myEthiopia.com
  • ደወል

የአዲሱ ጅምር አብዮት ዕጣ ፈንታ

11/2/2019

0 Comments

 
0 Comments

​ዘረኝነት እኩይ እንጂ ዋልታ ረገጥ አስተሳሰብ አይደለም

11/2/2019

0 Comments

 
ዋካንዳ ዘኢትዮጵያ
 
ስንቶቻችን አስተውለን እንደሆነ ባላውቅም፥ ዘርንና እምነትን መሠረት ያደረጉ አንዳንድ ጥቃቶች የተፈጸሙት ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እግራቸው ከኢትዮጵያ ወጣ ሲል ነው:: በነዚያኑ ጊዚያት በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ያሉ ሥልጣናቸውን ያጡና ሥልጣን ላይ ለመውጣት የቋመጡ ሁሉ እኩዩን ድርጊት ሳያወግዙመግለጫ በማውጣት በፌዴራል መንግሥቱ ላይውርጅብኝ ያወርዱበታል:: ብዙ አዳማጭ እንደሌላቸው ቢያውቁትም በፕሮፓጋንዳ ኃያልነት እምነት ስላላቸው ለመላው የኢትዮጵያ “ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” በመንግሥት ላይ እንዲነሱ ጥሪ ያቀርባሉ:: ለውጡን፣ የለውጡን ግምባር ቀደም መሪዎችና ጠቅላይ ሚንስትሩን ከሚደግፈው ሕዝብ ለመነጠል እነርሱ በሚቆጣጠሯቸው፣ በሚዛናዊነት ስም የሁሉንም ድምፅ እኩል እናሰማለን በሚሉና ወሬ ካገኙ ምንም ይሁን ምን በሚያናፍሱ የመገናኛ ብዙሃንና ማኅበራዊ ሚድያዎች አማካኝነት ከፍተኛ ዘመቻ ያደርጋሉ:: እነዚህን የመሳሰሉ የተቀነባበሩ፣ ተደጋጋሚ ሴራዎችና ድርጊቶች ሲፈጸሙ የዚች ድሀ አገርና ሕዝብ ንብረት ወድሟል፣ ሁላችንም በፍርሃት ተውጠናል፣ ንፁሃን ወገኖቻችንን አጥተናል:: ሰሞኑን የሆነውም ይኸው ነው::
 
የሴረኞቹ እኩይና ዘላቂ ዓላማ ግቡን ባይመታም የአገራችን የፍትህ ሥርዓት ቀርፋፋ በመሆኑ፥ ወንጀለኞች ተገቢውን ቅጣት ሲያገኙ ባለመታየታቸው፥ ዘረኞችና መሰሪዎች የልብ ልብ አግኝተው በሐሳብ ነፃነት ስም ደረታቸውን ነፍተው ይመላለሳሉ::
ዘረኝነት ዋልታ ረገጥ አስተሳሰብ ነው ብሎ ማለት ስህተት ነው:: ዘረኝነት እኩይና አስጸያፊ ነው:: በጥቂት አገሮች ተሞክሮ አንድም መልካም ውጤት አላመጣም:: ታሪክ የሚያስተምረን ዘረኝነትና ዘረኞች ብዙ ጥፋት ካደረሱ በኋላ እነርሱም መጥፋታቸውን ነው:: በየትኛውም አገር ዘረኞች ቢኖሩም ደረታቸውን ነፍተው እንደልባቸው የሚመላለሱት ግን አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ነው:: በሌሎች አገራት ግን ብቅ ሲሉ ዘረኝነትን የሚኮንኑ ሲረባረቡባቸው ወደ ጉድጓዳቸው ገብተው ሲያሴሩ ይውላሉ::
 
