ዋካንዳ ዘኢትዮጵያ
ዳኛው ማነው? የተሰኘውን በአምባሳደር ታደለች ኃ/ሚካኤል የተጻፈውን መጽሐፍ አንብቤ ስጨርስ እርሳቸው የጠየቁትን ጥያቄ ለመመለስ ሳወጣና ሳወርድ በመጽሐፋቸው ውስጥ ብዙ“ዳኞችን”አየሁ:: ጉልበት፣ ጠብመንጃ፣ ባለጊዜ፣ አድርባይነት፣ ርዕዮተ ዓለም በአንድ ወገን ሆነው ያሻቸውን ፍርድ ሲሰጡ፥ እንደ ኩራዝ ብርሃን ጭል ጭል የምትል በጎ ሕሊና ደግሞ ግራ ቀኙን በመመልከት እፁብ ድንቅ የሚያስብል ዳኝነትን ስትሰጥ ትታያለች:: አምባሳደር ታደለችም ይህችን በጎ ሕሊና ሲያዩ “እንዴት ሊሆን ቻለ?”በማለት አግራሞትና ጥያቄ እንደፈጠረባቸው ተገንዝቤያለሁ::እኔ እንደገባኝ የእርሳቸው የ“ዳኛው ማነው?” ጥያቄ በመግቢያው ላይ የፍትሕ በመውጫው ላይ ደግሞ የታሪክ ዳኝነትን ነው:: ዳኛ፦ ግራ ቀኙን መመልከት እንዲችል መኻል ላይ ያለ ሰው ወይም ተቋም ነው:: በአገራችን የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ግን መኻል መሆን ተወዳጅ አይደለም:: በደርግ ዘመን “መኻል ሰፋሪዎች ሚናችሁን ለዩ” በማለት መኻል ላይ የቆመ ዳኛ እንዳይኖር ተደርጓል:: መኻል ላይ የነበሩ ልክ “ከወንድሞቿ በላይ ከፍ እንዳለች ማሽላ ወይ ለወፍ አለበለዚያ ለወንጭፍ” እንደሚባለው ለአንዱ ሲሳይ ሆነዋል:: በኢህአዴግ ዘመንም ቢሆን መኻል የሚባል የለም:: አንድ ሰው በቅንነት ለአገርና ለወገን ይጠቅማል ብሎ የሚናገረውን አሳብ የነ እገሌ አሳብ ነው በማለት ይፈረጃል:: ስለዚህ የአንድ ጎልማሳ ሰውን እድሜ ያክል፥ በአገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ጭል ጭል ከምትለዋ በጎ ኅሊና በስተቀርተቋሟዊ የሆነ እውነተኛ ዳኛ አለ ለማለት ያስቸግራል:: ይህ ልምምድ ለኅምሳ ዓመታት እንደ ሸረሪት ድር አእምሯችንን ተብትቦ ስለያዘው፥ዳኝነትን የምናየው ከራሳችን አቋም አንጻር ብቻ ነው:: ስለዚህ በዳይና ተበዳይን በትክክል ለመለየት አልተቻለም:: ባለጊዜ የወደቀውን ጥፋተኛ ያደርጋል፤ እርሱ ሲወድቅ ደግሞ በሌላ ባለጊዜ ጥፋተኛ ይባላል፤ ያ በመጀመሪያ ጥፋተኛ የተባለው ደግሞ ከወደቀበት አንሰራርቶ እኔ ጥፋተኛ አልነበርኩም ይላል:: እንዲህ እንዲህ እያለ እስከዛሬ ደርሰናል:: በታሪክም ሆነ በትርክት መግባባትና መስማማት አዳጋች ሆኗል:: መወገን እንጂ መኻል ላይ ቆሞ እንደ ባለ አእምሮ ማሰብ እንደ ክፉ ነገር ተወስዷል:: ከእውነተኛ ዳኝነት ይልቅ “ሕጋዊንና ሕገወጥነትን” ቀላቅሎ መሄድ እንደ ትክክለኛ የትግል አቅጣጫ ይታያል:: ከዚህም የተነሳ ዳኝነትን የሚያዛቡ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ድርጊቶችን በእለት ተእለት ሕይወታችን ማየት እንግዳ አይደለም::ከእኛ በተቃራኒ የቆሙት ላይ ሕጋዊ ርምጃ ሲወሰድ መንግሥትን ማወደስ፥ በእኛ ላይ ሲሆን ግን መንግሥትን