስከተሉም ነው:: የለውጡም መሪዎች ሰዎች ስለሆኑ በሕዝቡ ውስጥ ለተከሰቱት እነዚህ ስሜቶች ሰለባ ለመሆናቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ ላይ ይታይ የነበረው ሐዘን፣ ቁጭትና የልብ ስብራት ምስክር ነው:: የቡጢዎቹ ዋና ዓላማ ለውጡ በታሰበለት ጎዳናና መርሕ እንዳይሄድ በማድረግ ማጨናገፍና የለውጡን አራማጆች ወይ በዝረራ አለበለዚያም በበቃኝ ከጨዋታው ውጪ ማድረግ ነው::ቡጢዎችን ተከትለው የሚሰጡ አንዳንድ መግለጫዎች፣ ዛቻዎች፣ ስድቦችና የሴራ ትንታኔዎች የዚህ ዓላማ ተቀጥላ ናቸው::ከመንግሥት አካላትም ወጥነት የጎደላቸው መግለጫዎች ለሴራ ተንታኞች ሰፊ በር በመክፈት ለዚህ ዓላማ እንደ ግብዓት በመሆን ማገልገላቸውን ልብ ልንል ይገባል:: ሌተና ጄኔራል አበባው ታደሰ በጄኔራል ሰዓረ መኮንን የአስከሬን ሽኝት ላይ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው “አንድነቱን፣ሰላሙን፣ ፍቅርን፣ መቻቻልንና ብልፅግናን” ነው:: ሕዝብ ለውጡን አይቃወምም:: እርቀሰላምን፣ ይቅርታን፣ ፍቅርን፣ ዴሞክራሲንና ብልፅግናን የሚቃወም ሕዝብ እንዴት ሊኖር ይችላል? በሕዝብ ስም ግን ለእነዚህ መልካም እሴቶች አደናጋሪ ትርጉም በመስጠት በለውጡ ላይ ቡጢ የሚያሳርፉ መኖራቸውን ግን በዓይናችን እያየን ነው:: በልመና በምትኖርና ብድሯን መክፈል ባልቻለች በዚህች ድሃ አገር ውስጥ ይኼ ሁሉ ልዩ ኃይል፣ ይኼ ሁሉ ሚልሽያ፣ ይኼ ሁሉ ዝግጅት፣ ይኼ ሁሉ የጦር መሣሪያ እንዲኖረን በተለያዩ ደረጃ ያሉና መሠረታዊ የምጣኔ ሀብት እውቀት ያላቸው መሪዎቻችን ለምን እንደፈለጉ ለእኔ ግልፅ ባይሆንልኝም ለውጡ አቅጣጫውን ስቶ ወደሌላ መንገድ ከሄደ ግን በአገራችንና ሕዝቧ ላይ የሚያስከትለውን ውድመት በዝርዝር ለማሰብ እኔ በግሌ አልፈልግም:: እርቀ ሰላም ለማውረድ ኮሚሽን ቢቋቋምም ያለ ሁላችን ተሳትፎ በጥቂት የኮሚሽን አባላት ብቻ እርቀ ሰላም ማምጣት አይቻልም:: እነርሱን ከመጠበቅ ይልቅ ቢያንስ ለጥቂት ሳምንታት ለቡጢ የምናደርጋቸውን ዝግጅቶችንና ድርጊቶችን በማቆም ለሰላም፣ ይቅርታና እርቅ ያለንን ተነሳሽነት በተግባር ብናሳይ ምናለበት?ቢያንስ አንድ ክልል ወይም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወይም አክቲቪስት ወይም የአገር ሽማግሌ ወይም የሃይማኖት መሪ ወይም መምህራን ወይም የታክሲ አሽከርካሪዎች ወይም ጋዜጠኞች ወይም አርቲስቶች ወይም … በኢትዮጵያ ውስጥ ደም የማይፈስበት ሳምንታት እንዲኖሩ ጥሪ ቢያደርጉ፣ ሌሎች ጥሪውን ተቀብለን፣ ቀን ቆርጠን፣ ያለሴራ፣ ያለግጭት፣ ያለሞት መኖር እንዲለምድብን ይህን ብናደርግ ምን ክፋት አለው? እስቲ እንጀምር? እስቲ አገራችን ከደም ትረፍ?ወገኖቼ:- ሁሉም ነገር በእያንዳንዳችን እጅ ላይ ነው:: ውድ የሆኑ ወገኖቻችንን ደም ያፈሰሰ፣ውርደት እንጂ ክብር የማያሰጥ፣ ኪሳራ እንጂ ሽልማት የማያስገኝ የጥፋት ትእይንትን ከመመልከት አገርንና ሰውን በሚፈውስ ተግባር ላይ ጊዜያችንን ብናጠፋ አይሻልምን? ለለውጡ መንስዔ የሆነው የሕዝብ እንቢተኝነትና ተቃውሞ ቢሆንም ለውጥን ግን ሕዝብ መምራት ስለማይችል የለውጡ አቅጣጫና ግብ ከፀሐይ በታች በመሪዎቹ ቆራጥነት፣ ጽናት፣ ብልሃት፣ ችሎታ፣ ልምድ ፣ብስለትና ዝግጅት መዳፍ ውስጥ ነው:: ምንም እንኳ ከዚህም ከዚያም የሚሰነዘሩ ቡጢዎች ቢኖሩም ለውጡን የሚመሩት ሁሉ ለማሸነፍ እንደተዘጋጀና ቡጢዎች ሲያርፉበት እቅዱን ከሚያጋጥሙት ተግዳሮቶች ጋር በማጣጣም ተስፋ ሳይቆርጥ እስኪያሸንፍ ድረስ በፅናት እንደሚቧቀስ ቦክሰኛ በመሆን፣ ተስፋ ሳይቆርጡ፣ የተነሱበትን ዓላማና መርሕ ባለመልቀቅ የኢትዮጵያን ታላቅነት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ፈር ቀዳጅና መሠረት ጣይ በመሆን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ታሪክ እንደሚሠሩ እምነቴ ፅኑ ነው:: በተቃርኖ የቆሙትን ወደ መሐል በመሳብ፣ መሐል ላይ የቆሙትን ከለውጡ ዓላማዎች ጋር አብረው እንዲቆሙ በመጋበዝ፣ ለለውጡ ስኬት የሚደክሙትን በማበረታታትና በመደገፍ እንደተለመደው ብልሃት የተሞላበት በሳል አመራር እየሰጡ የቡጢዎችን መጠንና አቅም እየቀነሱ እንደሚቀጥሉ ተስፋ አደርጋለሁ:: የለውጡ ዓላማዎችና ግቦች እንኳን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ለውጭ አገር ሕዝቦች ጭምር አጓጊ ናቸው:: ከአፍሪካ መሪዎች እንዴት መልካም ነገር ይወጣል ብለው በመገረም ስኬቱን የሚከታተሉ ብዙ ናቸው:: እኛ ኢትዮጵያውያን የጉዳዩ ባለቤት ስለሆንን የለውጡ መሪዎች በቡጢዎች ብዛት ተስፋ እንዳይቆርጡና የተነሱበትን ዓላማ ስተው ወደኋላ እንዳይመለሱ በቃልና በተግባር ልንደግፋቸው ይገባል:: ናፓሊዎን እንዳለው “ዓለማችን በበለጠ እየተጎዳች ያለችው በክፉ ሰዎች ዓመፅ ሳይሆን በመልካም ሰዎች ዝምታ ነው”:: በዚህ ጉዳይ ዝምታ ወርቅ አይደለም:: ኢሜል፥ [email protected] |