ዘረኝነት ሰዎች ያልሆኑትን ናችሁ ብሎ እንዲያብጡና እንዲኮፈሱ በማድረግ፥ ሌላውን እንዲንቁና እንዲጠሉ የሚያስተምር የሰው ልጆች ጠላት ነው:: ዘረኞች መርዝን በማር፣ ጥላቻን በፍቅር ለውሰው በራሳቸው ማሰብ ላቆሙ ተከታዮቻቸው ያጎርሳሉ:: ዘረኝነትና ወገናዊነት ልዩነት አላቸው:: ወገናዊነት ወገኑን ከመውደዱ የተነሳ ለወገኑ እኩልነት፣ እድገትና ብልፅግና የሚደክም ነው:: ዘረኝነት ግን ሌላው እንዲጠፋ፣ እንዲቆረቁዝና እንዲደኸይ ሌት ተቀን የሚለፋ ነው:: ዋልታ ረገጥ ወገናዊነት ደግሞ ወደ ዘረኝነት ለመቀየር ጫፍ ላይ የደረሰ አስተሳስብ ነው:: ዘረኞች የማኅበረሰብጠንቅ (Sociopath)እናወፈፌ (Psychopath)ስለሆኑ ቦታቸው ክብር ሳይሆን የሥነ ልቦና ሕክምና ቤት ነው:: ስለዚህ የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የክልል መስተዳደሮች ዘረኝነትንና ዘረኞችን መታገስ የለባቸውም:: 
 
“…ቀኝጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤” የሚለው የወንጌል ትምህርት ለግለሰቦች እንጂ ለመንግሥት የተሰጠ ኃላፊነት አይደለም:: የመንግሥት ኃላፊነት ክፉ አድራጊዎችን መቅጣት መልካም አድራጊዎችን ደግሞ ማመስገን ነው:: ክፉ አድራጊዎችን ለመቅጣት እንዲችል አስፈላጊው የሕግ ማእቀፍና አቅም “ሰይፍ” ስለያዘ ሊጠቀምበት ይገባል::የመንግሥት ባለሥልጣናት በግላቸው ሌሎች ላደረሱባቸው በደል መታገስ ይችላሉ፤ ምርጫው የራሳቸው ነው:: በደል አድራሾች ግን በሕግ መጠየቃቸውን የእነርሱ ትዕግስት ማስቀረት የለበትም:: የፍትህ ሥርዓቱ “ማንም ሰው ከሕግ በላይ አይደለም” በሚል መርህ ላይ መቆሙ ለምንመኛት ኢትዮጵያ ጽኑ መሠረት ነው:: የፌዴራል መንግሥትና የክልል መስተዳደሮች በሚያስተዳድሩት ሕዝብና ግለሰቦች ላይ ክፉዎች በደል ሲያደርሱ “በትዕግስት” ሲያልፉ፥ መልካም አድራጊዎችን መቅጣታቸውና ክፉ አድራጊዎችን መሸለማቸው  መሆኑን ሊረዱ ይገባል:: ፈጣሪም ሕዝብም የሚወደው፥ መንግሥት ክፉ አድራጊዎችንና ወንጀለኞችን የሚቀጣ ሲሆን ነው::
 
በቀጠሮ ብዛት የሚታወቀው የአገራችን የፍትህ ሥርዓት በክፉ አድራጊዎች ላይ በፍጥነት ፍርድ መስጠት ይኖርበታል:: ፍትህ ለአንድ ሕዝብና አገር እጅግ አስፈላጊ ነው:: ክፉዎች ፍርድ አላገኙም ማለት በተበደሉ ላይ እንደመቀለድ ይቆጠራል:: ፍትህን የፖለቲካ መሣሪያ ማድረግና በሰበብ ባስባቡ ማጓተት ወንጀለኞችን ማበረታታት ነው:: እኩዮችን በተለይ ዘርንና ሃይማኖትን መሠረት አድርገው ጥቃት የፈጸሙትን ፍርዳቸውን ከነአሳፋሪ ድርጊቶቻቸው ለሕዝብ ግልፅ ማድረግም አስፈላጊ ነው:: እንደ ሰሞኑ ዓይነት ያሉ ጥቃቶች የጅምላ ጭፍጨፋ ታናሽ ወንድሙ እንጂ “የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” መብት መከበር አይደሉም::
 
