myEthiopia.com
  • ደወል

እንዴት በይቅርታ እንሻገር

11/24/2018

0 Comments

 
ዋካንዳ ዘኢትዮጵያ

በአገራችን ኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው ለውጥ ማዕከል ካደረጋቸው መርሆዎች ውስጥ አንዱ “በፍቅር እንደመር፤በይቅርታ እንሻገር” የሚል ነው:: የዚህ መርህ ተናጋሪና በሕዝቡ ውስጥ ሰርፆ እውን እንዲሆን የመሪነቱን እርፍ የጨበጡት ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ናቸው:: ብዙዎች “በፍቅር እንደመር” ላይ ጥያቄ ባያነሱም “በይቅርታ እንሻገር” ላይ ግን የተለያዩ አስተያየቶች በተለያዩ መንገዶች እየሰጡ ነው:: ኢትዮጵያውያን በመደብ ትግልና በርዕዮተ ዓለም ስም፣በፓለቲካ ሽኩቻ፣በዘርና ቋንቋ አንዳንዴም በሃይማኖት ልዩነቶች እርስ በርሳቸውና በአምባገነኖች ለሞትና የአካል ጉድለት፣ለሥቃይና ስደት፣ ለመሳሰሉት ሲዳረጉ አገሪቱ ደግሞ ለድህነት፣ኋላ ቀርነት፣የሀብት ብክነትና ዘረፋ ተዳርጋለች:: ክቡር የሆነው የሰው ልጅ እንደ ግል ንብረት የተፈለገው በተደረገበትና እየተደረገ ባለበት አገርበ“ይቅርታ” ጉዳይ ላይ ውዝግብና ውዥንብር ከመፍጠር ይልቅ ሰፊ ውይይት አድርጎ መግባባት ላይ መድረስና እልባት መስጠት ተገቢ ነው:: ምክንያቱም “ይቅርታ” ክቡር፣ ያለፈን ቋሻሻ ታሪክ ዘግቶ ለሰዎችና ለአገር ፈውስ የሚያመጣ ሐሳብና ድርጊት ስለሆነ ነው:: አለባብሰውም ሆነ ንቀው ቢያልፉት ጊዜ ጠብቆ በማገርሸት ብልጭ ያለችውን የእድገታችንን ተስፋ ይገታብናል፤ ነፃነታችንን ያጨልምብናል:: ይቅርታ መጠየቅና ይቅርታ ማድረግ በፈጣሪና በሰዎች መካከል ያለ ግንኙነት በመሆኑ ሰዎች እርስ በርሳቸው ይቅር ሲባባሉ ፈጣሪም ደስ ይለዋል፤የእርሱን ፈለግ ተከትለዋልና!ስለዚህ ከይቅርታ ጋር ተዛምዶ ያላቸውን አስተሳሰቦችና ቅድመ ሁኔታዎችን በጥንቃቄ ተመልክቶ፣የደቡብ አፍሪካ፣ሩዋንዳ፣ላቲን አሜሪካና የመሳሰሉትን አገራት ልምድንም ዳስሶ፣የራሳችንን እሴቶች፣አቅምና አእምሮ ተጠቅመን፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅም ድምዳሜ ላይ መድረስ አስፈላጊ ነው:: 
 
“ይቅርታ” ትርጉም የሚኖረው በዳይና ተበዳይ ሲኖሩና ሁለቱም ወገኖች ቢያንስ በመርህ ደረጃ ይቅር ለመባባል ዝግጁ ሲሆኑ ነው::በሂደት የበደለ ይቅርታ እንዲያደርግለት ተበዳይን ይጠይቃል፤የተበደለ ደግሞ ይቅርታ ያደርጋል:: ወይም የተበደለ በዳይን በጥፋቱ ይወቅስና በዳይ በጥፋቱ ተፀፅቶ ይቅርታን ይጠይቅና የተበደለው ይቅርታ ያደርግለታል:: “ይቅርታ” በማኅበረሰቡ ዘንድ የተለመደ ቃልና ድርጊት ከመሆኑ የተነሳ ቀላል ቢመስልም ከእርሱ ጋር አብረው የሚሄዱት መልካም እሴቶችና ተጓዳኝ ሐሳቦች ውስብስብ ያደርጉታል:: እነዚህ መልካም እሴቶችና ተጓዳኝ ሐሳቦች፦ሰላም፣እውነት፣ፍትህና ምሕረትናቸው:: ሁሉም በጎ ናቸው፤ ነገር ግን በይቅርታ ጎዳና ላይ ሁሉንም ለሟሟላት ስንሞክር የይቅርታው መንገድ ተወሳስቦ ውሉ ይጠፋብናል:: ባልና ሚስት ወይም አገራት መታረቅና ይቅር መባባል የሚያስቸግራቸው በክፉ ነገሮች ምክንያት ሳይሆን በነዚህ መልካም እሴቶች ለመስማማት ወይንም እነሱን አስማምተው ለመሄድ ባለመቻላቸው ነው:: በኔ አስተሳሰብ ለይቅርታ ስኬታማነት የነዚህን እሴቶች ማንነት፣ከይቅርታ ጋር ያላቸውን ዝምድና መመልከትና መረዳት፤ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር አገናዝቦ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው::
 
እስቲ የይቅርታን ተጓዳኝ ሐሳቦች አንድ ባንድ እንመልከት::
 
ሰላም
 
“ሰላም” በዳይና ተበዳይ ወይም የተቃቃሩ ወገኖች በመካከላቸው ያለውን መጠቃቃት በማቆም ረጋ ብለው ለመነጋገር፣ሰዎች በቤታቸው፣በአካባቢያቸውና በየትኛውም የአገራቸው ክፍል ያለምንም ፍርሃት ለመዘዋወር፣ለመስራትና ለመኖር የሚያስችላቸው መልካም ድባብ ነው:: የመጠቃቃቱ መጠን ከመበሻሸቅ፣ ከስድብና በመጥፎ ቃላት ከመወነጃጀል አልፎ አካላዊ ጥቃትን ተሻግሮ እስከ መገዳደል ሊደርስ ይችላል:: እስከ አሁን ያለው የአገራችን ፖለቲካ “ጭር ሲል አይወድም”፤”ጠላት” ይፈልጋል:: ያ “ጠላት” እንዲፈራ፣እንዲሸማቀቅና እንዲጠላ ስያሜ ይሰጠዋል፦ዘውድ ናፋቂ፣ አናርኪስት፣ ፋሺሽት፣ ባንዳ፣ መሐል ሰፋሪ፣ ቀኝ መንገደኛ፣ ግራ ተስፈንጣሪ፣ ገንጣይ፣ አስገንጣይ፣ ፀረ-ቻርተር፣ ትምክህተኛ፣ ጠባብ፣ ዘረኛ፣ ጀብደኛ፣ ተንበርካኪ፣ ኪራይ ሰብሳቢ፣ እረ ስንቱ! ለ”ጠላት” ቶሎ ብሎ ስያሜ መለጠፍ “ጠላትን” ለማጥቃት የሚያስችል ፖለቲካዊ ጥበብ እንደሆነ ተወስዶ ቢሆንም እንኳ ለእኛ ግን ተከፋፍለን እንድንባላ አደረገን እንጂ አልጠቀመንም:: ንግግሮቻችን ሰውን በአንድ “ሳጥን” ውስጥ በመክተት ስለሚጀመሩ ከምክንያታዊ ክርክርና ውይይት ይልቅ ንትርክ፣ስድብና ዛቻ የተሞሉ ሆነው ከዚያም አልፈው ወደ አካላዊ ጥቃትና ግድያ አድርሰውናል፣እያደረሱንም ነው::  ሰዎች ወደ አካላዊ ጥቃትና ግድያ የሚደርሱት፦


