myEthiopia.com
  • ደወል

​ቡጢያችንን አቁመን ተባብረን ለውጡን እናስቀጥል

7/6/2019

0 Comments

 
ዋካንዳ ዘኢትዮጵያ
 
በከባድ ክብደት የዓለም የቦክስ ሻምፒዮን የነበረው ታዋቂውማይክ ታይሰን “የመጀመሪያውን ቡጢ እስኪቀምስ ድረስ ሁሉም ቦክሰኛ እቅድ አለው”ብሎ ነበር::  ቦክሰኞች ተፎካካሪያቸውን ለማሸነፍ የሚያስችላቸውን ዘዴዎች በደንብ አጥንተውና ተዘጋጅተው ወደ ፍልሚያው ቦታ ይገባሉ:: ሆኖም ከባድ የሆነ ቡጢ ፊታቸው ላይ ሲያርፍ ምድርና ሰማዩ ይዞርባቸውና የተዘጋጁበት እቅድ ሁሉ እንደ ጉም ብን ብሎ ይጠፋባቸዋል:: ማይክ ታይሰን ወደ ግጥሚያ ከመግባቱ በፊት እንዲህ ዓይነት ተግዳሮት እንደሚገጥመው በሚገባ እንደሚያውቅ ከዚህ አነጋገሩ መረዳት ይችላል::  የንግግሩ ዋናው ጭብጥ ግን አንድ ቦክሰኛ አሸናፊ መሆን የሚችለው ፊቱ ላይ ያረፈበትን ቡጢ በጽናት ተቋቁሞ፣ ይዞት የመጣውን እቅድ ከነባሪያዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ለድል መብቃቱ ላይ ነው::
 
በአገራችን ኢትዮጵያ “በድንገት” የተከሰቱት የለውጥ አራማጆች:-“በይቅርታእንሻገር፣ በፍቅር እንደመር” የሚል መርሕ ይዘው ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግናና እውነተኛ ዴሞክራሲ ለመምራት ከተነሱ ከዓመት በላይ ሆነው:: በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በለውጡ ላይ ብዙ “ቡጢዎች” አርፈውበታል::ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰኔ 24 ቀን 2011ዓ.ም  ከተወካይ ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ ከዘረዘሯቸው ቡጢዎች በተጨማሪ በክልሎችና በፌዴራል መንግሥት መካከል ያሉ አለመግባባቶችና ተግዳሮቶች፣ በአንዳንድ ክልሎች መካከል ያሉና የነበሩ የጦርነት እምቢልታና ነጋሪቶች፣ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ከፍተኛ የሆኑ የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎች፣ ውዥንብሮች፣ በምናምንቴዎች የሚነገሩ ተራ ስድቦች፣ አሉባልታዎች፣እርሳቸው እንዳሉት እኛ የማናውቃቸው ሌሎች ሴራዎች በለውጡና በመሪዎቹ ላይ ከተሰነዘሩት ከባድ፣ መካከለኛና ቀላል “ቡጢዎች” ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው::
 
እነዚህ ቡጢዎች በውድ ወገኖቻችን ላይ የሕይወት፣ የአካልና የሥነልቦና ጉዳት፣ በአገራችን ላይ ብርቱ ጠባሳ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ደግሞ ድንጋጤንከዚያም ሐዘንን ከዚያም ስጋትን ከዚያም ውዥንብርን ከዚያም ተስፋ መቁረጥን እንደ ደረጃቸው አስከትለዋል፤እያስከተሉም ነው:: የለውጡም መሪዎች ሰዎች ስለሆኑ በሕዝቡ ውስጥ ለተከሰቱት እነዚህ ስሜቶች ሰለባ ለመሆናቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ ላይ ይታይ የነበረው ሐዘን፣ ቁጭትና የልብ ስብራት ምስክር ነው:: የቡጢዎቹ ዋና ዓላማ ለውጡ በታሰበለት ጎዳናና መርሕ እንዳይሄድ በማድረግ ማጨናገፍና የለውጡን አራማጆች ወይ በዝረራ አለበለዚያም በበቃኝ ከጨዋታው ውጪ ማድረግ ነው::ቡጢዎችን ተከትለው የሚሰጡ አንዳንድ መግለጫዎች፣ ዛቻዎች፣ ስድቦችና የሴራ ትንታኔዎች የዚህ ዓላማ ተቀጥላ ናቸው::ከመንግሥት አካላትም ወጥነት የጎደላቸው መግለጫዎች ለሴራ ተንታኞች ሰፊ በር በመክፈት ለዚህ ዓላማ እንደ ግብዓት በመሆን ማገልገላቸውን ልብ ልንል ይገባል::
 
ሌተና ጄኔራል አበባው ታደሰ በጄኔራል ሰዓረ መኮንን የአስከሬን ሽኝት ላይ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው “አንድነቱን፣ሰላሙን፣ ፍቅርን፣ መቻቻልንና ብልፅግናን” ነው:: ሕዝብ ለውጡን አይቃወምም:: እርቀሰላምን፣ ይቅርታን፣ ፍቅርን፣ ዴሞክራሲንና ብልፅግናን የሚቃወም ሕዝብ እንዴት ሊኖር ይችላል? በሕዝብ ስም ግን ለእነዚህ መልካም እሴቶች አደናጋሪ ትርጉም በመስጠት  በለውጡ ላይ ቡጢ የሚያሳርፉ መኖራቸውን ግን በዓይናችን እያየን ነው:: በልመና በምትኖርና ብድሯን መክፈል ባልቻለች በዚህች ድሃ አገር ውስጥ ይኼ ሁሉ ልዩ ኃይል፣ ይኼ ሁሉ ሚልሽያ፣ ይኼ ሁሉ ዝግጅት፣ ይኼ ሁሉ የጦር መሣሪያ እንዲኖረን በተለያዩ ደረጃ ያሉና መሠረታዊ የምጣኔ ሀብት እውቀት ያላቸው መሪዎቻችን ለምን እንደፈለጉ ለእኔ ግልፅ ባይሆንልኝም ለውጡ አቅጣጫውን ስቶ ወደሌላ መንገድ ከሄደ ግን በአገራችንና ሕዝቧ ላይ የሚያስከትለውን ውድመት በዝርዝር ለማሰብ እኔ በግሌ አልፈልግም:: 
 