የዘረኞች ኃይል እንደ እሳት የሚለበልብ ምላስና እንደልብ የሚበተን ገንዘብ ናቸው:: እነዚህ ከሌሏቸው ሽባ ናቸው:: መንግሥት የተደራጀ መዋቅሩንና የዲፕሎማሲ ግንኙነቱን በመጠቀም ምንጮቻቸውን ማድረቅ ይኖርበታል:: የዘረኞች ዕውቀትና ገንዘብ ለጥፋት እንጂ ለልማት ውሎ አያውቅም፤ በአገሪቱ ውስጥ እስካሁን የታየውም ይኼው ነው::
 
መጋቢት 18 ቀን 2011ዓ.ም ታትሞ በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ “በየትኛው ፍቅር እንደመር?” በሚለው ጽሑፌ የአገራችንን ፖለቲካ ለዜጎች መተዉ እንደሚገባ “አንቺ ምንቸገረሽ ሁለት አባት አለሽ፣ አንዱ ቢሞትብሽ በአንዱ ትምያለሽ፤” በማለት ጽፌ ነበር:: በተወካዮች ምክር ቤትማክሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)ይህንኑ ጉዳይ አንስተውት ነበር:: የሌሎች አገራት ዜግነት ያላቸው ፖለቲከኞችና አክቲቪስት ነን ባዮች አገራችን በእሳት ብትጋይ የሚሄዱበት አገር አላቸው:: እኛ ግን ያለችን ይቺው አንድ አገር ናት:: በትውልዳቸው ኢትዮጵያውያን ስለሆኑ ከሌሎች የውጭ አገራት ዜጎች በተለየ ሁኔታ መታየታቸው አግባብ ነው:: ይህ አግባብ ግን በአገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ እንጂ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት አልፎም የመንግሥትን ሥልጣን በግርግር እንዲይዙ አይደለም:: መንግሥት፥ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሆነው የሌሎች አገራት ዜግነት ያላቸውን ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት እንዲሰናበቱ፣ አሉታዊና አፍራሽ ድርጊት የሚጫወቱትን በሕግ ጠይቆ የተፈረደባቸውን ብይን ሲጨርሱ ወደ አገራቸው ማሰናበት ይኖርበታል:: ይህ ርምጃ ፍትሐዊ እንጂ አምባገነንነት አይደለም::
 
የመንግሥት ጆሮና ዐይን ሕዝብ ነው:: የአሁኑ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት ሕዝብ ስጋቱን ገልጾ ነበር:: ሰሚ ግን አላገኘም:: የአገር መከላከያ በዋናነት የተቋቋመው ከውጭ የሚመጣ ጠላትን ለመከላከል ነው:: በአገር ውስጥ ላሉት ችግሮችና ወንጀሎች ግን የፖሊስና ሚሊሻ ኃይል በቂ ናቸው:: እነዚህ ኃይሎች ውጤታማ የሚሆኑት ከዘረኝነት ነፃ መሆናቸው ሲረጋገጥና ከሕዝብ ጋር ተቀናጅተው ሲሠሩ ነውና ሕዝብን በጸጥታና ደህንነት ጥበቃ ውስጥ ተሳታፊ ማድረግ ለዘላቂ ሰላም ዋስትና ነው:: ለውጡ በታለመለት መንገድ እንዲሄድ የብዙሃኑ ፍላጎት ነውና በዚህ ለመሳተፍ ወደ ኋላ የሚል የለም::ለውጡ ቢጨናገፍ የሚተካው ሥርዓት ያለፈው ሳይሆን የባሰና የከፋ ነው:: ክግብፅ ሁለተኛው አብዮት ውድቀት እንማር::
 