  1. ረጋብለው መነጋገር ሲያቅታቸውና በሂደትበሚለዋወጧቸው ቃላቶች በመቆሳሰል ጥላቻን ሲያዳብሩ፣ወይም
  2. ሐሳባቸው ተደማጭነት ሳያገኝ ይቀርና ጉልበት ተጠቅመው ልክ ለማስገባትና ሐሳባቸውን ለማስፈጸም፣ ወይም
  3. በጉልበተኞች ከሚደርስባቸው ጥቃት ራሳቸውን ለመከላከል ሊሆን ይችላል:: 
 
እንዲህያሉት ድርጊቶች የሚከወኑት በፖለቲካ ድርጅቶችና በአገራት መካከል ብቻ ሳይሆን በግለሰቦች፣በቤተሰብ፣በባልና ሚስት ጭምርም ነው:: ለምሳሌ በባልና ሚስት መካከል የሚታዩት አካላዊ ጥቃቶችና ፍቺዎች ምክንያቶቹ ብዙ ቢሆኑም መሰረታዊ ምንጩ ግን ሐሳብን በርጋታ ለመነጋገር አለመቻል ነው::ስለዚህ ረጋ ብሎ መነጋገርና መደማመጥ ለሰላም አስፈላጊ ነው:: የአንደበትን አዎንታዊና አሉታዊ ሚናን መናቅ ተገቢ አይደለም:: መጽሐፉ “አንደበት እሳት ነው” ደግምም “ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ” ይላልና!
 
ያለ “ሰላም” ስለይቅርታና ፍቅር መነጋገር አይቻልም:: ጎራ ለይተው በነፍጥ የሚፋለሙ ድርጅቶችም ሆኑ አገራት ስለይቅርታናእርቅ ከመነጋገራቸው በፊት የተኩስ ማቆም ስምምነት ማድረግ አለባቸው:: በተቃራኒ ወገን ቆመው በተለያየ መንገድ ሲቆራቆሱ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶችና ፓርቲዎች እርስ በርስ መበሻሸቃቸውን፣መወነጃጀላቸውን፣መሰዳደባቸውንና መገዳደላቸውን ቆም ማድረግ አለባቸው:: እገሌ የተባለው ድርጅት እንዲህና እንዲህ ነው እየተባባሉ ስለይቅርታ ማሰብ ከእውነታ ራስን መነጠል ነው:: ስለዚህ ይቅር ለመባባል መንገድ ስንጀምር የክላሽንኮቭ ትጥቅን ብቻ ሳይሆን የስድብ፣ የዝልፊያና የመበሻሸቅ ትጥቅንም መፍታት ያስፈልጋል::
 
ዘላቂ ሰላምን በኢትዮጵያ ለማምጣት ትልቅ አስተዋጽዖ ከሚኖራቸው ተቋማት ውስጥ አንዱ የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎቻቸው ናቸው:: ምክንያቱም አብዛኛው የአገራችን ሕዝብ ሃይማኖት ስላለው ነው:: ዛሬ ከተለየዩ የአገራችን ክፍሎች ሰዎችን የሚያፈናቅሉና የሚገሉ ሰዎች በአገራችን ውስጥ ካሉት የአንዱ እምነት ተከታዮች ናቸው ብንል ስህተት አይሆንም:: እንደ ጠላት ቆጥረው የሚያንገሏቷቸው ወገኖች ምናልባትም ከነሱ ጋር ተመሳሳይ እምነት ያላቸውና በአንድ ወቅት አብረው ፈጣሪያቸውን ወደሚያመልኩበት ቤተ-እምነት ይሄዱ የነበሩትን ነው:: በወዲያኛው ዓለም ከተለያዩ የዓለም ሕዝቦች ጋር ለዘላለም አብረን እንኖራለን የሚል እምነት ያላቸው ሰዎች በአጠገባቸው ሌላ ቋንቋና ባህል ካላቸው ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር ለአጭር ዘመን መኖር አለመቻላቸው የሃይማኖት መሪዎች ብዙ ስራ እንደሚጠብቃቸው አመላካች ነው:: የፖለቲካ ሰዎች ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን አጉልተውሲሰብኩ የሃይማኖት መሪዎች ፍቅርንና አብሮ መኖርን  ሰብከው ቢሆን ኖር ዛሬ ክቡር በሆኑት የሰው ልጆች ላይ የምናየው መፈናቀልና ሞት ቢያንስ በጣም ውስን ይሆን ነበር:: አለመታደል ሆኖ የሃይማኖት መሪዎች የጊዜው ፖለቲካዊ አስተሳሰብና ሸር ሰለባ ሆነው እርስ በርሳቸው ሲጠላለፉ የኢትዮጵያን ሕዝብከጥላቻና ከዘረኝነት ሊታደጉት አልቻሉም:: ዛሬ የተሻለ እድል በኢትዮጵያ ስላለ የሃይማኖት መሪዎችና ተከታዮቻቸው ባለፈው ቸልተኝነትና ጥፋቶቻቸው ንስሐ ገብተው  ተከታዮቻቸው ፈሪሀ-ፈጣሪ እንዲኖራቸውና የሰው ልጅን ክቡርነት እንዲረዱ በማስተማርና ምሳሌ በመሆን ቶሎ ብለው የድርሻቸውን ቢወጡ ሰላምን ለማስፈን ስኬታማ እንደሚሆኑ አያጠራጥርም፤ ለመንግሥትም ሸክሙ ቀላል ይሆንለታል:: 
 