እርቀ ሰላም ለማውረድ ኮሚሽን ቢቋቋምም ያለ ሁላችን ተሳትፎ በጥቂት የኮሚሽን አባላት ብቻ እርቀ ሰላም ማምጣት አይቻልም:: እነርሱን ከመጠበቅ ይልቅ ቢያንስ ለጥቂት ሳምንታት ለቡጢ የምናደርጋቸውን ዝግጅቶችንና ድርጊቶችን በማቆም ለሰላም፣ ይቅርታና እርቅ ያለንን ተነሳሽነት በተግባር ብናሳይ ምናለበት?ቢያንስ አንድ ክልል ወይም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወይም አክቲቪስት ወይም የአገር ሽማግሌ ወይም የሃይማኖት መሪ ወይም መምህራን ወይም የታክሲ አሽከርካሪዎች ወይም ጋዜጠኞች ወይም አርቲስቶች ወይም … በኢትዮጵያ ውስጥ ደም የማይፈስበት ሳምንታት እንዲኖሩ ጥሪ ቢያደርጉ፣ ሌሎች ጥሪውን ተቀብለን፣ ቀን ቆርጠን፣ ያለሴራ፣ ያለግጭት፣ ያለሞት መኖር እንዲለምድብን ይህን ብናደርግ ምን ክፋት አለው? እስቲ እንጀምር? እስቲ አገራችን ከደም ትረፍ?ወገኖቼ:- ሁሉም ነገር በእያንዳንዳችን እጅ ላይ ነው:: ውድ የሆኑ ወገኖቻችንን ደም ያፈሰሰ፣ውርደት እንጂ ክብር የማያሰጥ፣ ኪሳራ እንጂ ሽልማት የማያስገኝ የጥፋት ትእይንትን ከመመልከት አገርንና ሰውን በሚፈውስ ተግባር ላይ ጊዜያችንን ብናጠፋ አይሻልምን?
 
ለለውጡ መንስዔ የሆነው የሕዝብ እንቢተኝነትና ተቃውሞ ቢሆንም ለውጥን ግን ሕዝብ መምራት ስለማይችል የለውጡ አቅጣጫና ግብ ከፀሐይ በታች በመሪዎቹ ቆራጥነት፣ ጽናት፣ ብልሃት፣ ችሎታ፣ ልምድ ፣ብስለትና ዝግጅት መዳፍ ውስጥ ነው:: ምንም እንኳ ከዚህም ከዚያም የሚሰነዘሩ ቡጢዎች ቢኖሩም ለውጡን የሚመሩት ሁሉ ለማሸነፍ እንደተዘጋጀና ቡጢዎች ሲያርፉበት እቅዱን ከሚያጋጥሙት ተግዳሮቶች ጋር በማጣጣም ተስፋ ሳይቆርጥ እስኪያሸንፍ ድረስ በፅናት እንደሚቧቀስ ቦክሰኛ በመሆን፣ ተስፋ ሳይቆርጡ፣ የተነሱበትን ዓላማና መርሕ ባለመልቀቅ የኢትዮጵያን ታላቅነት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ፈር ቀዳጅና መሠረት ጣይ በመሆን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ታሪክ እንደሚሠሩ እምነቴ ፅኑ ነው:: በተቃርኖ የቆሙትን ወደ መሐል በመሳብ፣ መሐል ላይ የቆሙትን ከለውጡ ዓላማዎች ጋር አብረው እንዲቆሙ በመጋበዝ፣ ለለውጡ ስኬት የሚደክሙትን በማበረታታትና በመደገፍ እንደተለመደው ብልሃት የተሞላበት በሳል አመራር እየሰጡ የቡጢዎችን መጠንና አቅም እየቀነሱ እንደሚቀጥሉ ተስፋ አደርጋለሁ::
 
የለውጡ ዓላማዎችና ግቦች እንኳን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ለውጭ አገር ሕዝቦች ጭምር አጓጊ ናቸው:: ከአፍሪካ መሪዎች እንዴት መልካም ነገር ይወጣል ብለው በመገረም ስኬቱን የሚከታተሉ ብዙ ናቸው:: እኛ ኢትዮጵያውያን የጉዳዩ ባለቤት ስለሆንን የለውጡ መሪዎች በቡጢዎች ብዛት ተስፋ እንዳይቆርጡና የተነሱበትን ዓላማ ስተው ወደኋላ እንዳይመለሱ በቃልና በተግባር ልንደግፋቸው ይገባል:: ናፓሊዎን እንዳለው “ዓለማችን በበለጠ እየተጎዳች ያለችው በክፉ ሰዎች ዓመፅ ሳይሆን በመልካም ሰዎች ዝምታ ነው”:: በዚህ ጉዳይ ዝምታ ወርቅ አይደለም::

ኢሜል፥ wakanda.ethiopia@gmail.com
0 Comments

    Amharic

    Archives

    January 2022
    October 2020
    August 2020
    April 2020
    November 2019
    September 2019
    July 2019
    April 2019
    November 2018
    October 2018
    September 2018
    August 2018
    July 2018

    Categories

    All
    Current Affairs
    Sport
    The God Factor Forum

    RSS Feed

Copyright © 1999 - 2023
  • ደወል