myEthiopia.com
  • ደወል

አንድ ነገር እናድርግ?

9/25/2019

0 Comments

 
0 Comments

​መሻሻል ያለበት ሕገ መንግሥቱ ወይስ እኛ?

9/19/2019

0 Comments

 
ዋካንድ ዘኢትዮጵያ 
 
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊከ (ኢፌዴሪ) ሕገ መንግሥት አዋጅ ታውጆ በተግባር ላይ ከዋለ 24 ዓመታትን አስቆጥሯል:: አሁን የመጣው ለውጥ ከመጀመሩ በፊት በገዢው ፓርቲና በመንግሥታዊ መዋቅሮቹ ሲነገር የነበረው “የማንነት ጥያቄዎች መልስ አግኝተዋል፤ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት ሙሉ ለሙሉ ተረጋግጧል፤ ሕዝቦች በመከባበርና በመቻቻል የሚኖሩበት ሥርዓት ተዘርግቷል፤ ከዚህ በኋላ ትኩረታችን ዋነኛ ጠላታችን የሆነውን ድህነት ለማጥፋት ልማት ላይ ነው” የሚል ነበር:: የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችና ካድሬዎቻቸው ይህን ቢሉም ይህ አባባል ከፕሮፓጋንዳ በስተቀር ሌላ ፋይዳ እንዳልነበረው እንኳን የኢትዮጵያ ሕዝብ እነርሱም ያውቁታል:: በግምባሩ ውስጥ ያሉት ድርጅቶችና አጋሮቻቸው “ነፃ ወጥተን ነፃ አውጥተናል” እያሉ “ነፃ አውጪ” የሚለውን ስያሜያቸውንየሙጢኝ ማለታቸው በሚናገሩትና በሚያምኑበት መፍትሔ ሙሉ እምነት እንዳልነበራቸው ማረጋገጫ ነው:: የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት ሙሉ ለሙሉ ከተረጋገጠ ነፃ የሚወጡት ከማን ነው? እንወክለዋለን የሚሉት ሕዝብ መብቱ ተከብሯል ካሉ ትኩረታቸው መሆን ያለበት ኢትዮጵያን መገንባት ላይ መሆን አልነበረበትም?
ከለውጡም በኋላ ቢሆን፦ ተሸብበው የነበሩት ምላሶች ሲፈቱ፣ ታስረው የነበሩት እጆችና እግሮች ሲለቀቁና ተሰደው የነበሩት ወደ አገር ቤት ሲመለሱ ለዋናው ችግራችን ምላሽ ሰጥቷል ተብሎ ሲነገርለትና ዓመታዊ ፌስቲቫል ሲደረግለት የነበረው መፍትሔ እውነት እንዳልነበር በአገራችን የተከሰቱት ግጭቶችና ግድያዎች፣ መፈናቀሎች፣ የክልልነት፣ የማንነትና የወሰን ጥያቄዎች፣ በክልል መስተዳደሮች መካከል የተከሰቱት የእርስ በእርስ ውንጀላዎች፣ ሕዝብ በሕዝብ ላይ እንዲነሳና እንዳይተማመን የሚደረጉ የጥላቻ ቅስቀሳዎችና የጦርነት ነጋሪቶች ወዘተ ምስክሮች ናቸው::
እነዚህ ተሞክሮዎች መጥፎ ቢሆኑም የሚያስተምሩን ቁም ነገር ግን አላቸው:: ይኸውም የሰዎችን መብት የሚጥሰውም ሆነ የሚያከብረው፣ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጨውም ሆነ የሚያቀራርበው በወረቀት ላይ የሰፈረው ሕገ መንግሥት ሳይሆን ሰዎችመሆናቸውን ነው::
 