ለሰላም ሌላው ትልቅ ድርሻ ያላቸው የአገር ሽማግሌዎች ናቸው:: በቅርቡ በአዲስ አበባ አካባቢ በተደረገው ግድያ፣ ዝርፊያና መፈናቀል ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ግፍ ተፈጽሞባቸዋል ብለው የተቆጡ የአርባ ምንጭ ነዋሪዎችን የጋሞ የአገር ሽማግሌዎች ልጆቻቸውና ወንድሞቻቸው ወደ ጥፋትና በቀል እንዳይሄዱ በባህላቸው መሰረት እርጥብ ቅጠልና ሳር ይዘው በመማፀን ሊመጣ የነበረውን ጥፋት በማስቆም ሰላምን አምጥተው ሁላችንንም አስደንቀውናል:: ፈጣሪ ረጅም ዕድሜ ከጤንነትና በቂ ሀብት ጋር ያብዛላቸው:: ይህ  የእርቅ ተምሳሌት ለጋሞ ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ተስፋ ነው:: ምክንያቱም ሽማግሌን የሚያከብር ማኅበረሰብ መኖሩንና ይህ የአገራችን ትልቅ እሴት እንዳልሞተ ያሳየ በመሆኑ ነው:: ስለዚህ እንዲህ አይነት የተከበረ ድርጊት በአባገዳዎችና በሌሎችም የአገር ሽማግሌዎች ቢደረግ የሕዝባችን ሰቆቃ አክትሞ፣ ሰላምም ሰፍኖ፣ ይቅር ለመባባል የሚያስችለን ድባብ ኖሮን የምንመኛትን አገር መገንባት ላይ በሙሉ ኃይላችን ለማተኮር እንችላለን::
 
የተጀመረውን ለውጥ ለመደገፍና ግቡን እንዲመታ ስለምንፈልግ “ተደምረናል” የሚሉ አክቲቪስትና ፖለቲከኞች እንኳ “በፍቅር እንደመር በይቅርታ እንሻገር” የሚለው እሳቤ ከወህኒ እንዲወጡና ወደ አገራቸው እንዲገቡ ያስቻላቸው መሆኑን በፍጥነት ረስተው በድል አድራጊነት መንፈስ በየቦታው በመሄድና ሚዲያን በመጠቀም “በፍቅር እንደመር፤ በይቅርታ እንሻገር”የሚለውን ሐሳብ የተቃርኖ በሚመስል መንገድ የራሳቸውን አስተሳሰብና እምነት ላይ ብቻ ሲያተኩሩ ለመታዘብ ችለናል:: የራሳቸውን አስተሳስብና እምነት ለደጋፊዎቻቸውና ለሚሰሟቸው መናገራቸው ጥሩ ቢሆንም ለውጡን መደገፍ ማለት የለውጡን አብይ እሳቤ ማስተጋባትም መሆኑን መርሳት የለባቸውም:: ለነሱ የሆነላቸው ይቅርታና ፍቅር በአገሪቷ ለሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ ስለሚያስፈልግ ሰከን ብለው ሕዝቡንም በማስከን ሰላም ቦታዋን ይዛ ለይቅርታና ፍቅር ምቹ ድባብ እንድትፈጥርላቸው በማድረግ ለውጡን መደግፍ ይኖርባቸዋል:: 
 
በተፈጥሮው፥ ሰው ከእንጀራ በተጨማሪ “ወሬ” ይፈልጋል፤ መናገር፣ መስማትና ማንበብ ይፈልጋል:: በተለይ አጓጊ የሆኑ ወሬዎች ትኩረቱን ይስቡታል:: ለዚህም ነው አንዳንድ “ዩ ቲዩበሮች” ሰበር ዜና፣ አስደንጋጭና አስደሳች ዜና ብለው የሚያስተዋውቁት:: ይህንን ፍላጎቱን ለማርካት ጎረቤቱን “ምን ተወራ” ብሎ ይጠይቃል፣ አቅሙና ሁኔታዎች እንደፈቀዱለት ወደተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ጎራ ይላል:: የመገናኛ ብዙሃንም መልካምና እውነትን ከመገቡት ቀናና በጎ ይሆናል፤መጥፎና አሳሳች ነገርን ከመገቡት ጠማማና ክፉ ይሆናል:: ስለዚህ የመገናኛ ብዙሃን ምንም እንኳ የተቋቋሙበት የራሳቸው ዓላማና ግብ ቢኖራቸውም በፕሮግራሞቻቸው ውስጥ የሰላምንና አብሮ የመኖርን አጀንዳ ጣልቃ እያስገቡ የአስተማሪነት ድርሻቸውን ቢወጡ በማኅበረሰቡ ላይ በጎ ተፅእኖ በማምጣት ሰላም ቦታዋን እንድትይዝ ያደርጋሉ:: 
 
ገዢውን ፓርቲ የመሰረቱት ድርጅቶች፣ አጋር ድርጅቶቻቸው፣አባላትና ደጋፊዎችም ቢሆኑ ለውጡ የጥልቅ ተሃድሶ ውጤት ነው ብለዋልና በመካከላቸው ያላቸውን ልዩነቶች በሰከነ መንፈስ አቻችለው ከመግለጫ ማውጣት ባሻገር በተግባር ሰላምን ለማስፈን በግንባር ቀደምትነት ሌት ተቀን መስራት አለባቸው:: 
 
ይህ ለውጥ እንዲመጣ እልህ አስጨራሽ የሆነ ሰላማዊ ትግል በማድረግ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለው ወጣት ጥያቄዎቹ ሊመለሱለት የሚችለው ለውጡ ስኬታማ ሲሆን ብቻ መሆኑን ተረድቶ ሰላምን በሚያደፈርስ ወሬና እንቅስቃሴ ባለመሳተፍ፣ ብዙዎች አካላታቸውንና ህይወታቸውን የገበሩለትን ለውጥ እንደ አይኑ ብሌን በመጠበቅ፣ ከእልህ፣ ከጉልበተኝነትና ስሜታዊነት በመቆጠብ ለሰላም በጥበብና በጥንቃቄ ጉልህ ሚና ሊጫወት ይገባል::
 
ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ሰላምን ለማስፈን ቁርጠኛ መሆን ትልቁ የቤት ሥራው እንደሆነ መዘንጋት የለበትም:: ግጭትን የሚፈጥሩ፣ሰውን የሚያፈናቅሉ፣ ሕዝብን ከሕዝብ የሚለያዩ፣የጦር መሳሪያ የሚያዘዋውሩ፣ የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈጽሙ፣ በዘር ላይ ተመስርተው ጥቃትንና ግድያን የሚፈጽሙና የሚያስፈጽሙትን ያለማዳላት  “በሕግና በሕግ” ብቻ መቅጣት ይኖርበታል:: “በሕግና በሕግ” ብቻ የሚለው ሊሰመርበት ይገባል፤ ምክንያቱም በአገራችን የሕግ የበላይነት ሲባል “ግንባር ግንባሩን” በለው ማለት የሚመስላቸው አይታጡምና::
 
