myEthiopia.com
  • ደወል

መንግሥት የሕዝብን የቃላት ትርጉም በወጉ ይረዳ

1/12/2022

0 Comments

 
ዋካንዳ ዘኢትዮጵያ
 
የዶ/ር ዐብይ አሕመድ መንግሥት ፈጣንና ምስጢራዊ ከመሆኑ የተነሳ ዱብዳ ርምጃዎችን በመውሰድና የሕዝብን ጆሮዎች ጭው የሚያደርጉ መረጃዎችን በመልቀቅ ይታወቃል:: ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ሰሞኑን በእነእስክንድር ነጋ በእነጃዋር መሐመድና በስድስት የህወሃት ከፍተኛ ባለሥልጣናትላይ የነበሩትን ክሶች ማቋረጡን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሰበር ዜና ያስታወቀው ድርጊት ነው::
 
ይህ ሰበር ዜና ድንጋጤን የፈጠረው በሁለት ሳምንታት ያሸነፍናቸው ጠላቶቻችን ምን ኃይል አግኝተው ነው መንግሥት እንደዚህ ድንገተኛ ውሳኔ ለመወሰን ያስገደደው በሚል ይመስለኛል:: በተለይ ደግሞ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው በአገሪቱ ውስጥ በሙሉ ኃይላቸው ጉልህ ተሳትፎ እያደረጉ ባሉበት ወቅትና የተለያዩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በመገናኛ ብዙሃን በመቅረብ ከህወሃት ጋር ድርድር አይታሰብም ባሉበት “ማግስት” መሆኑ ጉዳዩ ድንጋጤ ብቻ ሳይሆን ቁጣም አስከትሏል::
 
ይህ ጉዳይ ትልቅ የአገር ጉዳይ ነውና ኢትዮጵያውያን ሁሉ እየተነጋገሩበት ይገኛሉ:: እኔም ጉዳዩን ከሰማሁበት ጊዜ ጀምሮ በግሌም ከወዳጆቼም ጋር በመሆን ማብሰልሰሌ አልቀረም:: በተለይ ደግሞ በሁለት የአገራችን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ማብራሪያከተሰጠ በኋላ ውሳኔያችን ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ነውና እባካችሁ ተቀበሉልን የሚል የአክብሮት መማጸኛ ከቀረበልን በኋላ ለምን ሙሉ ለሙሉ መርካት አቃተን የሚለው ጥያቄ ትኩረቴን ስለሳበው በ2010 ዓ.ም የታወጀውን የምህረት አዋጅና በ2008 ዓ.ም የዓቃቤ ሕግን ሥልጣንና ኃላፊነት ለመወሰን የወጣውን አዋጅ ሳነብ በመንግሥትና በተራው ሕዝብ መካከል “ምህረት” የሚለው ቃል ፍችውና ጽንሰ አሳቡ የተለያዩ መሆናቸውን አስተውያለሁ::
 
እርግጥ ነውጠቅላይ ዐቃቤ ሕግዶ/ር ጌድዮን ጢሞቴዎስምህረትም ይቅርታም አላደረግንም የሆነው ክስ መቋረጥ ነው ቢሉም  በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ማብራሪያ ግን ክስ ማቋረጥና ምህረት ተደባልቀዋል:: ክስ ማቋረጥ፣ ምህረት፣ይቅርታ ልዩነት ቢኖራቸውም በጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ የተሰጡት ፍቺዎችና አሠራሮች ለባለሙያ ይጠቅማሉ እንጂ በተራው ሕዝብ ዘንድ የጎላ ልዩነት የላቸውም:: ምክንያቱም እውነታው ወንጀለኞች ለጊዜውም ይሁን በቋሚነት ከእስር ተፈተው በተከሰሱበት ወንጀሎች አሁን አይጠየቁም:: 
 