መሳደብ ወይም የሽምግልና ጋጋታማብዛት ልማድ ሆኗል:: ለራስ የፓለቲካ ግብ ጥቅም ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥትን ማክበርም ይሁን መጣስ ምንም ልዩነት የላቸውም:: ሕዝብን ለማደናገር ሕገ መንግሥት ሲጣስም ሳይጣስም ተጣሰ ብሎ መጮህ ለጆሮ የሰለቸ “ሙዚቃ” ነው::ሰዎች በግፍ ከቀያቸው ሲፈናቀሉ ዝም ያለ “አክቲቪስት” አፈናቃዮች በቁጥጥር ስር ሲውሉ ሰብአዊ መብት ተጣሰ ይላል:: መኻል ላይ የቆሙ ሰዎችና ተቋሟት በሌሉባት አገር “ባለጊዜ” እንጂ “ዳኛ” ሊኖር አይችልም:: ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው ለውጥ ሲመጣ “ተደምረሃል?” የሚለው ጥያቄ በተራው ሰው ዘንድ በስፋት ይጠየቅ የነበረው መኻል ላይ መሆን ትክክል አይደለም ከሚለው አጉል አባዜ የመነጨ ነው:: ለለውጡ ድጋፉን ለመግለጽ አዲስ አበባን ያጥለቀለቀው የሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ሰልፍ ተሳታፊ፥ በአገር ውስጥከሚኖሩትም ሆነ ከውጭ ከመጡ ግለሰቦችና ድርጅቶች “ኪስ” ውስጥ ለመግባት ብዙም ጊዜ አልወሰደበትም:: ምክንያቱም የለመድነው ጎራ ለይቶ መጎሻሸም እንጂ መኻል ላይ ቆሞ ግራ ቀኙን መመልከት አይደለም:: ወደ ግራም ሆነ ወደ ቀኝ ፈጥኖ ከመግባት መኻል ላይ ቆሞና መዝኖ የሚበጀውን መምረጥ የተሻለ ነበር:: እንግዲህ እውነተኛ ዳኛ የምንፈልግ ከሆነ መኻል ላይ የቆሙ ግለሰቦችና ተቋሟት ያስፈልጉናል:: ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች ጋር በነበራቸውየውይይት ጊዜ “ሲቪክ ሶሳይቲ ሚዛን የሚያስጠብቅ” ነው በማለት መኻል ላይ ያለ ተቋምን አስፈላጊነት ተናግረዋል:: ይህ መኻልላይ ላሉና ለመሆን ለሚፈልጉ ትልቅ ተስፋ ነው:: ምክንያቱም ከረጅም ዓመታት በኋላ መኻልላይ መቆም ጥሩ መሆኑን ከገዢው ፓርቲና መንግሥት በይፋ ስለሰማን ነው:: ይህ መልካም ጅምር ከግብ እንዲደርስ የፓለቲካ ፓርቲዎችና መንግሥት መኻል ላይ ያሉ ተቋማትን ለራስ ፍላጎት መጠቀሚያ ከማድረግ መቆጠብ ይኖርባቸዋል:: ተቋማቱም የመንግሥትና የፓለቲካ ፓርቲዎች መጠቀሚያ ከመሆን ራስን ማጽዳት ይጠበቅባቸዋል:: ይህ ሲሆን በአገራችን ኢትዮጵያ ዳኛ ይኖራል፣ ዴሞክራሲም ያብባል፣ በጎ ሕሊና ያላቸው ትልቅ ሰዎችም ይበዛሉ:: ከዚህ በተጨማሪ ብዙ የተባለለት የፍትሕና ርትእ አካሉ መኻል መሆን እጅግ አስፈላጊ ነው:: በዚህ አካል ላይ የፓርቲዎችም ሆነ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ለቡድን እንጂ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ መልካም አስተዳደር፣ እድገትና ዴሞክራሲ ጥቅም የለውም:: በጎ ሕሊና ያላቸው፣ መኻል ላይ የቆሙ፣ ለእውነት ተገዢ የሆኑ፣ ለገንዘብ የማይጓጉ፣ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ ሰውን የሚያከብሩ፣ በሙያቸውና በስብእናቸው የተከበሩ ሰዎችን በዚህ ተቋም ውስጥ ማብዛት እውነተኛ ዳኛ እንዲኖረን ያደርጋል:: የኃይማኖት ተቋማትም መኻል ነበሩ ማለት አይቻልም:: ባለጊዜና ጉልበተኛ ወደፈለገው ሲጎትታቸው፣ እንደፈለገው ሲያምሳቸው ብዙ ዓመታትን አስቆጥረዋል:: ዛሬም ቢሆን ሳይጎተቱ ለመጎተት ራሳቸውን ያዘጋጁ፣ ጭርስኑ ጎራ ለይተው ከፓለቲከኞች የማያንስ የመከፋፈል ሥራ የሚሠሩ የኃይማኖት መሪዎች ይስተዋላሉ:: በግላቸው የፈለጉትን መሆን ይችላሉ፤ ተቋሙን ግን መኻል ላይ እንዲቆም መተው ለኃይማኖቱም ለአገርም ይጠቅማል:: ምክንያቱም የኃይማኖት ተቋማት መኻል መሆን በጎ ሕሊናና ሚዛናዊነት ያላቸው ዜጎችን በማዘጋጀት እውነተኛ ዳኞች እንዲኖሩን ያደርጋል:: በእኔ እይታ እስካሁን ድረስ በሙስሊሙም ሆነ በክርስቲያኑ ዘንድ የዳኝነትን ማዕረግ የተጎናጸፉ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ ይመስሉኛል::እርሳቸውን ያነሳሁት ታዋቂ ስለሆኑ ነው እንጂ ብዙ ሰው የማያውቃቸው፣ ሚዛናዊ የሆኑ፣ የሚመሩትን ምዕመን በጎ ሕሊና እንዲኖረውና እንዲያመዛዝን የሚያስተምሩ መኖራቸውን አውቃለሁ:: እንደ እነዚህ ዓይነት ያሉ መሪዎችን በሁሉም የእምነት ተቋማት ፈጣሪ እንዲያበዛልን ምኞቴ ነው:: ሰው አእምሮ ያለው ፍጡር ነው:: የተፈጠረውም ማመዛዘን እንዲችል ሆኖ ነው:: ስለዚህ የሰው ልጅ የሆነ ሁሉ መኻል ላይ በመቆም የሠራቸውንና የሄደበትን ጎዳና ለማየት ከሕሊናው ጋር የሚሟገትበት ጊዜ ሊኖረው ይገባል:: በራሱ ላይ ዳኛ ያልሆነ እንዴት ብሎ ሌላውን ሊዳኝ ይችላል? ሕሊናን የጣለ ሰው መሪ ከሌለው መርከብ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ከአደጋ አያመልጥም:: ሲሳሳት የማይጸጸት ሰው ሕሊናውን ጥሏልና ከሰው ተራ ወጥቷል:: መኻል ላይ የቆሙ ሰዎች ብዙዎችን ከስህተት ይታደጋሉ:: በጎ ሕሊና ያላቸውና መኻል ላይ የቆሙ ሰዎች (ወላዋይ ማለቴ አይደለም) ኖረው ቢሆን ኖሮ ብዙ ወገኖቻችን በሕይወት ይኖሩ ነበር:: በመጨረሻም፥የተጀመረው ለውጥ ግንባር ቀደም መሪዎች ከላይ የዘረርኳቸው ተቋማት ፍሬ እንዲያፈሩ የድርሻቸውን ይወጣሉ የሚል እምነት አለኝ:: ነገር ግን እንደ ቀደምቶቹ ባለጊዜዎችና ጉልበተኞች፥ መኻል ላይ የቆሙትን በማሸማቀቅ፥ የሰውም የተቋማትም ዳኞች ማፍራት እንዳንችል ቢያደርጉ፥ የታሪክ አቅጣጫን የሚዘውር፣ መንግሥታትን የሚያስነሳና የሚጥል ፈጣሪ የምን ጊዜም ዳኛ መሆኑን መርሳት የለባቸውም:: የእርሱ ዳኝነት በዚህም በወዲያኛው ዓለም ነውና በተቻለን መጠን በእርሱና በሰዎች ዘንድ በጎ ሕሊና እንዲኖረን መትጋት ለሁላችንም ይበጃል::
0 Comments
|