እንግዲህ ያለፈውን በይቅርታ ዘግተን ለወደፊት በፍቅር ተያይዘን አገራችንን በዴሞክራሲና በልማት ለመገንባት እንችል ዘንድ ሁሉም ወገን  “ተኩስ” በማቆም በሰለጠነ መንገድ ለመነጋገር ዝግጁ መሆን ይኖርበታል:: ሰላም የዶክተር ዐቢይና ለውጡን በግምባር ቀደምትነት የሚመሩት ግለሰቦች አጀንዳ ነው ብሎ የሚያስብ ካለ ለአገራችንና ሕዝቧ ደንታ የሌለው ሰውና ድርጅት ነው:: የሰላም አለመኖር፥ የለውጡ መቀልበስና የአገራችን መፈራረስ ነውና ሁላችንም የበኩላችንን ማበርከት አለብን::
 
“ሰላም” ለታሰበው የይቅርታና የዘላቂው ሰላም ጉዞ ቅድመ ሁኔታ ብትሆንም በተለያየ የፖለቲካ አስተሳሰብና ርዕዮት የተንቆራቆሱና የሚንቆራቆሱ ቡድኖች “ሰላም ሰላም” ብለው ቢዘምሩም በተግባር ግን ስለ ሰላም የሚኖራቸው አቋም የተለያየና እንዲያውም በተቃራኒው ሊሆን ይችላል::


  1. ሁሉም ድብቅም ሆነ ግልፅ አጀንዳቸውን የሚያስፈጽምላቸው አለመረጋጋት ነው ብለው በማሰብ፤ላይ ላዩን ስለ ሰላም በማውራት ሰላምን የሚያሳጣ ተግባርና ወሬ ላይ ሊያተኩሩ ይችላሉ:: ለዚህ ደግሞ ማኅበራዊ ድረ ገፆችና መገናኛ ብዙሃን ብዙ አስተዋፅዖ ያደርጋሉ:: እነሱንም በመጠቀም አንዱ አንዱን በመወንጀል ለሰላም መደፍረስ ተጠያቂ ለማድረግና የሕዝብድጋፍ ለማግኘት ደፋ ቀና ሊሉ ይችላሉ::
  2. አንዱ ወገን ስለ ሰላም ተግቶ ሲሰራ ሌላኛው ወገን ከእግር እግሩ ስር እየተከተለ የተሰራውን በማፍረስ ወይንም ቀድሞ የቤት ስራ እየሰጠው ሰላም እንዳትመጣ እኩይ ስራ ሊሰራ ይችላል::
  3. ሁሉም የሰላም አለመኖር ግቡ መጠፋፋት መሆኑን ተገንዝበው፣የሰላም መኖር ደግም ለይቅርታ በር ከፋች መሆኑን በመረዳት ሰላምን ለማምጣት አብረው በመስራት ለራሳቸውም ሆነ ለደጋፊዎቻቸው እፎይታን ሊያጎናጽፉ ይችላሉ:: ለምሳሌ በኢትዮጵያና ኤርትራ በቅርቡ የተጀመረው የሰላም ጉዞ ለሁለቱ አገርሕዝቦች በተለይ ደግሞ በድንበር አካባቢ ላሉት ምን ያክል እፎይታና ደስታን እንደሰጠ ምስክሮች ነን፡፡
 
ከሰላም እጦት የሚያተርፉ ምናልባት ለውጡን የማይደግፉና ግርግር ስልጣን ላይ ያወጣኛል ብለው የሚያስቡ ሊሆኑ ይችላሉ:: በኢትዮጵያ አውድ ግን እነርሱም መጠቀማቸውን እጠራጠራለሁ:: ስለዚህ ለአገራችን ህልውና፣ለይቅርታ፣ለብልፅግናና ዴሞክራሲ ከሰላም ውጭ አማራጭ ስለሌለን ሁላችንም ከልባችን ለሰላም መስፈን ከአንደበታችን ጀምሮ እስከ ቃታ የሚስብ ጣታችን ድረስ ለሰላም በማስገዛት አስተዋፅዖ ማድረግ ይኖርብናል::ከዚህ ጋር አብረን መገንዘብ ያለብን፦ ለይቅርታ ሰላም እጅግ አስፈላጊ የመሆኗን ያክል ያለ ይቅርታ ዘላቂ ሰላም ማምጣት አይቻልም:: ምክንያቱም የይቅርታ አለመኖር ቂምን ህያው ያደርግና እሱም ቀኑን ጠብቆ አቅም ሲያገኝ የበቀል በትሩን ሲዘረጋ ሰላም ትደፈርሳለች:: ከለመድነው የቂምና የበቀል ዑደት ለመውጣት “በይቅርታ መሻገር” ይበጃል:: ስለዚህ ለሰላም የምንጮኸውን ያክል ለይቅርታም መጮኽ ይገባናል::
 
እውነት
 
እውነት የይቅርታ ጓደኛ ናት:: የበደለንና የተበደለን የምትለየው እውነት ናት:: ያለ እሷ ይቅርታ ትርጉም የለሽ ትሆናለች:: አንድ ሰው ተበድያለሁ ስላለ ተበድሏል ማለት አይቻልም:: በአንፃሩም የበደለ ምንም አላጠፋሁም በማለቱ ንፁህ ሊሆን አይችልም:: ስለዚህ በዳይንና ተበዳይን ቁልጭ አድርጋ የምታሳይ እውነት በዚህ ጊዜ ታስፈልጋለች::

ለምሳሌ: ኢህአዴግ ለረጅም ዓመታት “በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ እስረኛ የለም” ሲል ነበር:: ይህንን ሲል እኔ ማንንም አልበደልኩም፣ ነገር ግን ወንጀለኞችን በማሰር ሕግን አስከብሬያለሁ ማለቱ ነበር:: ይህን ስላለ ንፁህ ነው አላስባለውም:: እውነት ግን ይህ አባባል እውነታ እንዳልነበረው አሳይታናለች:: እውነት የነገሩ መነሻ ምን እንደነበረ፣ማ ምን እንዳደረገና ለምን እንዳደረገ፣ቦታውን፣ጊዜውን፣የጠፋውን ጥፋትና ጉዳት መጠን ነቅሳ አውጥታ የበደለንና የተበደለን በግራና ቀኝ አሰልፋ ታሳየናለች:: እውነት ይህንን ሁሉ አድርጋ ለይቅርታ መንገድ ብትከፍትም በራሷ ይቅርታን ወዲያውኑ ታመጣለች ማለት አይቻልም:: ምክንያቱም እውነቱ ከታወቀ በኋላ በዳይና ተበዳይ የሚከተሉትን ማድረግ ስለሚችሉ ነው::