ይህ እውነታው ቢሆንም በአገራችን ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶችና ተከታዮቻቸው ዘንድ ሕገ መንግሥቱ በራሱ ችግራችንን ይፈታ ይመስልራሳቸውንከችግሩ ነጥለው ግዑዙን ሕገ መንግሥት ትልቅ የመነጋገሪያ ርዕስ አድርገውታል፤ እንደ ፖለቲካ አመለካከታቸውም የተለያየ ትርጉም ይሰጡታል:: ለአንዳንዶቹ “የአምላክ ቃል” ነው:: የአፈጻጸም ችግር እንጂ በይዘቱ እንከን አልባ ነው:: ስለዚህ ምንም መሻሻል ሊደረግበት አይገባም ባይ ናቸው:: ለአንዳንዶች ደግሞ “ሰምና ወርቅ” አለው:: “ሰሙ”ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አብረው እንዲኖሩ የሚያደርግ ሲሆን “ወርቁ”ደግሞ አገር መበተኛ ሰነድ ነው:: ስለዚህ በሴረኞች የተቀረጸ ስለሆነ መቀየር ወይም መሻሻል አለበት ይላሉ:: ለአንዳንዶች ብዙ “አንድምታዎች” አሉት:: በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያለ እያንዳንዱ አንቀጽ ትርጉሙ “አንድም እንዲህ አንድም እንደዚያ” ሊሆን ይችላል:: ስለዚህ አስፈላጊ ሲሆን ከእነርሱ የተለየ ቋንቋ የሚናገሩትን ወገኖቻቸውን ከቀያቸው ያፈናቅሉበታል ሲያሻቸው ደግሞ ሌላ ክልል ሄደው ይሄም የእኛ ነው ይሉበታል:: ለአንዳንዶች ደግሞ “መንፈስ” ነው:: ሕገ መንግሥት ሰው ይሁን ቁስ ይሁን ኢህአዴግ ይሁን አይታወቅም:: የማይታይ፣ የማይጨበጥ፣ “ሁሉ በሁሉ የሆነ” ኃይል ነው:: ብቻ ሕገ መንግሥቱ ተጣሰ ሲባል የጣሰውን “ጋኔን” መቀመቅ ለማውረድ አገርን ቀውጢ ያደርጋሉ::
 
አንድን ችግር ለመፍታት የሚሰጥ መፍትሔ ሌላ ያላሰብነውን ችግር ሊያስከትል ይችላል:: ለምሳሌ አምፖል የተሠራበት ዓላማ ብርሃን እንዲሰጥ ነው:: አምፖል የተፈጥሮ ብርሃን በማይኖርበት ጊዜ ብርሃን በመስጠት የተሠራበትን ተግባር ሲፈጽም ሙቀት በማመንጨት ያላሰብነውን ችግር ይወልዳል:: ይህንን ያልታሰበና እርሱ ደግሞ የሚወልዳቸውን ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ሳይንቲስቶችና መሐንዲሶች ያለማቋረጥ ምርምር በማድረግ መፍትሔ ይፈልጋሉ:: ኢትዮጵያን ለማዳን የሰጠነው መፍትሔ ሌላ ያላሰብነውን ችግር ቢፈጥር እንደ ባለ አእምሮዎች ላልታሰበው ችግር መፍትሔ መፈለግ እንጂ በችግሩ መደሰት ወይም መቆዘም ወይም ለሥልጣን መወጣጫ መጠቀም ለአገርና ሕዝብ ምንም ጥቅም አያስገኝም::
 
አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት የተረቀቀው ከቅንነት ነው ብለን ገምተን እንደወረደ ስንመለከተው በመግቢያው ላይ በግልፅ የተቀመጡ የታሰበለት(intended)ዓላማዎችና እምነቶች አሉት:: በመግቢያው መደምደሚያ ላይ:- የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች “ገነት” የምትመስል ኢትዮጵያን አብረው ለመገንባት ያስችላቸው ዘንድ ከላይ ለተጠቀሱት ዓላማዎችና እምነቶቻቸው በማሰሪያነት እንዲያገለግላቸው ሕገ መንግሥቱን መርጠው በላኳቸው ወኪሎቻቸው አማካኝነት ማጽደቃቸውን ያበስራል::እነዚህን ዓላማዎችና እምነቶችን ማሳካት ይችሉ ዘንድ ከመሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች አንስቶ እስከ “የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን እስከ መገንጠል ድረስ  ያለምንም ገደብ”መብት እንዳላቸው በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ተደንግጓል:: ሕገ መንግሥቱ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን መብት በማስከበር ኢትዮጵያን እንዳትበታተን ያደርጋታል በሚል እሳቤ እንደተቀረጸ የሕገ መንግሥቱ ጠበቃ ነን ከሚሉ ወገኖቻችን ለብዙ ዓመታት ሲናገሩ ሰምተናል::  ይህን ንግግራቸው እውነት ነው ብለን በቅንነት ብንወስደው ሕገ መንግሥቱ የረቀቀውና የጸደቀው ትልቅ አገርን ለመገንባት እንጂ ትልቁን አገር ትንሽ ለማድረግ አይደለም ብለን መደምደም እንችላለን::  ስለዚህ ሕገ መንግሥቱን በመንተራስ የአገሪቱን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት የሕገ መንግሥቱ ዓላማ ስላልሆነ እንደ ችግር ተወስዶ መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል:: ላልታሰበ (unintended) ችግር መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ዛሬ በሕገ መንግሥቱ ስም ለውጡን ቀልብሶ የሕዝብን ተስፋ ለማጨለም፣ ተጣሰ በማለት ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማጋጨትና ኢትዮጵያን ለመበተን የሚፈልጉ የፖለቲካ ተዋንያን አሉ:: እነዚህ ድርጊቶች ግን የሕገ መንግሥቱ ዓላማዎችና እምነቶች አይደሉም:: አገርን ለመገንባትና አብሮ ለመኖር እንጂ ለመበተንና ሕዝብን ለማጋጨት ተሰብስቦ ሕገ መንግሥት ማርቀቅ አያስፈልግም:: ባልና ሚስት በቃል ኪዳን የሚተሳሰሩት ተቻችለው በደስታ አብረው ለመኖር እንጂ ለመፋታት አይደለም:: ፍቺ የጋብቻ ቃል ኪዳን ያልታሰበ(unintended)ክስተት ነው:: ሕገ መንግሥቱ ሲጸድቅ በከፍተኛ የደስታ ስሜት ሲጨፍሩ የነበሩት ተወካዮች ያስጨፈራቸው አንቀጽ 39 ያውም “…እስከመገንጠል…” የምትለዋ ቃል ከነበር ትልቅ ስህተት ሠርተዋል ምክንያቱም ያ ድርጊት ተጋቢዎች በሰርጋቸው ዕለት ልንፋታ እኮ መብት አለን ብለው ከመጨፈር ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ነው::
በምሣሌነት በአሁኑ ወቅት መነጋገሪያ የሆነውን የቋንቋን ጉዳይ እንመልከት:: “ማንኛውም ብሔር ብሔረሰብ ሕዝብ በቋንቋው የመናገር የመጻፍ ቋንቋውን የማሳደግ …መብት አለው” የሚለውን መልካም ሀሳብ ዘረኞች ሕዝብንና ሕዝብን ለማራራቅ በመጠቀም ያልታሰበ(unintended)ችግርን ይፈጥሩበታል:: ጤነኛ አእምሮና ለአገራችን በጎ ሀሳብ ካላቸው ሰዎች የሚጠበቀው ግን ከሕገ መንግሥቱ የታሰበለት(intended)ዓላማዎች ውስጥ አንዱ የኢኮኖሚ ትስስር መፍጠር ነው፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ መግባባት ያስፈልጋል፤ ስለዚህ ምን ማድረግ ይሻለናል? ብለው መምከርና መመካከር ነው::
 