የዘረኝነት ሰለባ የሆኑትን አዛውንቶች፣ ጎልማሶችንና ወጣቶችን ሥነ ልቦናና አስተሳሰብን ለመቀየር ብርቱ ትግልና ሥራ ይጠይቃል:: የእርቀ ሰላም ኮሚሽን በተለያዩ ደረጃዎች ከሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች፣ አባገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ በአገር ውስጥና ውጭ ከሚኖሩ ምሁራን፣ የክልልና ወረዳ አስተዳደሮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የሚዲያ ባለቤቶች፣ አክቲቪስቶች፣ የፖለቲካ ሰዎች፣ ወዘተ ጋር በመቀናጀት መጠነ ሰፊ የሆነ ሥራ ይጠብቃቸዋል:: የእነርሱ ሥራ አመራር መስጠት እንጂ ሥራው የሚሠራው በሌሎች መሆኑን ተገንዝበው የእርዳታ ጥሪ ቢያደርጉ መልካም ነው:: በሙያው የተካኑ ባለሙያዎችና የእርቀ ሰላምን ወቅታዊነት የተረዱ ሰዎች የተቻላቸውን ለማገዝ ይፈልጋሉ::  ነገር ግን እንዴት አድርገው ከኮሚሽኑን ጋ እንደሚገናኙ አያውቁም:: በጣም አስፈላጊ የሆነው ጉዳይ ተገቢውን ትኩረት አላገኘም ብዬ አስባለሁ:: ምክንያቱም የእርቀ ሰላሙ ኮሚሽን በሚዲያ አማካኝነት ወደ ሕዝብ ብቅ የሚለው ከብዙ ወራት በኋላ ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ስለሆነ ነው::
 
በአዳስ አበባና አካባቢዋ በፌዴራሉ መንግሥት አማካኝነት አጓጊ የሆኑ ፕሮጀክቶች ታቅደው እየተሠሩ ነው:: እነዚህ ፕሮጀክቶች ወጣቱ ጉልበቱንና ዕውቀቱን ለመልካም ነገር እንዲጠቀምበትና እርሱም እንዲጠቀም ያግዛሉ:: ክልሎች እርስ በእርስ ከመቆራቆስ ይልቅ፥ ተመሳሳይ እቅዶችና ፕሮጀክቶችን ነድፈው ቆመንለታል ለሚሉት ሕዝብ በተለይ ለወጣቱ የሥራ እድልና ተስፋ ቢፈጥሩ፥ ወገኖቹ ላይ የሚሰነዝረውን ገጀራና ዱላ ራሱንና ወገኑን በሚጠቅም ተግባር ላይ ያውለዋል::ዕውን ሊሆን የሚችል ተስፋ ለሰው ልጅ ምግብ ነው:: የዛሬው ጨለማ በነገው ብርሃን እንደሚተካ የሚያይበት መነጽር ነው:: በአዲስ አበባ ላይ የታየው ብርሃን በክልሎችም እንዲታይ የክልሎችና ወረዳ መስተዳደሮች ስብሰባንና ሴራን ቀንሰው መሬት የሚወርድ ሥራ ላይ ቢተጉ ይሻላል::
 
በመጨረሻም፥በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ ድረ ገጾችና ማኅበራዊ ሚዲያዎች አገራቸውንና መላውን ሕዝቧን የሚወዱ፣ ከተለያዩ ማኅበረሰብ የወጡ፣ የተለያየ የዕውቀትና የትምህርት ደረጃ ያላቸው ዜጎች ለኢትዮጵያ ይጠቅማል ብለው ያሰቡትን ጊዜ ወስደው ይጽፋሉ፣ ይናገራሉ፤ይመክራሉ:: የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት እነዚህን ሐሳቦች ጨምቆ ለሚመለከተው አካል ያስተላልፋል የሚል ግምት አለኝ፤ እርግጠኛ ግን አይደለሁም:: ምክንያቱም ሐሳቦቻቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የላኩ ጽሑፎቻቸው ለሚመለከተው መድረሳቸውን የሚገልጽ ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳላገኙ ከማውቃቸው ለመረዳት ስለቻልኩ ነው:: ሥራ ከበዛባቸው ቢያንስ “ራስ-ሰር ምላሽ” ከምስጋና ጋር ማድረግ ይገባቸዋል:: መንግሥት መናገር ብቻ ሳይሆን ማዳመጥ፥ ማዳመጡንም ማሳወቂያ መንገድ መቀየስ አለበት::
0 Comments

    Amharic

    Archives

    January 2022
    October 2020
    August 2020
    April 2020
    November 2019
    September 2019
    July 2019
    April 2019
    November 2018
    October 2018
    September 2018
    August 2018
    July 2018

    Categories

    All
    Current Affairs
    Sport
    The God Factor Forum

    RSS Feed

Copyright © 1999 - 2023
  • ደወል