  • ሁለቱም ወይም አንዳቸው እውነትን በመቃወም በእውነት ላይ ዘመቻ ሊያደርጉ ይችላሉ:: ይህ ሊሆን የሚችለው ሁለቱም ወገኖች ወይም አንዳቸው እውነትን በአድሏዊነት በመክሰስ ነው:: ለምሳሌ: በቅርቡ የኢንጂነር ስመኘው በቀለን አሟሟት በተመለከተ የፌደራል ፖሊስ የሰጠው መግለጫ ተቃውሞ ገጥሞታል:: ፖሊስ የራሴንና የሌሎችን ሙያ ተጠቅሜ የደረስኩበት ድምዳሜ ነው ቢልም እንኳ የሁሉንም ሰው አመኔታ አላገኘም:: ይህን የፓሊስ ድምዳሜ ለዚህ ችግር ከዳረጉት ምክንያቶች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ:-
    • ሀ. የምርመራው ውጤት ከመውጣቱ በፊት የተለያዩ አስተያየቶችና እውነት መሰል መረጃዎች በድረ ገፆችና በማኅበረ ሚዲያዎች ስለተለቀቁ የማኅበረሰቡን ሚዛናዊነት አዛብተውት ስለነበር
    • ለ. ወንጀሉን ሰርተዋል ተብለው አስቀድመው የተፈረጁ ቡድኖችና ግለሰቦች በማኅበረሰቡ ዘንድ ስለነበሩና የምርመራው ውጤት በማኅበረሰቡ ውስጥ ከተሰራጩት ግምቶች የተለየ በመሆኑና
    • ሐ. የኢትዮጵያ ሕዝብለረጅም አመታት በመንግሥት ባለስልጣናትና ተቋማት ሲዋሽ ስለነበር ከነዚህ ባለስልጣናትና ተቋማት የሚወጡትን መግለጫዎች እውነት ናቸው ብሎ ለመቀበል ስለሚቸገርም ነው:: 
የኢንጂነሩን ጉዳይ በምሳሌ ያነሳሁት የእርሳቸው የአሟሟት ምርመራ ውጤት ትክክል ነው ወይስ አይደለም የሚል ክርክር ለማንሳት ሳይሆን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ተነስቶ “የእውነትን እውነተኛነት” ለማወቅ ምን ያክል ከባድና ፈታኝ መሆኑን ለመረዳት ያስችለናል በሚል ነው::
  • የተበደለ የይቅርታ ሌላ ጓደኛ የሆነችውን ፍትህን በመጥራት እሷ በነገሩ ውስጥ ካልገባች ይቅርታ ብሎ ነገር መስማት አልፈልግም በማለት ከይቅርታ መስመር ሊወጣይችላል:: ለምሳሌ አንዳንድ ወገኖቻችን የአገርን ሀብት ሰርቀዋል የሚባሉትን ግለሰቦች ይቅር ማለት የምንችለው የዘረፉትን ሲመልሱ ብቻ ነው ሲሉ ይደመጣሉ:: “ወንጀለኞች የእጃቸውን ማግኘት አለባቸው” የሚል አባባል በግለሰቦችና በድርጅት መሪዎች ሲነገር መስማት ዛሬ አዲስ አይደለም::
  • የበደለ ወይንም እርቅን ለማምጣት በመሐል የገቡ አስታራቂዎች ደግሞ ፍትህ እዚህ ውስጥ ለምን ትጠራለች፣ይልቅስ ሌላኛዋን ወዳጅ ምሕረት ትጠራ በማለት የተበደለ ፍትህን ትቶ በምሕረት አማላጅነት እንዲስማማ በመማፀን ይቅር ለመባባል ብቸኛው አማራጭ ምሕረት ነች ሊሉ ይችላሉ:: ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ የተሞከረውና ተሳክቶለታል የተባለው አካሄድ የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን እውነትን ካጣራ በኋላ የበደለ ጥፋቱን በተበዳይ ፊት አምኖ ከተፀፀተ ለበዳዩ ምሕረትን ማድረግ ነበር:: ነገር ግን በድለሃል የተባለው ግለሰብ እውነቱ ልክ አይደለም ወይም ይቅርታ አልጠይቅም ሲል ብቻ ወደ ፍትህ እንዲሄድ ተደርጓል::
  • ሁለቱም የእውነትን እውነተኛነት በመቀበል፣ተበዳይ በእውነት ረክቶ በዳይ በጥፋቱ ተፀፅቶ ይቅር በመባባል በመካከላቸው የነበረውን የጥልና ቂም ግድግዳን በማፍረስ በአዲስ ጎዳና ጉዞ ለመጀመር ሊስማሙ ይችላሉ::
 
ከዚህ ትንታኔ እንደምንረዳው እውነት በይቅርታ እሳቤ ውስጥ ትልቅ ድርሻ አላት:: ነገር ግን ሁሉም የሚስማሙበት “እውነት” ላይ መድረስ ቀላል አይደለም:: ስለዚህ እውነት የሚያፈላልጉ ወገኖች የበዳይና የተበዳይ አመኔታ ሊኖራቸውና በተቻለ መጠን ከማንም ተፅእኖ የራቁ ሊሆኑ ይገባቸዋል:: እውነት የይቅርታ ረዳት በመሆን ሐቁ ወለል ብሎ እንዲታይ ብታደርግም ይቅርታን ታመጣለች ብሎ መደምደም አይቻልም:: ወይ ይዘመትባታል አለበለዚያ አንቺ በቂ አይደለሽም ተብላ ፍትህና ምሕረት ይጠራሉ:: ስለዚህ እውነትን ማወቅ የችግሮቻችን መፍትሔ ይሆናል ብለን የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን ለማቋቋም ደፋ ቀና ከማለታችን በፊት ፍትህንና ምሕረትን መመልከት አስፈላጊ ነው::
 
ፍትህ
 
ፍትህ የበደለ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ በማድረግ፣የተበደለ እንዲካስ ወይም በበዳይ መቀጣት ተበዳይ እንዲረካ በማድረግ ትታወቃለች::ምንም እንኳ እውነቱ መታወቁ፣አጥፊውና ተጎጂው መለየቱ፣ለይቅርታ በቂ አይደለም በማለት ፍትህ ብትጋበዝም ያለ እውነት ግን ፍትህ ዋጋ የላትም:: ፍትህ በእውነት ላይ ትደገፋለች:: ፍትህ ስሜት የላትም:: የፍትህ ስራዋ እውነት ላይ በመመርኮዝ ሕግን ተገን አድርጋ ብይን መስጠት ነው:: ፍትህ የይቅርታ መሰረት ተደርጋ ጣልቃ ከገባች በኋላ የበደለና የተበደለ ከሚከተሉት ውስጥ የመሰላቸውን አቋም ይወስዳሉ::


