በዋካንዳ ዘኢትዮጵያ
ከዚህ በፊት “እንዴት በይቅርታ እንሻገር?” በሚል ርዕስ በጻፍኩት ጽሁፍ መጨረሻ ላይ “በፍቅር እንደመር” ላይ ለመጻፍ ቃል ገብቼ ስለነበርቃሌን ለማክበርና የፍቅርን ታላቅ ኃይል ለመጻፍ በማሰላሰል ላይ እያለሁ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ የተከሰተ አንድ ገጠመኝ ትዝ አለኝ:: “ዳይናሚክስ” የሚባል የ”ፊዚክስ” ዘርፍ ትምህርት አስተማሪየነበረ ኢጣሊያዊ፦ ለመፍታት ከባድ የሆነ ጥያቄ እንዴት እንደሚሠራ አሳየንና “ገብቷችኋል?” ብሎ ጠየቀን፤ ሁላችንም ዝም አልን:: “አልገባችሁም?” ብሎ እንደገና ጠየቀን፤ አሁንም ዝም አልን:: ከዚህ በኋላ የሚከተለውን በላቲን ቋንቋ ጥቁር ሰሌዳ ላይ በጠመኔ ጻፈ:: “Vox Clamantis in Deserto” ትርጉሙም “በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ” ነው:: በአገራችን ኢትዮጵያ ወቅቱን በተመለከተ ብዙ መልካም ሐሳብ ያለባቸው ጽሁፎች፣ አውደ ጥናቶችና ንግግሮች ተደርገዋል፤ እየተደረጉም ነው:: በኢትዮጵያ ውስጥ የመጣውን ለውጥ አራማጆች:- ያለፉትን በደሎችና ስህተቶች ለታሪክ ተመራማሪዎች ትተን “በይቅርታ እንሻገር”፤ የተሰሩት በጎ ሥራዎች ላይ ለመጨመር “በፍቅር እንደመር” የሚል መርሕ ይዘው ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ወደ የተሻለ አብሮ የመኖር፣ዴሞክራሲና እድገት ለማድረስ የሚያስችልን ጎዳና ለማስተካከልና የለውጡ በጎ አስተሳሰብ ተቋሟዊ እንዲሆን ሌትና ቀን እየሠሩ ይገኛሉ:: የእነዚህ መልካም አሳቢዎችና ለውጥ አራማጆች ድካም እንደ እኔ አስተማሪ ሰሚ ያጣ የምድረ በዳ ጩኸት ሆኖ ይሆን ወይ የሚል ስጋት አለኝ:: ምክንያቱም የብዙዎቻችን ጆሮዎች የሚከፈቱት ህዝብን ለሚያፋቅሩና ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሔ ለሚያመጡ ሐሳቦች ሳይሆን ለተራ አሉባልታ፣ለጥላቻና ግልብ ጀብደኝነት በመሆኑ ነው::
0 Comments
|