በሕዝብ ስም መናገር አልችልም:: የእኔና የእኔ ብጤዎችአጀንዳግን ሕገ መንግሥቱ ይሻሻል ወይስ አይሻሻል፣ መጪው ምርጫ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ይደረግ ወይስ ይራዘም አይደለም:: እነዚህ የፖለቲከኞች አጀንዳዎችሲሆኑ የእኛን ቀልብ ስበው ድጋፋችንን ለማግኝት የሚጠቀሙባቸው ስልቶች ናቸው:: ከለውጡ በኋላ በተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች መካከል እየተደረጉ ያሉት ክርክሮች ከምርጫ 97 የቀጠሉ ትእይንቶች ይመስላሉ፤ አዲስ ነገርና የተሻሻለ ሀሳብ የለባቸውም:: ያ ትእይንት ደግሞ በምን እንደተጠናቀቀ ከሁላችን በላይ እነርሱ ያውቁታል፤ ዋጋ ከፍለውበታል፤ አስከፍለውበታልም:: ሕገ መንግሥቱን እንኳን ተራው ሕዝብ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እንኳ እንዳላነበቡት ከሚናገሯቸው ንግግሮች መገመት ይቻላል:: መሻሻል ካለበት ከሁሉም በፊት መሻሻል ያለበት በወረቀት ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ሳይሆን የእኛ  በተለይ በአገራችን ፖለቲካ ወሳኝ ሚና ያላቸው ወገኖቻችን ውስጣዊ ባሕርይ ነው:: 
 