  1. ሁለቱም በፍትህ ፍርደ ገምድልነት ላይ ቅሬታን ያሰማሉ:: ስለዚህ በመካከላቸው ይቅርታን ማምጣት አይችሉም:: ይልቁንም “ፍርደ ገምድሉን ፈራጅ” የጋራቸው ሦስተኛ ወገን ጠላት ያደርጉትና የጥላቸውንና የጥላቻቸውን አድማስ ያሰፉታል::
  2. የበደለ ቅጣቱን በውድም ይሁን በግድ ስለተቀበለ ይቅርታ መጠየቅ አስፈላጊ አይደለም ብሎ ሊደመድም ይችላል:: አልፎ ተርፎም ያለ ጥፋቱ እንደተፈረደበት እየተናገረ ሊኖር ይችላል:: “በወህኒ ቤት የታሰሩትን ሁሉ ምን ሰርተው እንደታሰሩ ብትጠይቋቸው ሁሉም ንፁሃን እንደሆኑና በግፍ እንደታሰሩ ይነግሯችኋል” የሚለውን ስላቅ መርሳት የለብንም::
  3. የተበደለም ፍትህ ስላገኘ የበዳይን ሥቃይና መከራ በማሰብ በዚሁ ረክቶ፣ይቅርታ ማድረግ የሚለውን መርህ ረስቶ፣ቀሪ ዕድሜውን ቂም ቋጥሮ መኖር ይችላል:: በዳይ በሰራሁት ተፀፅቻለሁ ቢልም እንኳ እውነቱን አይደለም በሚል ጥርጣሬ ይቅር ለማለት ሊቸገር ይችላል::
  4. የተበደለ የበዳይን መፀፀት በማየት ወይም የአምላክን ትዕዛዝ ለመፈፀም ወይም በኋላ ላይ የምንመለከተውን “ምሕረት”ን በመመርኮዝ የፍትህን ጉዳይ ለፍትህ ተቋማት በመተው የይቅርታ እጁን ሊዘረጋ ይችላል::ነገር ግን ወደዚህ ውሳኔ ያደረሰው ፍትህ ስለተሟላ እንዳልሆነ ማስተዋል ያስፈልጋል::
  5. በዳይ በዕርምት ላይ እያለ ህይወቱንና ድርጊቶቹን ሁሉ ለመፈተሽ እድል ያገኝና የተበደለን ይቅርታ ጠይቆ የተበደለም ይቅር ብሎ የበቀል፣ቂምና ጥላቻ ምዕራፍ ሊዘጋ ይችላል::
 
ፍትህ ምናልባት የተበደለን ታስደስት ይሆናል እንጂ በበዳይና በተበዳይ መካከል ይቅርታና እርቅን ለማምጣት ያላት ችሎታ በጣም ስስናደካማነው:: ቢሆንም ግን የበደለ በሰራው በደል ካልተፀፀተ በይቅርታ ላይ በር ስለሚዘጋ ያለው አማራጭ ፍትህ ትሆናለች:: በአሁኑ ጊዜ አቃቤ ህግ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ፍርድ ቤት እያቀረበ ያለው ስራው ስለሆነ ብቻ ሳይሆን በዳዮች ናቸው ተብለው የሚጠረጠሩት በይቅርታ እንሻገር ለሚለው ጥሪ በጎ ምላሽ ባለመስጠታቸውና ይልቁንም ንፁህ ነን እያሉ በመምጣታቸው ይመስለኛል::
 
ፍትህ አስተማሪ ልትሆን የምትችለው ማረሚያ ቤቱ በእውነት ማረሚያ ቤት ከሆነ ብቻ ነው:: ይህንን ለማድረግ ደግሞ ማረሚያ ቤቶች የታራሚዎችን አካላዊ፣ አእምሯዊ፣ ሞራላዊ፣ስነልቦናዊና መንፈሳዊ ብቃትን ለመገንባት በሚያስችላቸው ደረጃ ላይ መገንባት አለባቸው::

ከዚህ በተጨማሪ የፍትህ በትሯ የሚያም ስለሆነ “ነግ በኔ” በማለት ሰዎች ዳግመኛ ግፍ ከመስራት እንዲቆጠቡ የአስተማሪነት ሚና ልትጫወት ትችላለች:: ዳሩ ግን ሰዎች በተፈጥሮ ከተሰጣቸው ስጦታዎች ውስጥ አንዱ ፈጥነው የመርሳት ችሎታ ስለሆነ ዳግመኛ እንደማያጠፉ ከፍትህ የቅጣት በትር ሙሉ ዋስትና ማግኘት አይቻልም:: እንዲያውም  በትሯን በመልመድ ግፋ ቢል “ከርቸሌ”ነው፤ ወይም የገንዘብ ቅጣት ነው በሚልየበደልዑደትውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡

በኢትዮጵያ ግፈኛ መንግሥትን ታግለው የጣሉና ግፈኞችን ወህኒ ቤት የወረወሩ “ነፃ አውጭዎች” ከፍትህ አስተማሪነት የተነሳ ግፍ ከመስራት አልተቆጠቡም:: እስካሁን ያለው ታሪካችን ባመዛኙ “የፋሲካው በግ በገናው በግ ይስቃል”አይነት ነው:: ያው በሌሎች የጠሉትን የግፍ ድርጊት እስከሚወድቁ ድረስ ያደርጉታል:: ሆኖም አንዳንድ በመንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን የነበራቸው ግለሰቦች እነሱና ጓዶቻቸው በሚያውቋቸው ምክንያቶች ዘብጥያ ከወረዱ በኋላ በአገርና ሕዝብላይ በሰሯቸው በደሎች በመፀፀት ይቅርታ ለመጠየቅ በቅተዋል:: እነዚህ ግለሰቦች የፃፏቸውን መጽሐፍትና የሰጧቸውን ቃለ ምልልሶች ልብ ስንል ግን ወደ ፀፀትና ይቅርታ የመራቻቸው ፍትህ ሳትሆን በሚያምኗቸው ሰዎች በደረሰባቸው “ኢ-ፍትሃዊነት” ነው:: ለምሳሌ የአሁኑ ገዢ ፓርቲ አንዳንድ የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮችና የመንግሥት ባለስልጣናት ፓርቲያቸውና መንግሥታቸው በዜጎች ላይ ኢ-ፍትሃዊ ድርጊት እንደሚፈጽም ተገንዝበው ስርዓቱ ትክክል አይደለም፣የሰራሁትም ትክክል አልነበረም በማለት የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ የጠየቁት ያው ድርጊት በእነሱ ላይ ተፈጽሞ በማየታቸው ነው::  ወደዚህ መደምደሚያ እንዲደርሱ የረዳቻቸው ከ”ፍትህ” ይልቅ “ኢ-ፍትህ” ናት፤ ኢ-ፍትህ ራሷን አጋልጣ፣የበደለ አይኑን ከፍቶ አጥርቶ እንዲያይና ይቅርታእንዲጠይቅ አስተማሪና ምክንያት መሆኗ ደግሞ አስደንጋጭ ክስተት ነው፤”እሾህን በእሾህ” በመሆኑ!በእኔ ግምት እኛ ኢትዮጵያውያን “እሾህ ለእሾህ” መፍትሔ እንዲሆን፣ “ኢ-ፍትህ” ይቅርታን እንድታመጣልን የምንፈልግ አይመስለኝም፤ ፍትህ ደግሞ ብዙ ካልረዳችንእስቲ “ምሕረት” ትረዳን እንደሆነ እንመልከት::
 