“ምህረት” የሕግ ቃል ብቻ ሳይሆን የኅይማኖት ቃልም ነው:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ኅይማኖተኛ ነውና ከኅይማኖቱ የወረሰው ፍቺ አለው:: ለነገሩ “የቃል ትርጉም የሚገኘው በማኅበረሰቡ ውስጥ ነው”ይባል የለ! በተጨማሪም የምህረት ትርጉም በግዕዙ ግሥ መቅጣትን ከማቅናት ጋር ያስተካክላል::
 
መንግሥት “ምህረት” ሲል የእንግሊዝኛ አቻው “Amnesty”ሲሆን እንደ እኔ ያለው ተራው ሕዝብ “ምህረት” ሲል የእንግሊዝኛ አቻው “Mercy” ነው::  ከእንግሊዝኛው ልዩነት ባሻገር መንግሥትና ሕዝብ በቃሉ አጠቃቀም ላይ መሠረታዊ ልዩነት አላቸው:: መንግሥት “ምህረት”አደረግሁ ሲል ወንጀለኛው በጥፋቱ መፀፀቱንና ከጥፋቱ መመለሱን ማረጋገጫ ኖሮት ሳይሆን የግለሰቡ መፈታት ለአገር ጥቅም አለው በሚል መነሻ ነው:: እንዲያውም የመንግሥትን የሞራል ልቀትን የሚያጎላ ነው:: በሕዝብ አረዳድ ግን ከምህረት በፊት ፀፀትና ንስሀ አሉ:: ስለዚህ ወንጀለኛ በመንግሥት ምህረት ተደረገለት ሲባል ሕዝብ ወንጀል ከሠራው ግለሰብ በጥፋቱ መፀፀቱንና ሁለተኛ አይለምደኝም ማለቱን ይጠብቃል::የሕዝብ ስጋት ምንጩ ለምህረት ካለው መረዳት አንጻር ስለሆነ ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር የተፈቱት ግለሰቦች እንደገና በሕዝብ ላይ ፍጅትና በደል ላለማድረሳቸው ምን ዋስትና አለ ነው:: ተፀፅተዋል? ሁለተኛ እንደ በፊቱ አናደርግም ብለዋል? ፈጣሪ እንኳን ምህረት የሚያደርገው በፍጹም ልባቸው ለተፀፀቱ ነው:: ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ አዎንታዊ ምላሽ ካልተገኘ በስንት ጸሎትና እግዚኦታ በስንት መስዋእትነት የተገላገልናቸው ሰዎች ተመልሰው በመካከላችን መከሰታቸው ምቾት አይሰጥም::መንግሥት ከፈጣሪ በላይ ርህራሄ ያሳየ መስሎ ታይቶኛል::
 
ሌላው ያለመግባባቱ መንስዔ መንግሥት ክሱን ያቋረጠው በዳዮችን ነጻ ለማውጣት እንጂ ተበዳዮችን ከግምት ውስጥ ሳያስገባ በመሆኑ ነው::ለውጡ በተጀመረበት ወቅት መንግሥት የብዙ ሰዎችን ክስ አቋርጧል፣ የምህረት አዋጅ አውጥቶ ምህረት አድርጓል:: በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደስ አለው እንጂ አልከፋውም፤ አልተቆጣም:: ምክንያቱም በዚያን ጊዜ ከእስር የተፈቱትና ወደ አገር ቤት የገቡት ተበዳዮች ስለሆኑ መንግሥት ደግሞ በዳይ ስለነበር ነው:: የመንግሥት ርምጃ በሕዝብ ላይ በሠራው በደል መፀፀቱን ማሳያ ነበር::  የአሁኑ ግን የተለየ ነው:: አሁን ከእስር የተለቀቁት ግለሰቦች በዳዮች ናቸው፤ ለዚያውም ሕዝብን!በሕዝብ የምህረት ጽንሰ አሳብ አረዳድ መሠረት ምህረት የሚያደርገው የተበደለው አካል ነው:: በኅይማኖቶቻችን ምህረት አድራጊው የበደልነው ፈጣሪ ነውና::ፈጣሪ ምህረት ሲያደርግ ወዶና የአጥፊውን እዳ ራሱ ችሎ ነው:: መንግሥት የወንጀለኞችን ክስ ሲያቋርጥ ለተበደሉት ምን አስቧል? የተበደሉትን ማማከር ለምን አልቻለም? በተበደሉት ስም ምህረት ማድረግ ይችላል ወይ? ለነዚህና መሰል ጥያቄዎች መልስ ስላልተሰጠ ቁጣ ብቻ ሳይሆን ሀዘንም በሕዝብ ልብ ውስጥ እየፈሰሰ ነው::
 