ላለፉት አርባ ዓመታትና ከዚያም በላይ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ድባብ የተቆጣጠሩት ፖለቲከኞች በሕይወታቸው ብዙ ውጣ ውረድ አጋጥሟቸዋል:: ለአብነት ያክል:- በተለያዩ መንግሥታት ታስረዋል፣ ተገርፈዋል፣ ጸያፍ ስድብ ተሰድበዋል፣ ተሰቃይተዋል፣ ቤተ ሰቦቻቸውንና ዘመዶቻቸውን በሞት አጥተዋል፣ ክተደገሰላቸው የሞት ድግስ ተርፈዋል፣ ጓደኞቻቸው ከአጠገባቸው ተወስደው ተረሽነዋል፣ አንዳንዶቹም ፊታቸው ተገድለዋል፣ የጓዶቻቸውንና የጠላቶቻቸውን ሬሳ ተራምደው አልፈዋል፣ እርስ በእርሳቸው ለሞትና  ለግርፋት አሳልፈው ተሰጣጥተዋል፣ አንዳንዶቹ የዘረኛነት ሰለባ ሆነው ሌላውንም በክለዋል፣የልጅነትና የወጣትነት ጊዜያቸውን በትግል ውስጥ በመሆን በዱር በገደሉ አሳልፈዋል:: እነዚህ ወገኖቻችን ምንም ያክል ጥንካሬ ቢኖራቸውም ሰዎች ስለሆኑ ከእነዚህ ገጠመኞቻቸው የተነሳ የስነልቦናዊና ማኅበራዊ ቀውሶች ሰለባ እንደሆኑ ብንገምት ከእውነቱ አንርቅም:: እነዚህን ቀውሶች ከሕይወታቸው ለማስወገድ ምን እንዳደረጉ ባላውቅም ሁሉም በተለይ አገርን ለመምራት በፉክክር ላይ ያሉት እልባት ቢያደርጉለት መልካም ነው:: ቢፈልጉ በእምነታቸው መሠረት ወደ ውስጥ የሚመለከቱበትን ጊዜና ሁኔታ አመቻችተው ቢያንስ ከራሳቸውና ከፈጣሪያቸው ጋር ታርቀው እንደ “አዲስ” ሰው ወደ መድረክ ብቅ ማለት ይችላሉ:: ነገር ግን ሁሉም ይህንን መንገድ ይከተላሉ ማለት ስለማይቻል ፈቃደኛ ከሆኑ (የእኔ ምክር ግን አስገዳጅ እንዲሆን ነው) ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የስነልቦና አዋቂዎችን እርዳታና ምክር  አግኝተው ውስጣዊ ተሃድሶ ቢያደርጉ ለእነርሱም ለኢትዮጵያ ሕዝብም ጠቃሚ ነው:: ዛሬ ቴክኖሎጂ በጣም ያደገበት ዘመን በመሆኑ የስነ አእምሮ የዕውቀት ዘርፍ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አድጓል:: የስነ አእምሮ እድገት ደግሞ የስነ ልቦናን ዘርፍ እንዲያድግ ረድቶታል:: የስነ ልቦና አዋቂዎች እንደሚሉት ከሆነ መጥፎ ወይም ክፉ ነገር ከሰው አእምሮ ውስጥ ሊጠፋ አይችልም፤ በመልካም ነገር ሲተካ ብቻ ነው በባሕርያችን ላይ ያለው ተፅእኖው የሚቀንሰው:: ቅዱስ መጽሐፍም “አሮጌውን ሰው አስወግዱ…በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ…አዲሱን ሰው ልበሱ” ይላል::
 
በይቅርታ እንሻገር፤በፍቅር እንደመር የሚለውመርህ በአንድ ዓመት ውስጥ ተረስቶ ቂምና ጥላቻ እያመረቀዙ ነው:: ለምን ብንል ይቅርታንና ፍቅርን ለመተግበር በሕይወታችን ውስጥ የተፈጠሩት ስነልቦናዊና ማኅበራዊ ቀውሶች አቅም ስላሳጡን ነው:: የበደሉንን ይቅር ለማለትና ሰዎችን ሰው በመሆናቸው ብቻ ማፍቀር የምንችለው ውስጣዊ ማንነታችን ሲቀየር ብቻ ነው:: ይቅርታና ፍቅር ቂምንና ጥላቻን ሲተኩ እኛም እንፈወሳለን፤ ኢትዮጵያም እፎይ ትላለች:: ስለዚህ ከሕገ መንግሥቱ በፊት መሻሻል ያለብን እኛ ነን:: ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል የእኛ ክፉ ባሕርያት ከውስጣችን መወገድ ቅድመ ሁኔታ ነው:: ሕገ መንግሥቱን ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ለማሻሻልም ሆነ ለመቀየር መቀባበል፤ የሌላውን ችግርና ስጋት እንደራስ ችግርና ስጋት መመልከት፤ መደማመጥ፤ መከባበር፤ ያለፈውን በይቅርታ መዝጋትና እንደ አዲስ መጀመር፤ ሰውንና አገርን መውደድ፣ በአጠቃላይ በጎ ባሕርያትን መላበስ ይጠይቃል:: ሕገ መንግሥቱን ያነበባችሁ ሁሉ ምን ለማለት እንደፈለግሁ ይገባችኋል::
 
በዚሁ አጋጣሚ መልካም አዲስ ዓመት ከአዲስ አስተሳሰብና ውስጣዊ ማንነት ጋር ለሁላችን እመኛለሁ::
 
 
 
 
 
 
 
 

0 Comments

    Amharic

    Archives

    January 2022
    October 2020
    August 2020
    April 2020
    November 2019
    September 2019
    July 2019
    April 2019
    November 2018
    October 2018
    September 2018
    August 2018
    July 2018

    Categories

    All
    Current Affairs
    Sport
    The God Factor Forum

    RSS Feed

Copyright © 1999 - 2023
  • ደወል