ምሕረት
 
ፍትህ በዳይን ስትቀጣ ምሕረት ግን በነፃ ትለቀዋለች:: መርሳት የሌለብን ፍትህም ሆነች ምሕረት እውነት ታስፈልጋቸዋለች:: የበደለ መበደሉን ካላመነ ምሕረት ትርጉም የለውም:: ለምሳሌ አንድ ሰው ማጥፋቱ፣ግፍ መስራቱ፣መበደሉ፣የአገርንም ሆነ የግለሰብን ሀብት መስረቁ፣በእውነት አማካኝነት እየተረጋገጠበት ንፁህ ነኝ፣ህሊናዬን የሚፀፅተው ነገር የለም እያለምሕረት ማድረግ ትርጉም የለውም:: እንዲህ አይነቱ ሰው እውነት አርነት እንድታወጣው ፍትህ ዘንድ መሄድ ይኖርበታል::
​
የተበደሉ ለበደላቸው የምሕረትን እጆች የሚዘረጉባቸው የተለያየ ምክንያቶች አሏቸው::


  1. ምሕረት ማድረጋቸው ከራሳቸው በላይ ለአገር፣ለሕዝብ፣ላሁኑና መጪው ትውልድ ጥቅም ያመጣል ብለው ሲያምኑ፣
  2. የፈጣሪያቸውን ትዕዛዝ መፈፀም ከራሳቸው ጉዳት በላይ መሆኑን በማመን እሱ ካደረገላቸው ምሕረት በመነሳት እነርሱም ይህንኑ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ሲገነዘቡ፣
  3. የበደላቸው እውነቱን ተቀብሎ ይቅርታ መጠየቁ በራሱ በቂ ነው ብለው ሲቀበሉ፣
  4. ምሕረት ማድረግ በይቅርታ መንገድ ላይ በተዘረጋው ማዕቀፍ የመጨረሻው ድርጊት ይሆናል ብለው ገና ከጅምሩ የተስማሙበት ሲሆን::
 
ምሕረት በዳይና ተበዳይ የኋላቸውን መጥፎና አስከፊ ምዕራፍ ዘግተው፣ወደፊት በአዲስ ተስፋ እንዲኖሩ ያላት ሚና ታላቅ ነው:: በምሕረት ሂደት ውስጥ በዳይና ተበዳይ፣በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የበደሉ ተባባሪዎችና ገፈት ቀማሾች ተሳትፎ ሳይኖራቸው፣በአንድ አዳራሽ ውስጥ የተሰበሰቡ ቡድኖችና ግለሰቦች በበዳዮች ስም ይቅርታ ከጠየቁና በተበዳዮች ስም ይቅርታናምሕረት ካደረጉ፣ይቅርታና  ምሕረት ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት አይችሉም:: ቢሞክሩ ግን በየቤቱ “ያልተነካ ግልግል ያውቃል” የሚላቸው ቁጥሩ ብዙ ነው::
 
የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ መንግሥት ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተርዐቢይአሕመድ በፓርቲያቸውና መንግሥታቸው ስም የኢትዮጵያን ሕዝብይቅርታ ሲጠይቁ እርሳቸውንና አብረዋቸው ያሉትን የለውጥ አራማጆችን እውነተኛነት በመረዳት ሕዝቡ ይቅርታ ማድረጉንና ድጋፉን በተለያየ መንገድ ገልጿል፤እየገለጸም ነው:: ነገር ግን ይህ ድርጊት የሁሉም የመንግሥትና የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ድምፅ መሆኑን እርግጠኛ ሆኖ በሙሉ ልብ ለሁሉም ይቅርታ ማድረግሕዝቡ የተቸገረው ወደ መድረክ ብቅ ብለው ቃለ ምልልስ የሰጡ አንዳንድ ከፍተኛ አመራሮች እነሱ በሚያውቋቸው ምክንያቶች የጠቅላይ ሚንስትሩን የይቅርታ መልዕክት ባለማስተጋባታቸው ነው:: በስልጣን ላይም ሆነ ነገ ስልጣን ላይ ለመውጣት እየተፎካከሩ  ያሉት ሁሉ በእውነት ታድሰው፣እርስ በርሳቸውናከኢትዮጵያ ሕዝብጋር ያለፈውን መጥፎ ታሪካችንን በይቅርታና ምሕረት ዘግተው፣መልካም የሆነውን በማጉላት፣ሰው በአመለካከቱ የማይታሰርባት፣እንግልት፣መፈናቀል፣ግድያ የማይኖርባት፤ጊዜው ያለፈበትን የተንኮል፣ግላዊና ጊዜያዊ ጥቅም የሚያስገኝ የፖለቲካ አካሄድን ዘመኑን በሚመጥን የሰለጠነ አካሄድ በመተካት፤ዜጎችየራሳቸውን ማንነት ይዘው፣እርስ በርስ ተከባብረው፣ከጎረቤቶቻቸው ጋር ያላቸውን የወሰን ችግሮች በውይይትና በውይይት ብቻ በመፍታት፣ሁላችንም አሸናፊና ደስተኛ ሆነን ለመኖር የምትመች አገርን ለመገንባት ቢነሱ ለኢትዮጵያ በረከት ይሆናሉ::
 
በዓለማችን ውስጥ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሕዝቦች በሰላምና በደስታ ዘና ብለው ይኖራሉ:: እኛስ እንዲህ ብንኖር ምን ይለናል?
 