እነዚህን የአረዳድ መዛባቶች ተገንዝበን ማስተካከያ ብናደርግ ወይም በሚቀጥሉት ውሳኔዎች ውስጥ ከግምት ውስጥ ቢገቡ በመንግሥትና ሕዝብ መካከል የሚፈጠሩትን ክፍተቶች ማጥበብ ይቻላል የሚል አስተያየት አለኝ:: ሕዝብ በመንግሥት ውሳኔ ላይ እምነትን በመጣል ከቁጣና ቁጭት ይልቅ ድጋፍነቱን ይቀጥላል:: ውስብስብ ችግሮችና ግጭቶች ባሉባት አገራችን ኢትዮጵያ መንግሥት የባለሙያ ቃላት ትርጉምን ብቻ ሳይሆን በሕዝቡ ውስጥ ያለውን ፍቺ ተረድቶ ጥያቄውን ለመመለስ ጥረት ቢያደርግ ጥቅም እንጂ ጉዳት አይኖረውም:: 
 
ዶ/ር ጌድዮን ጢምቴዎስ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት በአገራችን ኢትዮጵያ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት በመደበኛ የፍትህ ሥርዓት ስለማይቻል “የሽግግርና የተሃድሶ ፍትህ” ሥርዓትን እንከተላለን ብለውነበር:: እንግዲህ በዚህ ሂደት ውስጥ የተበደሉት በቂ ውክልና እንዲያገኙ፣ ድምጻቸው እንዲሰማ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉትን እሴቶችና ጽንስ አሳቦች ከግምት ውስጥበማስገባት፣ ፍትህ፣ ምህረት፣ ይቅርታ የመሳሰሉትን ቃላት “ሕዝባዊ ትርጉም“ በመስጠት በአገራችን ዘላቂ ሰላምና እድገት የሚመጣበት ጊዜ ቅርብ እንዲሆን ምኞቴም የዘወትር ጸሎቴም ነው::
 
በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ማብራሪያና ተማጽኖ ያቀረቡት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተደረገው ግጭት የመጀመሪያው ሰለባ በሆኑትና የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት ለማስከበር ከሌሎች የአገራችን የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን መስዋእትነት በከፈሉና እየከፈሉ ባሉ ከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ የጦር መኮንኖች፣ ውዶቻቸውን በሞት በተነጠቁ ቤተሰቦችና ወታደሮች፣ የአገሪቱና የክልሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የውጭ አገራት ተወካዮች በተገኙበት ፊት ቆመው ነው:: የዚህን እንድምታ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ በጭንቅ መልሰን ያገኘነውን አንድነታችንን በሚያፈርስ መንገድ ትናንት ለአገራችን አንድነት የቆመና ከለላ የሆነን የመንግሥት አመራርን “አሳልፎ ሰጠን” በማለት በችኮላ ባንመዝን የተሻለ ነው እላለሁ:: ከዚህ ይልቅ በመንግሥትና ሕዝብ መካከል ያሉትን ክፍተቶች ለማጥበብ ከችግሩ ይልቅ የመፍትሔ አካል ብንሆን ለወደፊቱ ርምጃችን ጥቅም ይኖረዋል:: 
0 Comments

    Amharic

    Archives

    January 2022
    October 2020
    August 2020
    April 2020
    November 2019
    September 2019
    July 2019
    April 2019
    November 2018
    October 2018
    September 2018
    August 2018
    July 2018

    Categories

    All
    Current Affairs
    Sport
    The God Factor Forum

    RSS Feed

Copyright © 1999 - 2023
  • ደወል