በይቅርታና ምሕረት ሂደት ውስጥ ምሕረት ያደረገ ለአገር፣ለሕዝብና ለትውልድ ባለውለታ ነው:: ምሕረት ማድረግ ከጀግንነት በላይ ጀግንነት ስለሆነ ለምሕረት አድራጊዎች ወደር የሌለው ዘላቂ የሆነ ክብር ሊሰጣቸው ይገባል:: ምሕረት አድራጊዎችን የረሳ አገርም ይሁን ሕዝብየቆመበትን መሠረትና የተተከለበትን ምሰሶ ረስቷልና የተረገመ ነው:: 
 
ምሕረት ዘላቂ መፍትሔ ልትሆን የምትችለው ከይቅርታ ጋር ከተቆራኘች ነው:: ምሕረት ያደረገ ይቅርታም ማድረግ መቻል አለበት:: ምክንያቱም ስሜት ያላት ይቅርታ ነች::ምሕረት በደለኛን ነፃ ታደርጋለች እንጂ ስሜት የላትም፤ስሜቷ የሚለካው በይቅርታ ነው::
 
ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተርዐቢይአሕመድ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፓርላማ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ስለ ይቅርታና ምሕረት ፍቺ ሰጥተው ነበር:: ለምሕረት የሰጡት ላይ ስስማማ ስለ ይቅርታ የሰጡት ግን አልተስማማኝም:: እርሳቸው እንዳሉት መንግሥት ለታሳሪዎች ይቅርታ ያደረገው አንደኛ ማስረጃ ሳይኖረው ስላሰራቸው፤ሁለተኛመንግሥት ራሱ ሽብርተኛ ስለነበር፤ሦስተኛ የኢትዮጵያ ሕዝብለኢህአዴግና ለመንግሥት ይቅርታ ስላደረገ ሲሆንበይቅርታ የተፈቱት ማስረጃ ሲገኝባቸው ተመልሰው ሊታሰሩ እንደሚችሉ እግረ መንገዳቸውን ጠቁመው ነበር:: በኔ እምነት ይህ ድርጊት ይቅርታ ማድረግ ሳይሆን መንግሥትና ገዢው ፓርቲ በራሳቸው ላይ እርምት መውሰዳቸውን ማሳያና ሕዝቡን ይቅርታ የመጠየቃቸው መገለጫ ነው::
 
በጽሁፌ መጀመሪያ እንዳልኩት የይቅርታ ጽንሰ ሐሳብ በፈጣሪና በሰዎች መካከል ያለ ግንኙነት ነውና ፈጣሪ ይቅር ካለ በኋላ ይቅርታ ላደረገለት ጥፋት ማስረጃ ለመፈለግ አይቧዝንም:: (የጠቅላይ ሚንስትሩ አባባል ክዚህ በኋላ ለሚሰሩት ጥፋት ከሆነ ግን እስማማለሁ)::ምሕረት በዳይን ነፃ ስትለቅ፣ይቅርታ ቂምንና በቀልን ማስወገጃ ስለሆነች አብረው መተግበራቸው የምሕረት ድካም መና ሆኖ እንዳይቀር ያደርጋል::
 
ማጠቃለያ
 
ይቅርታ፣ሰላም፣እውነት፣ፍትህና ምሕረት የማኅበረሰብ እሴቶች፣ የሃይማኖቶች ምሰሶዎች ናቸው:: ሁሉንም አንድ ላይ ቀላቅለን ይቅርታንና እርቅንና ለማምጣት ከተጠቀምንባቸው ይቅርታንና እርቅን ውስብስብ ያደርጉትና የማንወጣው ንትርክ ውስጥ ያስገቡናል:: ስለዚህ ለአገራችን ችግሮች የትኞቹ ያዋጡናል፣የትኞቹ ይቅርታን ውጤታማና ፈጣን ያደርጉታል፣የትኞቹ ወጪና ጉልበት ይቆጥቡልናል፣የትኞቹን ከዚህ በፊት ሞክረናቸው ለውጥ አላመጡልንም፣የአገራችንማኅበረሰቦችይቅር የመባባል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ልማዶች ወደየትኛዎቹ ያዘነብላልና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች አንስቶ የሚበጀውን መምረጥ ይኖርብናል::
 
በባህላችን በደል የደረሰበት ማኅበረሰብ፣ቤተሰብና ግለሰብ ለደረሰበት በደል አፀፋውን አለመመለሱ እንደ ደካማነት የሚያስቆጥረውና በየተገኘው አጋጣሚ የሚያሰድበው መሆኑ በአገራችን ሕዝብ መካከል የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ይቅርታን እንደ እሴት ለመትከል ብዙ ጊዜና  ድካም ይጠይቃል:: ለውጡ የተጀመረው “በፍቅር እንደመር፤በይቅርታ እንሻገር” በሚል መርህ ስለሆነ ከጊዜ ርዝመት የተነሳ ይህን መርህ በመዘንጋት፣ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከሚመጡ ግፊቶችና ከፍትህ ጥማት የተነሳ ከይቅርታ ይልቅ ወደ በቀል እንዳንሄድና የበፊቱን ታሪካችንን እንዳንደግም ብርቱ ጥንቃቄ ልናድርግ ይገባል:: “ደርግ ያለ ምንም ደም” ብሎ ጀምሮ በደም ጎርፍ እንደተጨማለቀ ሳንረሳ ክእርሱ ስህተት መማር አገር አዳኝ ብልህነት ነው:: እስካሁን በጥሩ መጀመር እንጂ በጥሩ መጨረስ አላወቅንበትም::
 
በይቅርታ መሻገር በአገራችን ማኅበረሰብና ፖለቲካ ውስጥ ያልተለመደ ጽንሰሃሳብ ስለሆነ በደንብ በማብላላትና በተለያየ መንገድ በመማማር ቶሎ ወደ መፍትሔብንመጣ መልካም ነው እላለሁ::
 
እኔ ይቺን ታክል ሞክሬያለሁ፤እናንተ ደግሞ የጎደለውን በመሙላት “ተደምረን” ለአገራችንና ሕዝቧ ችግሮች የመፍትሔአካል እንሁን::ወደፊት ደግሞ “በፍቅር እንደመር” በሚለው ላይ ጫር ጫር ለማድረግ እሞክራለሁ::

Email: wakanda.Ethiopia@gmail.com
0 Comments

    Amharic

    Archives

    January 2022
    October 2020
    August 2020
    April 2020
    November 2019
    September 2019
    July 2019
    April 2019
    November 2018
    October 2018
    September 2018
    August 2018
    July 2018

    Categories

    All
    Current Affairs
    Sport
    The God Factor Forum

    RSS Feed

Copyright © 1999 - 2023
  • ደወል